የቅጅ እና ተዛማጅ መብት ጥበቃ በኢትዮጵያ ህግ

ማውጫ

ይህን ጽሑፍ ያጋሩ

መግቢያ

አዕምሯዊ ንብረት የሰው ልጅ በተፈጥሮ ያለውን እምቅ የፈጠራ አቅም ተጠቅሞ የሚሰራቸው ልዩ ልዩ የሥራ ውጤቶችን የሚመለከት ሲሆን የአዕምሮ ንብረት ጥበቃ ሕግ ስንልም እነዚህ የፈጠራ ሥራዎች እንደማንኛውም ቁሳዊ ሀብት በንብረትነት ተቆጥረው እውቅና የሚያገኙበትና ጥበቃ የሚያገኙበትን የሕግ ሥርዓት ነው፡፡ አዕምሯዊ ንብረት ሰፋ ያለ ይዘት ያለው የሕግ ዘርፍ ሲሆን ከዋና ዋና ክፍሎቹ ውስጥም እንደ ቅጂና ተዛማጂ መብቶች፣ የፈጠራ ባለቤትነት መብት (patent Right)፣ የንግድ ምልክትና የንግድ ሚስጥሮችን የሚመለከቱ የጥበቃ ዘርፎችን ይይዛል፡፡ በዚህ አጭር ጽሑፍ የቅጅና ተዛማጅ መብቶችን ብቻ የሚመለከቱ ጉዳዮች በአጭሩ ተብራርተው የሚቀርቡ ይሆናለ፡፡

የቅጅና ተዛማጅ መብቶች ምንነት

በተለምዶ የቅጂና ተዛማጅ መብቶችን በአንድ ጠቅሎ የመጥራት የተለመደ አገላለፅ ቢሆንም ቃላቱ የየራሳቸው ትርጉም እና ህጋዊ ውጤት አላቸው፡፡ በቅጂ እና ተዛማች መብቶች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 410/1996 በአንቀጽ 2/8/ መሠረት የቅጅ መብት ማለት ከአንድ ሥራ የሚመነጭ የኢኮኖሚ መብት ሲሆን አግባብነት ባለው ጊዜ የሞራል መብቶችን ይጨምራል፡፡ በአዋጅ ቁጥር 410/96 አንቀጽ 7 መሠረት ኢኮኖሚያዊ መብት ሥራውን የማባዛት፣ የመተርጎም፣ የማከፋፈል እና ሌሎች በህጉ የተዘረዘሩትን መብቶች የሚመለከት ነው፡፡ በተመሳሳይ በአዋጁ አንቀጽ 8 ላይ እንደተመለከተው የሞራል መብት የሥራው አመንጪ ሥራው እንዲታወቅለት ወይም ሳይታወቅ እንዲቆይ የማድረግ፣ የብዕር ስም የመጠበቅ፣ ሥራውን የማሳተም፣ ክብሩንና መልካም ስሙን የሚያጎድፍ የሥራ መባዛት፣ መቆራረጥ ወይም በሌላ መልክ መቀየርን የመቃወም እና ሌሎች መሰል መብቶችን የተመለከተ መብት ነው፡፡

በሌላ በኩል በዚሁ አዋጅ በአንቀጽ 2(14) ላይ ተዛማጅ መብት ከዋኝ፣ የድምጽ ሪከርዲንግ ፕሮዲውሰር፣ የብሮድካስቲንግ ድርጅት በሥራው ላይ ያለው መብት ነው፡፡ በአጠቃላይ የቅጅና ተዛማጅ መብትን ስንመለከት ልብ ሊባል የሚገባው ጉዳይ የትኛውም ፈጠራዊ ክህሎት በታከለበት መንገድ የሚቀርብን ሐሳብ የሚመለከት እንደሆነ ነው፡፡

በዚህም መሠረት ይህ የሕግ ዘርፍ በሥነ-ጽሁፍ እና ሥነ ጥበብ ዘርፍ ወጥ የፈጠራ ሥራዎችን ለሚያመነጩ ደራሲያን፣ አርቲስቶች ወዘተ… እንደዚሁም በወጥ የፈጠራ ሥራዎች ላይ ተመስርተው የሚሰሩ ሌሎች የፈጠራ ሥራዎች ላይ የባለቤትነት መብት የሚሰጥ የሕግ ማዕቀፍ ነው፡፡ ለምሳሌ ከዋኞች /ተዋንያን እና ዘፋኞች/፣ ድምጽ ሪከርደርስ /አሳታሚዎች/፣ ካሴትና ኮምፓክት ዲስኮች፣ የብሮድካስት ተቋማ /ሬድዮና ቴሌቪዥኝ/ የመሳሰሉትን ሊይዝ ይችላል፡፡

ለአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ አስፋላጊነት

በአዋጁ መግቢያ ላይ እንደተመላከተው ለህጉ መውጣት እንደዋነኛ መነሻ ተደርጎ የተወሰደው ጉዳይ ኪነ-ጥበባዊና ሳይንሳዊ ፈጠራን ማበረታታት ሲሆን አያይዞም እነዚህ ፈጠራዎች በባህል ግንባታ፣ በማኅበራዊ እሴትና ኢኮኖሚው ዘርፍ ያላቸውን ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች ማሳደግ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ጥበቃ የተደረገላቸው የቅጅና ተዛማጅ የፈጠራ ሥራዎች

በአዋጁ ቁጥር 410/1996 አንቀጽ 2(30) ላይ በሕግ ጥበቃ ያገኙ የፈጠራ ሥራዎች ተዘርዝረው እናገኛለን፡፡ በዚህም መሠረት፡-

  • መፃህፍት፣ ቡክሌቶች፣ በመጽሄት ወይም በጋዜጣ ላይ የሚገኙ መጣጥፎች፣ የኮምፒውተር ፕሮግራሞች
  • ንግግር፣ ሌክቸሮች፣ ለአንድ ለተወሰነ ክፍል የሚደረግ መልዕክት አዘል ንግግር፣ የሀይማኖት ስብከትና ሌላ በቃል የቀረበ ሥራ
  • ድራማ፣ ድራማዊ የሙዚቃ ሥራ፣ በእንቅስቃሴ ብቻ የሚቀርብ ድራማ (ፓንቶማይምንስ)፣ የመድረክ ውዝዋዜ እና ሌላ ለመድረክ ተብሎ የሚሰራ ሥራ
  • የኪነ ህንፃ ሥራዎች
  • የሙዚቃ ሥራ፣ የኦዲዮቪዧል ሥራዎች፣ የስዕል፣ የቅብ፣ የሀውልት፣ የቅርፃ ቅርፅ፣ የህትመት፣ የፊደል ቅርፅ፣ ጥልፍና ሌላ የሥነ-ጥበብ ሥራ
  • የፎቶግራፍ ሥራዎች፣ ስዕላዊ መግለጫ፤ ካርታ፣ ፕላን፣ ንድፍና ባለ ሶስት ገፅታ ከጅኦግራፊ፣ ቶፖግራፊና ኪነ ሕንፃ ወይም ከሳይንስ ጋር የተያያዘ ሥራ እና መሰል ሥራዎችን ያካተተ ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የቅጂ እና ተዛማች መብቶች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 410/1996ን ባሻሻለው አዋጅ ቁጥር 872/2007 መሠረት የዕደ-ጥበብ ሥራዎች ጥበቃ ተደርጎላቸዋል፡፡

የቅጅና ተዛማጅ መብት ባለቤት መብቶች

የቅጅ መብቶች ለባለመብቶቹ ከሚያጎናጽፏቸው ኢኮኖሚ እና ሞራላዊ መብቶች ውስጥ፡-

  • ባለመብቶቹ ሥራዎቻቸውን ለመጠቀም ወይም ሶስተኛ ወገኖች እንዲጠቀሙባቸው የመፍቀድ፣
  • ሥራዎች እንዲባዙ፣ ለሕዝብ እንዲደርሱ፣ እንዲሰራጩ፣ እንዲተረጎሙ ወይም ወደሌላ ሥራ እንዲቀየሩ የመፍቀድ ወይም የመከልከል፣
  • የደራሲነት /የአመንጭነት/ መብት እውቅና እንዲያገኙ ማድረግ፣
  • በብዕር ስም የመጠቀም መብት፣
  • ክብሩና መልካም ስሙን የሚያጎድፍ የሥራ መዛባት እንዳይኖር የመጠበቅ ወይም የሥራው ወደ ሌላ መቀየር የሚያስከትለውን ጉዳት የመቃወም መብት፣
  • ሥራዎቹ ለኢኮኖሚዊ ጥቅም ሲውሉ የአገልግሎት ክፍያ ወይም ሮያሊቴ ከተጠቃሚው የማግኘት መብት በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡

ጥበቃ ለማግኘት የሚያስፈልጉ መስፈርቶች

በአዋጅ ቁጥር 410/1996 አንቀጽ 6(1) ላይ በተደነገገው መሠረት ማንኛውም የፈጠራ ሥራ አመንጪ ለሥራው ጥበቃ ለማግኘት ሥራው ወጥ (ኦርጅናል) መሆን እና ሥራው ግዙፋዊነት ያገኘ መሆን አለበት፡፡

  • ወጥ (ኦርጅናል) መሆን፡- የሥራ አመንጪው የሠራው ሥራ ከሌሎች ሥራዎች ላይ ያልተቀዳ መሆን እንዳለበት የሚገልፅ ሀሳብ ነው፡፡ ይህም ማለት ሥራው የሥራው አመንጪ ሰው የአእምሮ ውጤት መሆን አለበት የሚለውን እሳቤ ያያዘ ነው፡፡
  • ግዙፋዊነት (Fixed):- አንድ ሥነ-ጽሑፍ፣ የኪነ-ጥበብ ወይም በሳይንሳዊ ሥራ የሥራ አመንጪው የአእምሮው ውጤት የሆነ ወጥነት ያለው ሆኖ ጉዙፍ በሆነ ነገር ላይ መስፈር አለበት፡፡ ይህም ማለት የአእምሮ ውጤት የሆነው ሥራው በሃሳብ ደረጃ የቀረ ሳይሆን አንድ ግዙፍ በሆነ እቃ ላይ የሰፈረ መሆን አለበት፡፡ ለምሳሌ ያክል አንድ የመጸሐፍ ደራሲ የጽሑፉን ሀሳብ በአእምሮ ስለያዘ የቅጅ መብቱ አይጠበቅለትም፡፡ ይልቁንም ይህን የአእምሮ ውጤቱ የሆነውን ድርሰት በወረቀት ላይ ሲያሰፍረው ነው ጥበቃ የሚያገኘው፡፡ በአዋጅ ቁጥር 410/1996 በአንቀጽ 2(11) ላይ መቅረፅ ወይም ግዝፈት እንዲያገኝ ማድረግ ማለት አንድ ሥራ፣ ምስል፣ ድምፅ ወይም የአንደኛቸው አምሳያ ምትክ ለዚሁ ተብሎ በተዘጋጀ መሳያ አማካኝት እንዲታይ፣ እንዲባዛ፣ ወይም እንዲሰራጭ ማድረግ ማለት እንደሆነ ይገልፃል፡፡

መብቶች ፀንተው የሚቆዩበት ጊዜ

ከቅጅና ተዛማጅ መብቶች የሚገኙ የኢኮኖሚያዊ መብቶች የቆይታ ጊዚያቸውን በተመለከተ በሕጉ የተቀመጠ የጊዜ ገደብ አለው፡፡ ይህም በአዋጁ እና በማሻሻያው አዋጅ ቁጥር 872/2007 አንቀጽ 20 ላይ እንደተገለፀው የኢኮኖሚያዊ መብቶች የሥራ አመንጪው በህይወት በሚቆይበት ዘመንና ከሞተ በኋላ ለወራሾቹ እስከ 50 (ሃምሳ) ዓመት ፀንቶ እንደሚቆዩ ተገልፆል፡፡ ሥራው የፎቶግራፍ ሥራ ከሆነ ጥበቃው የሚቆየው ፎቶግራፉ ከተሰራ እስከ 25 ዓመት መሆኑን አንቀጽ 20(7) ላይ ተደንግጎ ይገኛል፡፡

በተመሳሳይ መልኩ የሞራል መብቶችም የሥራ አመንጪው በህይወት እስካለ ድረስ እና ከሞተ በኃላ የኢኮኖሚያዊ መብቶቹ ፀንተው ለሚቆዩበት ጊዜ ጥበቃ እንደሚደረግላቸው በአዋጁ አንቀጽ 8(4) ተገልፆል፡፡ ይህ ማለትም ከላይ በተገለፀው መሠረት የሞራል መብቶች የሥራው አመንጪ ከሞተ በኋላ ለወራሾቹ የሚተላለፉ እና እስከ 50 ዓመት በሕግ ጥበቃ አላቸው ማለት ነው፡፡

