ጋብቻ ሳይፈፀም እንደ ባልና ሚስት አብሮ መኖር በተሻሻለው የፌዴራል የቤተሰብ ህግ

ማውጫ

ይህን ጽሑፍ ያጋሩ

መግቢያ

የተሻሻለው የፌደራል የቤተሰብ ሕግ አዋጅ 213/1992 ቤተሰብ በሁለት አይነት መንገዶች ሊመሠረት እንደሚችል ያመላከተ ሲሆን እነዚህም በጋብቻ እና ጋብቻ ሳይፈፅሙ እንደ ባልና ሚስት አብሮ መኖር ናቸው። ጋብቻ ሳይፈፅሙ እንደ ባልና ሚስት አብሮ መኖር ከጋብቻ በተጨማሪ ህጋዊ እውቅና የተሰጠው ማህበረሰቡ ውስጥ ያለውን ነባራዊ ግንኙነት ማለትም ብዙ ሰዎች ህጋዊ ጋብቻ ሳይፈፅሙ ቤተሰብ እና ንብረት አፍርተው ስለሚኖሩ በዚህ ጥምረት አማካኝነት የሚፈጠርን የንብረት ውህደት እና የልጆች ሁኔታ ጥበቃ ማግኘት ያለበት በመሆኑ ነው። በተለይ የሴቶች እና ሕፃናትን መብት ከማስከበር አንፃር ከፍተኛ ጠቀሜታ ስለሚኖረው ነው። በዚህ ጽሑፍም ጋብቻ ሳይፈፅሙ እንደ ባልና ሚስት አብሮ ስለመኖር በተሻሻለው የፌደራል የቤተሰብ ሕግ የተካተቱ መሠረታዊ ጉዳዮችን፣ በግላዊ እና በንብረት ግንኙነት ዙሪያ የሚኖረውን የሕግ ውጤት ከጋብቻ ጋር በማነፃፀር በአጭሩ እንመለከታለን።

ጋብቻ ሳይፈፅሙ እንደ ባልና ሚስት አብሮ የመኖር ምንነት

የፌደራሉ የቤተሰብ ሕግ በአንቀጽ 98 መሠረት ጋብቻ ሳይፈፅሙ እንደ ባልና ሚስት አብሮ መኖር ማለት አንድ ወንድና ሴት “በሕግ በሚፀና አኳኋን” ጋብቻ ሳይፈፅሙ በትዳር መልክ አብረው የሚኖሩ ሲሆን ነው በማለት ትርጉም ሰጥቶታል። እዚህ ላይ የሚነሳው ጥያቄ “በሕግ የሚፀና አኳኋን” ሲባል ምን ለማለት ነው? የሚለው ነው። በዚህም በመጀመሪያ ደረጃ በህጉ አንቀጽ 2-4 ድረስ ከተመለከቱት ማለትም በክብር መዝገብ ሹም ፊት፣ በሀይማኖት ወይም በባህላዊ የጋብቻ ሥርዓት ከሚሉት በአንዱ የታወቀ የጋብቻ ሥርዓት አለመፈፀሙን የሚጠቁም ሲሆን ነገር ግን ወንድየውና ሴትየዋ የሚያሳዩት ሁኔታ በሕግ እንደተጋቡ ሰዎች ዓይነት መሆኑ አስፈላጊ ነው። ይህም ሲባል ምንም እንኳ በሕግ አግባብ የተጋቡ ባይሆኑም የተጋቡ ሰዎችን ሁኔታ ሲያሳዩና ቤተ ዘመዶቻቸውና ማኅበረሰቡ እንደተጋቡ ሰዎች የሚኖሩ ናቸው ብለው ሲገምቷቸው እንደሆነ ነው። በአካባቢያቸው እንደባልና ሚስት መስተዋሉ በቂ ማስረጃ ሲሆን የዚህን ሁኔታ መኖር አንደኛው ወገን ለማስረዳት የቻለ እንደሆነ ፍርድ ቤቱ የሕግ ግምት ሊወስድ ይችላል። ሆኖም ግን ማናቸውንም ዓይነት አስተማማኝ ማስረጃ በማቅረብ ይህ ግንኙነት አለመኖሩን በማስረዳት የሕግ ግምቱን ማፍረስም ይቻላል። ስለሆነም ጋብቻ ሳይፈፅሙ እንደ ባልና ሚስት አብሮ የመኖር ግንኙነት የፈጠሩ ሰዎች በጋብቻ ሥርዓት የትዳር ግንኙነት እንደመሰረቱ ሰዎች የሕግ ሰውነት የተሰጠው አካል ፊት ወይም በተፈጥሮ ሰው ፊት ግንኙነት መመስረታቸውን ቀርበው ማስረዳትም ሆነ ማስመስከር ወይም የተለየ ሥርዓት መፈፀም አይጠበቀባቸውም።

