ሥራ ከግለሰብ ጀምሮ ለሀገራት ህልውና መሠረት ነው፡፡ ለዚህም ሰዎች በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ተሰማርተው እራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ከማገዝ አልፈው ሀገራቸውን ያገለግላሉ፡፡ በሀገራችንም ዜጎች በተለያዩ የሥራ መስኮች በመሰማራት እራሳቸውን እና ቤተሰባቸውን ለማስተዳደር ጥረት የሚያደርጉ ሲሆን ከሚሰማሩባቸው ዘርፎች መካከል በተለያዩ ተቋማት ተቀጥሮ መሥራት አንዱ ነው፡፡ ዜጎች በመንግሥት ወይም በግሉ ዘርፍ ተቋማት ተቀጥረው የሚሰሩ ሲሆን የመንግሥት አስተዳደር ሰራተኞች የሚተዳደሩበት እና በሌሎች ዘርፎች ተቀጥረው የሚሰሩ ሰራተኞች የሚተዳደሩበት የሕግ ማዕቀፍ የተለያየ ነው፡፡ በዚህ አጭር ጽሑፍ ትኩረታችን የአሰሪ እና ሠራተኛ የሕግ ማዕቀፍ ሲሆን የአዋጁን ተፈፃሚነት ወሰን፣ በአሰሪዎች ሥር ተቀጥረው የሚሰሩ ሰራተኞች ከአሰሪዎቻቸው ጋር ስለሚኖራቸው የሥራ ውል ምንነት እና ተያያዝ ጉዳዮችን በዝርዝር እንመለከታልን፡፡
የአሰሪ እና ሠራተኛ አዋጅ ተፈፃሚነት ወሰን
የአሰሪ እና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ተፈፃሚ የሚሆነው በአሠሪና ሠራተኛ መካከል በሚደረግ በቅጥር ላይ በተመሠረተ የሥራ ግንኙነት እና ምልመላ ሂደት ላይ ሲሆን፤
- ለአስተዳደግ ሲባል፣ ለሕክምና ወይም ከሕመም ለመዳን ወይም እንደገና ለመቋቋም ወይም ለየሙያ መልመጃ ትምህርትን ሳይጨምር ለመማር ወይም ለመሠልጠን የተመሰረተ ግንኙነት ሲሆን፣
- ሠራተኛው የሥራ መሪ ሲሆን፣
- የግል አገልግሎት ቅጥር ሲሆን፣
- በልዩ ሕግ የሚተዳደሩ እንደ ጦር ኃይል ባልደረቦች፣ የፖሊስ ኃይል ባልደረቦች፣ የመንግሥት አስተዳደር ሠራተኞች፣ የፍርድ ቤት ዳኞች፣ ዐቃቢያነ ሕግ እና ሌሎችንም በሚመለከት እንዲሁም
- እንደተዋዋይ ወገን ዋጋ እየተከፈለው በራሱ የንግድ ሥራ ወይም በራሱ የሙያ ኃላፊነት የሚሰራ ሥራ የሚያከናውን ሰው ላይ ተፈጻሚ አይሆንም፡፡
የሥራ ውል ምንነት