የቅጅና ተዛማጅ መብቶች መጣስ ስለሚያስከትለው የሕግ ተጠያቂነት

ቅጅ እና ተዛማጅ መብቶች ጥሰት አስተዳደራዊ፣ የፍትሐብሔር እና የወንጀል ተጠያቂነትን ያስከትላል፡፡ ከወንጀል ተጠያቂነት አንጻር በአዋጅ ቁጥር 410/96 አንቀጽ 36 (በአዋጅ ቁጥር 872/2007 አንቀጽ 43 እንደተሻሻለው) ላይ እንደተደነገገው በወንጀል ህጉ የበለጠ የሚያስቀጣ ቅጣት ካልተደነገገ በቀር ማንም ሰው በአዋጁ ጥበቃ የተደረገላቸውን መብቶች ሆን ብሎ የጣሰ እንደሆነ ከ5 (አምስት) ዓመት የማያንስ እና ከ10 (አስር) ዓመት የማይበልጥ ፅኑ እስራት እና ከብር 25,000 (ሀያ አምስት ሺ) በማያንስ እና 50,000 (ሀምሳ ሺ) በማይበልጥ በገንዘብ መቀጮ ይቀጣል፡፡ ይኼው ወንጀል በከባድ ቸልተኝነት የተፈፀመ ከሆነ ከ1 (አንድ) ዓመት በማያንስ እና ከ5 (አምስት) ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራት እና ከብር 5,000 (አምስት ሺ) በማያንስና ከብር 25,000 (ሀያ አምስትሺ) በማይበልጥ መቀጮ የሚቀጣ ይሆናል፡፡ ይህ ቅጣት ወንጀሉ የፈፀመበትን ንብረት ማገድ፣ መያዝ፣ መውረስ እና ማስወገድንም ያካተተ ነው፡፡

የፍትሐብሔር ተጠያቂነቱን በተመለከተ በአዋጅ ቁጥር 410/96 አንቀጽ 34 በአዋጅ ቁጥር 872/2007 እንደተሻሻለው አንቀጽ 41 ላይ እንደተደነገገው ንብረቱ መብት መጣሱ ድርጊት እንዲቆም፣ እንዳይባዛ፣ እንዳይሰራጭ፣ ወዘተ… ጊዜአዊ እግድ ከመስጠት በተጨማሪ ጥፋት ያደረሰው ሰው ላይ በማስረጃ ሲረጋገጥ ባደረሰው ጉዳት እና ባገኘው ትርፍ ግምት ኢኮኖሚያዊ ካሳ እና የደረሰውን ጉዳት መሠረት በማድረግ በሚወሰን ነገር ግን ከብር 100,000 (አንድ መቶ ሺ) የማያንስ የሞራል ካሳ የሚወሰን መሆኑ በህጉ ላይ ተመልክቶ ይገኛል፡፡

የዳኝነት ሥልጣን በተመለከተ በማሻሻያ አዋጅ ቁጥር 872/2007 አንቀጽ 44 ላይ እንደተመለከተው ከውል ውጪ ኃላፊነትን ከሚመለከቱ ጉዳዮች በስተቀር ማንኛውንም በቅጂና ተዛማጅ መብቶች ጥሰትን በተመለከተ የሚነሱ የፍትሐብሔር ክርክሮችን የሚዳኘው በአእምሮአዊ ጽህፈት ቤቱ የተደረጃው የአእምሮአዊ ንብረት አስተዳደራዊ ችሎት ነው፡፡ የወንጅል ጉዳዮች ግን በመደበኛው ፍርድ ቤት የሚቀርቡ ናቸው፡፡

ማጠቃለያ

በጥቅሉ የሥነ ጽሑፍ፣ ዕደ-ጥበብ፣ የኪነ ጥበብ፣ ሳይንሳዊ ፈጠራዎች እና ተመሳሳይ የፈጠራ ሥራዎችን የቅጅና ተዛማጅ መብቶች በሕግ እውቅና መስጠትና ጥበቃ ማድረግ አዳዲስ ፈጠራዎች እንዲበራከቱ፣ የሚጠበቅባቸውን በህላዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ሳይንሳዊና ቴክኖሎጂያዊ እድገት በህብረተሰቡ ውስጥ እንዲያመጡ፣ የፈጠራው ባለቤቶች ከሥራቸው እንዲጠቀሙ እንዲሁም ሌሎች ሰዎችም ለፈጠራ ሥራ እነዲበረታቱ በማድረግ ኢንቨስትመትን በማሳደረግ ረገድ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል፡፡ በመሆኑም ማንኛውም ሰው ለሥራዎቹ አመንጪዎች የተሰጠውን የሕግ ጥበቃ በማክበር እና የመብት ጥሰቶች ከማድረግ በመታቀብ የመብት ጥሰቶችን መፈፀም ከሚያስከትሉት የሕግ ተጠያቂነት እራሱን ሊጠብቅ ይገባል፡፡

በንቃተ ሕግ ተምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