ጋብቻ ሳይፈፅሙ እንደ ባልና ሚስት አብሮ የመኖር ግንኙነት ህጋዊ ውጤት

እንደባልና ሚስት አብሮ መኖር ከጋብቻ የሚለየው አንዱ ጉዳይ ለጋብቻ አፈፃፀም የተቀመጡ ልዩ ልዩ ሥርዓቶችን መፈፀምን ሳይጠብቅ በግለሰቦች ስምምነት ብቻ ያለተጨማሪ ሥነ-ሥርዓትና ማረጋገጫ የሚመሠረት የቤተሰብ ግንኙነት መሆኑ ነው። ይህም በቤተሰብ ህጉ በአንቀጽ 98፣ 99(1)ና (2) እና 106/(1-3) ውስጥ በስፋት ተደንግጓል። ይሁንና ይህ ግንኙነት ልክ እንደጋብቻ ሁሉ በሕግ ጥበቃ የሚደረግለት እንደመሆኑ የራሱ ህጋዊ ውጤት ያለው ነው። እነዚህ ህጋዊ ውጤቶችም እንደሚከተለው ተብራርተዋል።

ንብረትን በተመለከተ ጋብቻ ሳይኖር እንደባልና ሚስት አብሮ መኖር የሚኖረው ውጤት

ጋብቻን አስመልክቶ እንደመርህ ተጋቢዎች የግል ግንኙነታቸውንና ንብረታቸውን በሚመለከት ‹‹የጋብቻ ውል›› ሊዋዋሉ ሲችሉ ይህ ባልሆነ ጊዜ ግን በጋብቻ ውስጥ የተፈራ ንብረት የጋራ ሆኖ እንደሚቆጠር በአንቀጽ 62 ተመላክቷል። ምንም እንኳን በመካከላቸው የተፈፀመ ጋብቻ ባለመኖሩ ‹‹የጋብቻ ውል›› የሚል ስያሜ ሊሰጠው ባይችልም እንደ ባልና ሚስት የመኖር ግንኙነት የፈጠሩ ሰዎችም ንብረታቸውን በሚመለከት የውል ስምምነት ሊያደርጉ የሚችሉ መሆኑ በአንቀጽ 102(1) መሠረት ሰፍሮ ይገኛል።

ይህ የንብረት አስተዳደር ውል ያልተደረገ እንደሆነ ወይንም ውሉ ዋጋ በማይኖረው ጊዜ ጋብቻ ሳይኖር እንደባልና ሚስት አብረው የሚኖሩ ሰዎች ለሶስት አመታት ላላነሰ ጊዜ አብረው የኖሩ እንደሆነ በግንኙነት ውስጥ እያሉ ያፈሩት ንብረት የጋራ ሀብት እንደሆነ ግምት ይወሰዳል። ይህ ብቻም ሳይሆን በተቃራኒ ማስረጃ እስካልተረጋገጠ ድረስ አብረው በመኖር ላይ እያሉ የሚኖሯቸው ንብረቶች በግንኙነት ውስጥ የተፈሩ እንደሆኑ ግምት እንደሚወሰድ የህጉ አንቀጽ 102(2) ያስረዳል።

በቤተሰብ ህጉ አንቀጽ 72 መሠረት የተጋቡ ሰዎች የትዳር ወጪዎችን በጋራ የመሸፈን ግዴታ እንዳለባቸው ሁሉ በአንቀጽ 101 በተመሳሳይ እንደ ባልና ሚስት በትዳር መልክ የሚኖሩ ሰዎች የጋራ ወጪያቸውን እያንዳንዳቸው አቅማቸውና ችሎታቸው በፈቀደ መጠን አስተዋፅኦ ማድረግ የሚጠበቅባቸው መሆኑን ተመላክቷል።