በአዋጅ ቁጥር 1156/2011 አንቀጽ 4 የሥራ ውል ማለት ማንኛውም ግለሰብ ደመወዝ እየተከፈለው በአሠሪው መሪነት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ለተወሰነ ወይም ላልተወሰነ ጊዜ ወይም የተወሰነ ሥራ ለአሠሪው ለመሥራት ከአሰሪው ጋር መስማማትን እንደሆነ ትርጓሜ ሰጥቶታል፡፡ ይህ የሥራ ውል ተዋዋይ ወገኖች በውሉ መሠረት የሚኖራቸውን መብትና ግዴታ፣ የሥራውን ዓይነትና ቦታ፣ ለሥራ የሚከፈለውን ደመወዝ መጠን፣ የስሌቱን ዘዴ፣ የአከፋፈሉን ሁኔታና ጊዜ እንዲሁም ውሉ ፀንቶ የሚቆይበትን ጊዜ ማካተት አለበት፡፡ በተጨማሪ ውሉ ሞራልን የሚቃረን እና በኅብረት ስምምነት ወይም በሥራ ደንብ ለሠራተኛው ከተሰጡት ጥቅሞች ያነሰ ጥቅም የሚሰጥ መሆን የለበትም፡፡
በአዋጁ አንቀጽ 5 እና ተከታዮቹ መሠረት የሥራ ዉል በጹሁፍ ወይም በቃል ስምምነት ሊደረግ ይችላል፡፡ ውሉ በጽሑፍ የሚደረግ ከሆነ የአሰሪውን ስምና አድራሻ፣ የሠራተኛውን ስም፣ እድሜ እና አድራሻ፣ የውሉን ስምምነት ይዘት እና የተዋዋዮቹን ፊርማ መያዝ ይጠበቅበታል፡፡ ውሉ በቃል የተደረገ ከሆነ ደግሞ ውሉ በተደረገ በ15 ቀናት ጊዜ ውስጥ አሰሪው በጽሑፍ ውል ውስጥ እንዲካተቱ የተጠቀሱትን ሁኔታዎችን የሚያካትት እና አሰሪው የፈረመበት የጽሑፍ መግለጫ ለሠራተኛው የሚሰጠው ሲሆን ሠራተኛው መግለጫው በደረሰው በ15 ቀናት ውስጥ ካልተቃወመ በሁለቱ መካከል የተደረገ ውል ሆኖ ይቆጠራል፡፡ ሆኖም እነዚህ ውልን ወይም የጽሑፍ መግለጫን የተመለከቱ ሁኔታዎች አለመሟላት ሠራተኛው በአዋጁ መሠረት ያሉትን መብቶች የሚያሳጣው አይሆንም፡፡
ከሥራው ውል የሚመነጩ መብት እና ግዴታዎች
አዋጁ በሥራ ውል መሠረት የሚመሠረት የአሰሪ እና ሠራተኛ ግንኙነት በተዋዋዮች ላይ መብትና ግዴታ የሚያስከትል ነው፡፡ በአንቀጽ 12 መሠረት አሰሪ በውሉ መሠረት ለሠራተኛዉ ሥራ የመስጠት፣ በሥራ ውሉ በሌላ ሁኔታ ካልተገለጸ በስተቀር ለሥራው የሚያስፈልገውን መሣሪያና ጥሬ እቃ የማቅረብ፣ ደሞዝና ሌሎች ክፍያዎችን የመክፍል፣ የሠራተኛውን ሰብዓዊ ክብር የመጠበቅ፣ ከሥራው ጋር በተያያዘ የሠራተኛውን ደኅንነትና ጤንነት ለመጠበቅና ከአደጋ ለመከላከል የሚስፈልጉ እርምጃዎችን በተመለከተ አግባብ ባለው ባለሥልጣን የሚሰጡትን ደረጃ እና መመሪያዎች የመከተል፣ የሠራተኛው ጤንነት እንዲመረመር በሕግ ወይም አግባብ ባለው አካል ግዴታ በሚጣልበት ጊዜ ለምርመራው የሚያስፈልገውን ወጪ የመቻል፣ ውል ሲቋረጥ ወይም ሠራተኛው ሲጠይቅ ሠራተኛው ሲሰራ የነበረውን የሥራ አይነት፣ ደሞዝ እና የአገልግሎት ዘመን የሚያሳይ የምስክር ወረቀት ለሠራተኛው ያለክፍያ የመስጠት፣ የስራ ውሉን ደንቦች