መግቢያ
የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የተሰጣቸውን ኃላፊነት፣ ተግባርና ተልዕኮ በብቃት፣ በጥራትና በውጤታማነት እንዲወጡ ለማድረግ አሰራራቸውን ግልጽነትና ተጠያቂነት ባህልን በማዳበር አድልዎ የሌለበት መልካም አስተዳደር በመገንባት፣ የሕዝብ አገልጋይነትን ባህል በማዳበር ለህብረተሰቡ ፍትሀዊ የሆነ አገልግሎት በመስጠት፣በሥነ-ምግባር የታነፀ ኃላፊና ሠራተኛን በማፍራትና መልካም ሥነ-ምግባርን በማስፈን ውጤታማ ሥራ እንዲሠራ ማስቻል፣ የሥነ-ምግባር ግድፈቶች እንዳይፈጸሙ ማስገንዘብ፤ ተፈጽመው ሲገኙ የእርምት እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል ሥርዓት መፍጠር ይገባቸዋል፡፡ የመንግሥት ሰራተኞችም የሥነ-ምግባር ጥሰት ፈፅመው ሲገኙ እንደየጥፋቱ አይነት አስተዳደራዊ፣ የወንጀል ወይም የፍትሐብሔር ተጠያቂነት አለባቸው፡፡ ይህ ጽሁፍ ሁለት ክፍል ያላው ሲሆን በመጀመራው ክፍል የመንግሥት ሠራተኛ ምንነትን፤ የስነ ምግባር ምንነትን እና አስፈላጊነትን እንዲሁም የስነ ምግባር መርሆችን የምናይ ሲሆን በክፍል ሁለት የስነ ምግባር ጥሰት የሚያስከትለው የሕግ ተጠያቂነትን እና የቅሬታ አቀራረብና አፈታት ሥርዓት በአጭሩ የምንዳስስ ይሆናል፡፡
የመንግሥት ሠራተኛ ማነው
አዲሱ የፌደራል የመንግሥት ሰራተኞች አዋጅ ቁጥር 1353/2017 አንቀጽ 2/1/ ላይ እንደተደነገገው የመንግሥት ሠራተኛ ማለት በፌደራል መንግሥት መሥሪያ ቤት ውስጥ በቋሚነት ተቀጥሮ የሚሰራ ነው፡፡ ሆኖም ሚኒስትር እና ሚኒስትር ዴኤታ፣ ኮሚሽነር እና ምክትል ኮሚሽነር፣ ዋና ዳይሬክተር እና ምክትል ዋና ዳይሬክተር እንዲሁም በተመሣሣይ ደረጃና ከዚያ በላይ የሆኑ የመንግሥት ተሿሚዎችን፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን እና የፌደሬሽን ምክር ቤት አባላትን፤ የፌደራል ፍርድ ቤት ዳኞች፣ ዓቃቢያነ ሕግን፤ ዲፕሎማቶችን ፣በመንግሥት የተለዩ ደኅንነት ተቋማት ፣መከላከያ ሠራዊት ፣የፌደራል ፖሊስ አባሎች እንደማይጨምር ተደርጎ ተተርጉሟል፡፡ ይህ ሲባል እነዚህ ከላይ የተጠቀሱ ሰራተኞች የፌደራል መንግሥት ሰራተኞች ቢሆኑም በፌደራል የመንግሥት ሰራተኞች አዋጅ ቁጥር 1353/2017 ሳይሆን የየራሳቸው የተለያየ መተዳደሪያ ሕግ እና ደንብ ስላላቸው ነው፡፡ በአወጁ አንቀጽ 2(3) መሠረት የመንግሥት መስሪያ ቤት ማለት ራሱን ችሎ በአዋጅ ወይም በደንብ የተቋቋመና ከመንግሥት በሚመደብ መደበኛ በጀት የሚተዳደር እና በአስፈጻሚ አካላት አዋጅ ቁጥር 1263/2014 በተቋቋሙ እና በቀድሞ የፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች አዋጅ ቁጥር 1064/2010 እንዳይሸፈኑ የተደረጉ የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤትን ያጠቃልላል። በተጨማሪ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በተግባር የመንግሥት መስሪያ ቤቶችን ዝርዝር እያወጣ ባለመሆኑ እና ከሲቪል ሰርቪስ መርሆዎች ዋነኛው የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ተመሳሳይ የሆነ አስተዳደር እንዲከተሉ ማድረግ በመሆኑና በርካታ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የአስተዳደር ነጻነት ያስፈልጋቸዋል በሚል ከመንግሥት መሥሪያ ቤት ትርጉም ውጪ በመሆናቸው ለሀገረ መንግሥት ግንባታ ስኬት ሲባል የመንግሥት መስሪያ ቤት ሰፋ ብሎ እንዲተረጎም ተደርጓል፡፡
ከዚህ ትርጉም የምንረዳው አንድ ሰው የፌደራል መንግሥት ሠራተኛ ነው የሚባለው በፌደራል መንግሥት መስሪያ ቤት ማለትም ራሱን ችሎ በአዋጅ ወይም በደንብ የተቋቋመ እና ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል በመንግሥት በሚመደብለት በጀት የሚተዳደር ሆኖ በሚኒስቴሮች ምክር ቤት በሚወጣው የመንግሥት መስራያ ቤቶች ዝርዝር ውስጥ የተካተተ የፌደራል የመንግሥት መስሪያ ቤት ውስጥ በቋሚነት ተቀጥሮ ወይም ተመድቦ ሲሰራ ነው፡፡ እዚህ ላይ የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣው አዋጅ ቁ 881/2007 አንቀጽ 2(2) እና 2(5) ላይ የተደነገጉትን ማየት አስፈላጊ ይሆናል፡፡ በዚህም የመንግሥት ሠራተኛ ማለት በመንግሥት መስሪያ ቤት ወይም በመንግሥት የልማት ድርጅት ተቀጥሮ፣ ተሹሞ፣ ተመድቦ ወይም በሕዝብ ተመርጦ በቋሚነት ወይም በጊዜያዊነት ሥራን የሚያከናውን ሰው እንደሆነ ተገልፅዋል፡፡ በአንቀጽ 2(12) ላይ በጊዜያዊነት ሥራን የሚያከናውን ሰው ማለት በቋሚነት ሳይቀጠር በክፍያ ወይም ያለክፍያ በሙሉ ጊዜ ወይም በትርፍ ጊዜ የመንግሥት መስሪያ ቤት ሥራን የሚያከናውን ሰው ሲሆን ተለማማጅ ሠራተኛን ያካትታል በማለት ደንግጓል፡፡ በዚህም ጊዚያዊ ሠራተኛ ሆነዉ የሚሰሩ ሰራተኞች በስራቸዉ አጋጣሚ የሕዝብ ሀብት ለመዝረፍ የሚያስችል አጋጣሚ እንዳይኖር ለማድረግ በዚህ ሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡ በመሆኑም ማንኛውም በመንግሥት ተቋም ውስጥ በጊዜያዊ ሠራተኝነት ተቀጥሮ፣ የኮንትራት ውል ተፈራርሞ፣ ወይም ልምድ ለማግኘት በሚል በክፍያ ወይም ያለክፍያ በሙሉ ጊዜም ይሁን በትርፍ ጊዜ ሥራ የሚያከናውን ሰው ሙስና ቢፈፅም ተጠያቂ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ይሁንና በሙስና ህጉ ለመንግሥት ሠራተኛ በተሰጠው ትርጓሜ የመንግሥት ሠራተኛ በቋሚነት ወይም በጊዜያዊነት ሥራን የሚያከናውን ሠራተኛን የተመለከተ ሲሆን በአፈፃፀም ወቅት በፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች አዋጅ ቁጥር 1353/2017 ላይ ጊዜያዊ ሠራተኛ ስላልተካተተ በሙስና አዋጅ ከተሰጠው ትርጓሜ ጋር የሚመሳሰል አረዳድ እንዲኖር ግልፅ ትርጓሜ ማስቀመጥ ያስፈልጋል፡፡