በጋብቻ ውስጥ የተፈራው የባልና ሚስት የጋራ ንብረት የሚተዳደርበት፣ የሶስተኛ ወገን እዳ የሚከፈልበት እና ንብረት የሚጣራበት እንዲሁም ጋብቻው ሲፈርስ የጋራ ንብረት ክፍፍል የሚከናወንበት ሁኔታ እንደ ባልና ሚስት የመኖር ትስስር ውስጥ ለተፈራው የጋራ ንብረት አንድ አይነት ውጤት ወይም ተፈፃሚነት ያለው መሆኑ በቤተሰብ ህጉ አንቀጽ 103 ተቀምጧል። ለምሳሌ ለጋራ ኑሯቸው ወይም ለልጆች አስተዳደግ ዓላማ የተገባ እዳ የጋራ እዳ ሆኖ ሁለቱም በአንድነትና በነጠላ ተጠያቂ የሚሆኑ ይሆናል ማለት ነው።

ግላዊና የእርስ-በእርስ ግንኙነትን በተመለከተ የሚኖረው ውጤት

የጋብቻ ግንኙነት በተጋቢዎቹ ወይም በባልና ሚስቱ የግላዊ ግንኙነት ላይ የሚኖረው ውጤት በቤተሰብ ህጉ ከአንቀጽ 49-56 ስር ተመላክቷል። በዚህም ተጋቢዎቹ እርስ በእርስ የመከባበር፣ መተጋገዝና መደጋገፍ፣ የቤተሰብ የጋራ አመራር፣ አብሮ የመኖር፣ የመኖሪያ ስፍራ ስለመወሰን እና የመተማመን ግዴታ እንዳለባቸው በግልፅ ተመላክቷል። ይሁን እንጂ ይህ አይነቱ አስገዳጅ ግላዊ ግንኙነት ውጤት እንደ ባልና ሚስት ለመኖር በሚመሠረት ግንኙነት ውስጥ በግልፅ በህጉ አልተቀመጠም። ከዚህ ሌላ በግንኙነቱ ውስጥ ልጆች ተወልደው እንደሆነ የወላጅነት ማረጋገጥ ሂደቱ ጋብቻን አስመልክቶ በተቀመጡት ድንጋጌዎች (123-179) አግባብ ይሆናል።

በዝምድና ላይ ስለሚኖር ውጤት

በቤተሰብ ህጉ አንቀጽ 9 መሠረት ‹‹ጋብቻ›› በተጋቢዎች ዘመዶች መካከል የጋብቻ ዝምድና የመፍጠር ውጤት ያለው ሲሆን እንደ ባልና ሚስት መኖር ግን የጋብቻ ዝምድና የሚያስከትል ውጤት የሌለው መሆኑ በአንቀጽ 100(1) ስር ተደንግጓል።

ምንም እንኳን ጋብቻ ሳይፈፅሙ እንደ ባልና ሚስት መኖር የጋብቻ ዝምድና የማያስከትል ቢሆንም በቤተሰብ ህጉ ጋብቻ እንዳይፈፀም በአንቀጽ 9 መሠረት ክልከላ የተደረገበት የጋብቻ ዝምድና ውጤት እንደ ባልና ሚስት አብሮ በመኖር ግንኙነትም የሚሰራ መሆኑን በአንቀጽ 100(2) ሥር ተደንግጓል። እንደምሳሌም ወንድየው ከሴቲቱ ወደ ላይም ሆነ ወደ ታች ከሚቆጠሩ ቀጥተኛ ዘመዶች ጋር እንዲሁም ወደ ጎን ከሚቆጠሩ የሴቲቱ እህቶች ጋር ጋብቻ መፈፀምም ሆነ እንደባልና ሚስት አብሮ የመኖር ግንኙነት መመስረት አይችልም፡፡ በዚህም ሁለቱ ግንኙነቶች ተፈጥሮአዊ የቤተሰብና የህብረተሰብ መገኛ ምንጮች መሆናቸውን የማስጠበቅ እውቅና እና ውጤት ያላቸው መሆኑ እንደሚያስገነዝብ መረዳት ይቻላል።