እና በሕግ የሚተላለፉ መመሪያዎችን እና ትእዛዞችን የማክበር ግዴታ አለበት፡፡ በሌላ በኩል ሠራተኛዉ በሥራ ውሉ ላይ የተመለከተውን ሥራ ራሱ የመሥራት፣ በሥራው ውሉ እና በሥራ ደንብ መሠረት በአሰሪው የሚሰጠውን ትእዛዝ የመፈፀም፣ መሣሪያዎችና ዕቃዎች ሁሉ በጥንቃቄ የመጠበቅ፣ ለሥራ ብቁ ሆኖ መገኘት፣ በሕይወትና በንብረት ላይ አደጋ ሲደርስ ወይም አስጊ ሁኔታ ሲፈጠር እራሱን ችግር ዉስጥ ሳይከት ተገቢውን ዕርዳታ የመስጠት፣ እራሱንና ባልደረቦቹን አደጋ ላይ የሚጥል ወይም የድርጅቱን ጥቅም የሚጎዳ ሁኔታ ሲያጋጥም ወዲያዉኑ ለአሠሪው የማስታወቅ እንዲሁም በሌሎች ድንጋጌዎች፣ በየኅብረት ስምምነት፣ በሥራ ደንብና በሕግ መሠረት የሚተላለፉ ትዕዛዞችን የማክበር ግዴታ እንዳለበት በአንቀጽ 13 በግልፅ ተመልክቷል፡፡
የሥራ ውል ሚቋረጥባቸዉ ምክንያቶች
የሥራ ውል በሕግ፣ በተዋዋዮች ስምምነት፣ በአሰሪ ወይም በሠራተኛው አነሳሽነት ወይም በህብረት ስምምነት ሊቋረጥ ይችላል፡፡
በሕግ መሠረት የሥራ ውል መቋረጥ
ውሉ ለተወሰነ ግዜ ሆኖ የተወሰነው ግዜ ሲያልቅ፣ ሠራተኛው ሲሞት፣ በሕግ አግባብ በጡረታ ሲገለል፣ በመክሰር ወይም በሌላ ምክንያት ድርጅቱ ለዘለቄታው ሲዘጋ፣ ከፊል ወይም ሙሉ ዘላቂ የአካል ጉዳት በመድረሱ ምክንያት ሠራተኛዉ ለመሥራት አለመቻሉ ሲረጋገጥ ውሉ በሕግ ሊቋረጥ ይችላል፡፡
በስምምነት የሥራ ውል መቋረጥ
ተዋዋይ ወገኖች የሥራ ውላቸውን ለማቋረጥ በጽሑፍ ስምምነት ሲያደርጉ የሥራ ውል ይቋረጣል፡፡ ነገር ግን ሠራተኛው በሕግ የተሰጠውን መብቱን ለመተው የሚያደርገው ስምምነት በሕግ ፊት የፀና ውጤት አይኖረውም፡፡
በአሰሪው ወይም በሠራተኛው አነሳሽነት የሥራ ውል መቋረጥ
አሰሪው ወይም ሠራተኛው በማስጠንቀቂያ ወይም ያለማስጠንቀቂያ የሥራ ውል የሚያቋርጡባቸው ህጋዊ ምክንያቶች በህጉ ተመልክተዋል፡፡
ያለማስጠንቀቂያ ውል የሚቋረጥባቸው ሁኔታዎች
በአዋጁ በአንቀጽ 27 መሠረት በኅብረት ስምምነት በሌላ አኳኋን ካልተወሰነ በስተቀር ሠራተኛው የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ እየተሰጠው በስድስት ወር ውስጥ ለስምንት ጊዜ የስራ ሰዓት አለማክበር ወይም ለአምስት ቀናት ከሥራ መቅረት፣ በሥራው ላይ የማታለል ተግባር መፈፀም፣ የአሠሪው ንብረት አለአግባብ መጠቀም፣ እንደጥፋቱ ክብደት በሥራው ቦታ አምባጓሮ ወይም ጠብ አጫሪነት ተጠያቂ መሆን፣ በወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ ምክንያት ለያዘው ሥራ ብቁ ሆኖ አለመገኘት፣ ሆነ ብሎ ወይም በከባድ ቸልተኝነት በአሰሪው ወይም ከድርጅቱ ጋር በቀጥታ ግንኙነት ባላው ማንኛውም ንብረት ላይ ጉዳት ማድረስ፣ በህይወትና ንብረት ላይ አደጋ የሚጥል ድርጊት ሆነ ብሎ ሥራ ቦታ መፈፀም፣ አሰሪው በግልፅ ሳይፈቅድለት ከሥራ ቦታ ንብረት መውሰድ፣ በሀሰተኛ ሰነድ መገልገል ወይም ለመገልገል መሞከር፣ በሥራ ቦታ የተከለከሉ አደንዛዥ እፆችንና የአልኮል መጠጦችን መጠቀም ወይም ተጠቅሞ ለሥራ ብቁ አለመሆን፣ በሥራ ቦታ ወሲባዊ ትንኮሳ መፈፀም፣ በሠራተኛው ላይ ከሰላሳ ቀናት ለሚበልጥ ጊዜ የእሥራት ፍርድ ተወስኖበት ከሥራ መቅረት እንዲሁም ሌሎች በአዋጁ እና በህብረት ስምምነት ያለማስጠንቀቂያ ውሉ ለማቋረጥ ያስችላሉ ተብለው የተጠቀሱ ምክንያቶች በተከሰቱ ጊዜ አሰሪው ያለማስጠንቀቂያ ውል የሚያቋርጥባቸው ሁኔታዎች ናቸው፡፡ በዚህ መሠረት አሰሪው የሥራ ውል በሚያቋርጥበት ጊዜ የሥራ ውሉ የሚያቋረጥበትን ምክንያትና ቀን በመጥቀስ ለሠራተኛው በጹሑፍ መግለፅ አለበት፡፡
በሌላ በኩል አሰሪው ወይም የሥራ መሪው የሠራተኛው ሰብዓዊ ክብርና ሞራል የሚነካ ወይም በወንጀል ህጉ መሠረት የሚያስቀጣ ሌላ አድራጎት ወይም ወሲባዊ ትንኮሳ ወይም ጥቃት ከፈፀመ፣ ለሠራተኛው ደኅንነት ወይም ጤንነት የሚያሰጋና ሊደርስ የተቃረበ አደጋ መኖሩን እያወቀ ወይም አደጋውን ለመከላከል የሚያስፈልጉ እርምዎችን እንዲወስድ ኃላፊነት በተሰጠው ባለሥልጣን በተሰጠው ትእዛዝ በተወሰነ የጊዜ ገደብ ውስጥ እርምጃ ካልወሰደ፣ በህብረት ስምምነት ወይም በስራ ደንብ ወይም አግባብ ባላቸው ሌሎች ህጎች በተወሰነው መሠረት አሰሪው ለሠራተኛው መፈፀም ያለበትን ግዴታዎች በመደጋገም ካልፈፀመ በአዋጁ አንቀጽ 32 መሠረት ሠራተኛው ያለማስጠንቀቂያ የሥራ ውሉን ማቋረጥ ይችላል፡፡ በዚህ መሠረት ሠራተኛው የሥራ ውሉን በሚያቋርጥበት ጊዜ የሥራ ውሉን የሚያቋረጥበትን ምክንያትና ቀን በመጥቀስ ለአሰሪው በጹሑፍ ማሳወቅ አለበት፡፡
በማስጠንቀቂያ የሥራ ውል የማቋረጥባቸው ሁኔታዎች