የሥነ-ምግባር ምንነት
የሥነ ምግባር ምንነት በተለያዩ ምሁራን የተለያዩ ትርጉም ይሰጠዋል፡፡ በዚህም ሥነ-ምግባር በአንድ ማኅበረሰብ የጋራ ህይወት፤ መንግሥት በሚሰጠው አገልግሎትም ሆነ በግሉ ዘርፍ ውስጥ ተቀባይነት ያለውንና የሌለውን ጥሩና መጥፎን ለመለየት፣ ለመግለፅና ስርዓት ለማስያዝ እንዲሁም የሙያና ሞራል ገዴታዎችን ለመወጣት እንድንችል የሚረዳን ሕግና ደንብ ወይም የባህሪ ደረጃ እንደሆነ በተለያዩ ምሁራን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ይገለፃል፡፡ መልካም ሥነ-ምግባር ሰዎች ማኅበራዊ ግዴታቸውን በመወጣት ግብረ-ገባዊ ብቃት እንዲኖራቸው ለሕግ ተገዥ እንዲሆኑ፤ በሌሎች ኪሳራ እንዳይበለፅጉ ለማድረግና ሀገርን ለዜጎች የተሻለች መኖሪያ ከማድረግ አንጻር ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ይታመናል፡፡ ስለሆነም የሕዝብ አደራ በመሸከም ህዝባዊ አገልግሎቶችን ከሚሰጡ የመንግሥት ሠራተኞች ከፍተኛ የሥነ-ምግባር ደረጃ ይጠበቃል፡፡
የመንግሥት ሰራተኞች ሥነ ምግባር ምንነት እና አስፈላጊነት
የሞያ ሥነ-ምግባር በአንድ የሞያ ዘርፍ የተሰማሩ አባላት በጋራ የሚመሩበት፣ የሚከተሉትና የሚተዳደሩበት ራሳቸውንና ስራቸውን ለመቆጣጠር የሚያግዝ የሥነ-ምግባር ደረጃን የሚያመለክት መርህ ወይም ደንብ ነው በማለት የተለያዩ ጥናቶች ይገልጹታል፡፡ በሌላ አነጋገር በአንድ ሙያ የተሰማሩ ሙያተኞች እውቀታቸውንና ችሎታቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ ሞያዊ ግዴታቸውንና ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ አቅጣጫ የሚያሲዝና የሚገዙበት ደንብ ማለት ነው፡፡ በጥቅሉ ስንመለከተው የሙያ ሥነ-ምግባር ማለት የአንድ ሞያ ባለቤት የሆኑ ሰዎች የዚያን ሙያ የሥነ-ምግባር መመሪያዎች፣ ይዘትና አስፈላጊነትን በተመለከተ የደረሱበት ስምምነት ወይም አስተያየት ነው ለማለት ይቻላል፡፡ ከዚህም በመነሳት የሞያ ሥነ-ምግባር የተለየ ግብረ-ገባዊ እሴት ሳይሆን በአንድ ሙያ ውስጥ የታቀፉ ሰዎች በስራቸው ሂደት የሚመሩበት ትክክለኛ ጠባይ ወይም ተቀባይነት የሌለውን ነገር የማያንፀባርቁበት ተግባር እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ስለሆነም ማንኛውም የመንግሥት ሠራተኛ የስራውን ስነ ምግባር በሚገዘው አዋጅ፣ ደንብ፣ ወይም የሥነ ምግባር ደንብ መመሪያዎች በመከተል አገልግሎቶችን መስጠት ይጠበቅበታል፡፡
የሞያዊ ሥነ-ምግባር የተለያዩ ጠቀሜታዎች ያለው ሲሆን የሞያ ሥነ ምግባር ደንቦች ሞያዊ ወጣ-ገባነትን ለማስቀረት፤ ከሞያው የሚጠበቁ ኃላፊነቶችንና ግዴታዎችን ለማመላከት፤ ቁጥጥር ለማድረግና የተገልጋዮችንም ሆነ የባለሙያዎችን ጥቅምና ደኅንነት ለመጠበቅ፤ የላቀ ሞያዊ ሥነ ምግባር ላላቸው እውቅና ለመስጠትና ሌሎቹን ለማበረታታት፤ በሙያው የሚነሱ አስቸጋሪ ጉዳዮችን በጋራ መፍትሔ ለማፈላለግ፤ ሞያዊ ጥራትን ለማስጠበቅ እና ለማስቀጠል ወዘተ እንደሆነ ይጠቀሳል፡፡