እንደ ባልና ሚስት የመኖር ትስስር በአንቀጽ 100(1) መሠረት የጋበቻ ዝምድና የማያስከትል በመሆኑ በቤተሰብ ህጉ አንቀጽ 198(1) መሠረት ቀለብ የመቁረጥ ግዴታ የማያስከትል ሲሆን በተቃራኒው ጋብቻ በቤተሰብ ህጉ አንቀጽ 9 መሠረት የጋብቻ ዝምድና የሚያስከትል በመሆኑ ቀለብ የመቁረጥ ግዴታን ያስከትላል።

ጋብቻ ሳይፈፀም የሚደረጉ ሌሎች ግንኙነቶች

ከጋብቻ ሥርዓት ወይም ጋብቻ ሳይፈፅሙ እንደባልና ሚስት አብሮ ከመኖር ውጪ በአንድ ወንድና በአንዲት ሴት መካከል የሚደረጉ ሌሎች ግንኙነቶች በሕግ ፊት ምንም ውጤት እንደማይኖራቸው የቤተሰብ ህጉ አንቀጽ 107(1) ይደነግጋል፡፡ አንድ ወንድና አንዲት ሴት በታወቀና በተደጋገመ ሁኔታ የሩካቤ ሥጋ ግንኙነት መፈፀማቸው ብቻ በሁለቱ መካከል ጋብቻ ሳይፈፀም እንደባልና ሚስት የመኖር ግንኙነት አላቸው ለማለት በቂ ምክንያት እንዳልሆነ የቤተሰብ ህጉ አንቀጽ 99(3) ይደነግጋል፡፡ ይህ ማለት ለምሳሌ አንድ ወንድ እና እንዲት ሴት ሰው በሚያውቀው ሁኔታ በጓደኝነት አብረው መሆናቸው ምንም አይነት የሕግ እውቅና የለውም ማለት ነው፡፡ ይልቁንም የቤተሰብ ህጉ ሽፋን ስር ለመውደቅ ጋብቻ ሳይፈፅሙ አብረው የሚሆኑ ሰዎች በሚኖሩበት ማኅበረሰብ ውስጥ ልክ እንደተጋቡ ሰዎች የትዳር ሁኔታ ማሳየት እንዳለባቸው እና ከተራ ግንኙነት በዘለለ ከፍ ያለ ኃላፊነትና ግዴታ የሚጠበቅበት ግንኙነት መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡

የግንኙነቱ መቋረጥ

በቤተሰብ ህጉ መሠረት ጋብቻ ሊፈርስ የሚችልባቸው ሶስት መንገዶች ከተጋቢዎቹ የአንደኛው ሞት፣ የአስገዳጅ ቅድመ ሁኔታዎች አለመሟላት እና ፍቺ እንደሆነ በአንቀጽ 75 ላይ ተመላክቷል። በአንፃሩ ጋብቻ ሳይኖር እንደባልና ሚስት የሚኖሩ ሰዎች በማንኛውም ጊዜ ግንኙነታቸው እንዲቋረጥ ሊወስኑ እንደሚችሉ ነገር ግን የንብረት ክፍፍልን በተመለከተ ጋብቻን የሚመለከቱት ድንጋጌዎች ተፈፃሚ እንደሚሆኑ በአንቀጽ 105 ተደንግጎ ይገኛል። እንዲሁም ግንኙነቱ እንዲቋረጥ ያደረገው ወገን ጥፋት አጥፍቶ እንደሆነ በተመሳሳይ ካሳ እንዲከፍል ሊደረግ ይችላል።

ማጠቃለያ

በአጠቃላይ ጋብቻ እና ጋብቻ ሳይፈፀም እንደ ባልና ሚስት አብሮ መኖር በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ እንደ ቤተሰብ መመስረቻ መንገዶች እውቅና ተሰጥቷቸው ይገኛሉ፡፡ በተጣማሪዎቹ የንብረት እና የግላዊ ግንኙነት ላይ የሚኖራቸው ውጤትም በህጉ ሽፋን ያገኘ ሲሆን በሕግ ደረጃ የሚመሳሰሉባቸዉ እና የሚለያዩባቸው ነጥቦች እንዳሉ ከቤተሰብ ህጉ ድንጋጌዎች መገንዘብ ይቻላል።

በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