በአዋጁ በአንቀጽ 28 መሠረት የሠራተኛው የሥራ ችሎታ ማጣት፣ የሥራ ችሎታውን ለማሻሻል አሠሪው ያዘጋጀለትን የሥልጠና ዕድል ባለመቀበሉ ምክንያት ሲሰራ የቆየውን ሥራ ለመቀጠል የሥራ ችሎታ የሌለው ሆኖ መገኘት ወይም ሥልጠና ከተሰጠው በኋላ አስፈላጊውን አዲስ የሥራ ችሎታ ለመቅሰም የማይችል መሆን፣ ሠራተኛው በጤንነት መታወክ ወይም በአካል ጉዳት ምክንያት ለዘለቄታው ሊሰራ የማይችል ሆኖ መገኘት፣ ድርጅቱ ወደ ሌላ ቦታ ሲዛወር ወደ አዲሱ ቦታ ተዛውሮ ለመሥራት ፈቃደኛ አለመሆን፣ ሠራተኛው የያዘው የሥራ መደብ በበቂ ምክንያት መሰረዝና ሠራተኛውን ወደሌላ ሥራ ማዛወር የማይቻል ሆኖ መገኘት፣ ድርጅቱ በሚያመርታቸው ምርቶች ወይም በሚሰጣቸው አገልግሎቶች ተፈላጊነት መቀነስ ምክንያት የድርጅቱ የሥራ እንቅስቃሴ በመቀዝቀዙ ወይም ትርፍ እየቀነሰ በመሄዱ የሥራ ውል ማቋረጥ አስፈላጊ ሆኖ መገኘት፣ የድርጅቱን ምርታማነት ለማሳደግ የአሠራር ዘዴዎችን ለመለወጥ ወይም አዲስ ቴክኖሎጂ ለመጠቀም ሲባል የሥራ ውል መቋረጥ የሚያስከትል መሆን አሰሪው ውሉን በማስጠንቀቂያ ሊያቋርጥ ከሚችልባቸው ምክንያቶች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ይህ በሚሆንበት ጊዜ በአንቀጽ 35 መሠረት ህጉ ያስቀመጠውን የማስጠንቀቂያ ጊዜ ለሠራተኛው አስቀድሞ መስጠት ይጠበቅበታል፡፡
በሌላ በኩል የሙከራ ጊዜውን የጨረሰ ሠራተኛ የሰላሳ ቀናት ማስጠንቀቂያ በመስጠት በማንኛውም ምክንያት ውሉን ማቋረጥ እንደሚችል በአዋጁ አንቀጽ 31 በግልፅ ተደንጓል፡፡
የሥራ ውል የማይቋረጥባቸዉ ምክንያቶች
ሠራተኛው በአሰሪው ላይ ቅሬታ ማቅረቡ፣ አሰሪ ስለተከሰሰ በክሱ ላይ ተካፋይ መሆኑ፣ የሠራተኛ ማህበር አባል መሆኑ፣ ሠራተኛው የሰራተኞች ተጠሪ ሆኖ ለመሥራት መፈለጉ ወይም መስራቱ፣ ድርጅቱ ከሌላው ጋር መቀላቀል የሀብት መከፋፈል ወይም የባለቤትነት መብት ወደ ሌላ መተላለፍ፣ ብሔር፣ ጾታ፣ ሐይማኖት፣ የፖለቲካ አመለካከት፣ የጋብቻ ሁኔታ፣ ዘር፣ ቀለም፣ የቤተሰብ ኃላፊነት፣ የዘር ሐረግ፣ እርግዝና፣ አካል ጉዳተኝነት፣ ወይም ማኅበራዊ አቋም የሥራ ውልን ለማቋረጥ ተገቢ ምክንያቶች ሊሆኑ አይችሉም፡፡
ማጠቃለያ
የሥራ ውል አሰሪ እና ሠራተኛ የሥራ ግንኙነታቸውን የሚመሰርቱበት እንደመሆኑ ውሉ ከሚመሠረትበት ጊዜ ጀምሮ በሥራ ላይ በሚቆይበትም ሆነ በሚቋረጥበት ጊዜ በህጉ የተቀመጡ ድንጋጌዎች ማክበር ሰላማዊ የአሰሪ እና ሠራተኛ ግንኙነት እንዲኖር ያግዛል፡፡
በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