የሥነ-ምግባር መርሆዎች
የመንግሥት መስሪያ ቤቶች መልካም ሥነ-ምግባር በተላበሱ ሠራተኞችና የስራ መሪዎች በሚገባ ካልተደራጁ ከአድሎ የጸዳ፣ ፍትሀዊና ቀልጣፋ የሆነ አገልግሎትን ለዜጎች ሊሰጡ አይችሉም፡፡ ስለሆነም የመንግሥት ሠራተኞች በሥራ ላይ ቆይታቸው ሊመሩበትና ሊከተሏቸው የሚገቡ 12 የሥነ-ምግባር መርሆች እነሱም ቅንነት፤ ታማኝነት፤ ግልፀኝነት፤ ሚስጥር መጠበቅ ሐቀኝነት፤ ተጠያቂነት፤ሕግ አክባሪነት፤ የሕዝብ ጥቅምን ማስቀደም፤ ተገቢ የሆነ ምላሽ መስጠት፤አድልኦ አለመፈጸም፤ ህጋዊ በሆነ ሰልጣን ብቻ መገልገል፤ አርአያነትን መርህ በማድርግ ስራቸውን ማከናወን ይጠበቅባቸዋል፡፡ መርሆዎቹ የመንግሥት ሠራተኞችና ባለስልጣናት በህብረተሰቡ ውስጥ ያላቸውን ሚናና መንግስታዊ አገልግሎቶችን ለዜጎች ሲሰጡ ሊኖራቸው የሚገቡ የባህሪ መገለጫዎችን የሚያሳዩ ናቸው፡፡ ይሁንና በአብዛኛው የመንግሥት ተቋማት በጽሑፍ ታትመው ከመታየታቸው ባለፈ ተግባራዊ ሲሆኑ አይታዩም፣ በመሆኑም እነዚህን መርሆዎች ለመንግሥት ሠራተኛውም ሆነ ለሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ጠቃሚ በመሆናቸው በሁሉም አካላት ሊተገበሩ ይገባል፡፡
የመንግሥት መሥሪያ ቤት ወይም ሠራተኛ የመንግሥት አገልግሎትን ሲሰጡ ሊከተሉት የሚገባ መሠረታዊ ዕሴት እና መርሆች ፡-
የመንግሥት መሥሪያ ቤት ወይም ሠራተኛ ሊከተል የሚገባው መሠረታዊ ዕሴትን በተመለከተ የፌደራል የመንግሥት ሰራተኞች አዋጅ ቁጥር 1353/2017 አንቀጽ 4 ስር ያስቀመጠ ሲሆን ይህም ማንኛውም የመንግሥት መሥሪያ ቤት ከተሰጠው ተልዕኮ አንፃር ተቋማዊ ዕቅዱን ከግብ ሊያደርስ የሚያስችል የሥራ ባህል እና የአመራር ሥርዓት ተከትሎ ማከናወን እንዳለበት እንዲሁም በመንግሥት መስሪያ ቤት ውስጥ ያለ አመራር ወይም ሠራተኛ አምስት መልካም ዕሴቶችን ማለትም መፍትሔ አፍላቂነትንና ግብረገብነትን፣ ግልጽነትና ተጠያቂነትን፣ ፕሮፌሽናሊዝምና እውነተኛነትን፣ቅልጥፍናና ውጤታማነትን፣ ብዝኃነትና አካታችነት አሠራርን ተግባራዊ ማድረግ እንዳለበት ይደነግጋል፡፡ የመንግሥት መስሪያ ቤት ወይም ሠራተኛ ሊከተል የሚገባው መሠረታዊ መርሆችን በአዋጁ አንቀጽ 5 ስር ያስቀመጠ ሲሆን ማንኛውም የመንግሥት መሥሪያ ቤት ወይም ሠራተኛ፤ በማናቸውም የፖለቲካ አስተሳሰብ፣ የፓርቲ አሠራር፣ ተፅዕኖ ወይም ጣልቃ ገብነት ሳይመራ የተሰጠውን ተግባር እና ኃላፊነት ሕግን ብቻ መሠረት በማድረግ ማከናወን እንዳለበት፤ ብቃትና ውድድርን መሠረት ያደረገ የብሔር ብሔረሰቦች፣ የአካል ጉዳተኞች፣ የወጣቶች እና የጾታ ስብጥር ዕቅድ አውጥቶ በሥራ ላይ እንዲውል ማደረግ እንዳለበት እንዲሁም የመንግሥት አገልግሎት በግልጽነት እና ተጠያቂነት የሚረጋገጥ ሥርዓት ገንብቶ መስጠት እንዳለበት፤ የተሰጠውን ተግባርና ኃላፊነት ባለማከናወን ያጓደለ ኃላፊ እና ሠራተኛ ተጠያቂ እንደሚሆን ይደነግጋል፡፡
በአዋጁ አንቀጽ 37 መሠረት ነፃና ገለልተኛ የመንግሥት አገልግሎትና አስተዳደር ሥርዓት መገንባትን በተመለከተ የመንግሥት አገልግሎትና አስተዳደር በግለሰባዊ ምኞትና ፍላጎት ላይ ከተመሠረተ የሰው ኃይል ምልመላ፣ መረጣና ስምሪት ነፃ የሆነና በዕውቀት ላይ የተመሠረተ፣ በምክንያታዊ የሥራ ክፍፍል የሚመራ፣ የአስተዳደር ሥርዓት መዘርጋት እንዳለበት፡፡ መንግሥታዊ እና ፖለቲካዊ ሥራ የራሱን አሠራር ሥርዓት ተከትሎ ሳይቀላቀሉ መሥራት የመንግሥት ሠራተኛ የተቀጠረበት እና ውል የገባበትን ሙያዊ ሥራ በመንግሥት ህጎች መሠረት እና የሜሪት ሥርዓትን ተከትሎ ከፖለቲካ፣ ከሃይማኖት እና ከመሳሰሉ ድርጅቶች ጣልቃ ገብነት ነፃ በሆነ መልኩ የሞያ ሥራውን መፈፀም እንዳለበት ይደነግጋል፡፡ በተጨማሪም በፖለቲካ ወገንተኝነት የሥራ ዕድል እና ደረጃ ዕድገት የማይጠይቅ፣ በሕዝብ ምርጫ አሸንፎ ለሚመጣ ፓርቲ በሚመሠረተው መንግሥት ውስጥ በብቃትና በታማኝነት የሚሠራ እና ህዝቡን በመሰጠት የሚያገለግል የመንግሥት አገልግሎትና አስተዳደር እንዲገነባ በትኩረት መሥራት እንዳለበት እንዲሁም የመንግሥት መስሪያ ቤቶች የሞያ መደብ እና የሥራ ደረጃ፣ መዋቅራዊ አደረጃጀት፣ አገልግሎት አሰጣጥ እና የሰው፣ የንብረት፣ የግዢ፣ ፋይናንስና ሀብት አስተዳደር ከማንኛውም ፖለቲካ ፓርቲ ተፅዕኖ ወይም ጣልቃ ገብነት ነፃ እና ሕግን መሠረት ተደርጎ መከናወን እንዳለበት ደንግጓል፡፡
በአዋጁ አንቀጽ 38 መሠረት ቀልጣፋና ተደራሽ የሆነ የመንግሥት አገልግሎት አቅርቦት ሥርዓት መዘርጋት እንደለበት ያስቀምጣል፡፡ ይህንንም ለማሳካት በአዋጁ አንቅጽ 44 መሠረት ማንኛውም የመንግሥት መሥሪያ ቤት ህብረተሰቡ ከመንግሥት መረጃና አገልግሎትን በቀላሉ እንዲያገኝ፣ በውስን የሰው ኃይል ብዙ ተግባራትን ለማከናወን፣ ግልጽነትና ተጠያቂነትን በመፍጠር ሙስናና ብልሹ አሠራርን በማስወገድ ዜጎች በመንግሥት ላይ ያላቸውን እምነት በማጠናከር የአንድ ማዕከል ዲጅታል የመንግሥት አገልግሎት ላይ የተመሠረተ ማድረግ እንዳለበት ይደነግጋል፡፡
ማጠቃለያ
በአጠቃላይ የሥነ ምግባር ደንብ ለአንድ መስሪያ ቤት መሠረት ወይም የማዕዘን ድንጋይ ናቸው ተብለው የሚገመቱትን መሠረታዊ የሥነ-ምግባር መርሆዎችና እሴቶች በግልጽ የሚያሳይ እንዲሁም ሰራተኞችና ኃላፊዎች ስራቸውን ሲያከናውኑ ሊያንጸባርቋቸው የሚገባቸውን ቁልፍ የሆኑ የመልካም ሥነ ምግባር መርሆዎችና እሴቶች ተላብሰው አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ፤ ከመስመርም ሲወጡ ተመጣጣኝ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚችል እንዲገነዘቡ እና በጣም ጠቃሚ የሆነ የመስሪያ ቤቱን የስራ ባህል የሚቀርፅ ወሳኝ የስራ አመራር መሳሪያ ነው፡፡