ሰዎች በማኅበራዊ መስተጋብር እርስ በርሳቸው በሚኖራቸው ግንኙነት ህጋዊ ተግባራትን ለመፈፀም፣ መብታቸውን ለማስከበር፣ ግዴታቸውን ለመወጣት እንዲሁም ህጋዊ ኃላፊነት ወይም ተጠያቂነትን ለመውሰድ ችሎታ ሊኖራቸው ይገባል።
በ1960 እ.ኢ.አ በወጣው የኢትዮጵያ ፍሐሀብሔር ሕግ እንደተደነገገው ማንኛውም ሰው ችሎታ የሌለው መሆኑ በሕግ ተወስኖ ካልተገለፀ በቀር ማንኛውንም ዓይነት የማኅበራዊ ኑሮውን ተግባር ለመፈፀም ችሎታ አለው። ይህም የሚያሳየው ሕግ የሚወስደው ግምት ማንኛውም ሰው በመርህ ደረጃ ችሎታ እንዳለው ነው። በዚህ አጭር የንቃተ-ሕግ ጽሑፍ የሰዎች ችሎታ ምንነት፣ የችሎታ ጠቀሜታ ወይም አስፈላጊነት እንዲሁም የሰዎች ችሎታ የማይኖርባቸውን ሁኔታዎች ከፍሐሀብሔር ህጉ አንፃር እንዳስሳለን።
የሰዎች ችሎታ ምንነት
የሕግ መዝገበ ቃላት በሆነው መሪያም ዌብስተር እንደተሰጠው ትርጉም ህጋዊ ችሎታ ማለት አንድ ሰው በሕግ መሠረት አንድን የተወሰነ ሁኔታ ወይም ግንኙነት ከሌላው ጋር የማድረግ ወይም በአንድ የተወሰነ ሥራ ወይም ግብይት ላይ የመሳተፍ ችሎታ እና ኃይል ነው። በተጨማሪም ችሎታ ውሳኔ ለማድረግ መረጃን የመጠቀም እና የመረዳት ችሎታ እና ማንኛውንም ውሳኔ ማስተላለፍ አቅም ማለት ነው። አንድ ሰው አእምሮው ከተዳከመ ወይም በሆነ መንገድ ጤናው ከተጓደለ አቅም ይጎድለዋል። ይህም ማለት በዚያን ጊዜ ውሳኔ ማድረግ አይችልም ማለት ነው። የሕግ ችሎታ በሕጉ መሠረት በእኩልነት የመስተናገድ መሠረታዊ የሰብዓዊ መብት አካል ነው። በመሆኑም ችሎታ ያለው ሰው በፍትሐብሔር ሥነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 33(1) መሠረት ፍትሐብሔር ክስ ማቅረብ የሚችል ሲሆን የፈፀመው የወንጀል ድርጊትም ካለ የወንጀል ህጉ መሠረት ኃላፊነት ይሆናል ማለት ነው።
የችሎታ ጠቀሜታ ወይም አስፈላጊነት
ችሎታ ህጋዊ ግንኙነቶችን በራስ ለማከናወን ጠቀሜታ አለው። ለአብነት ያክል አንድ ሰው ውል በራሱ ለመዋዋል ለምሳሌ ሽያጭ ለመፈፀም ችሎታ ሊኖረው ይገባል። ይኸውም እድሜው በሕግ በተወሰነው ልክ መሆን ያለበት እንዲሁም የአይምሮው የጤንነት ሁኔታ ጤነኛ መሆን ይኖርበታል። ያለበለዚያ ግን ህጉ በሚያስቀምጠው ሥርዓት ወይም በወኪል በኩል ህጋዊ ግንኙነቶችን ለመፈፀም ይገደዳል። እንዲሁም በወንጀል ጉዳይ የወንጀል ሕግን መሠረት በማድረግ ተጠያቂነትን ወይም ተከሳሽነትን ለመወሰን ወይም ሀላፊ እና ኢ-ሀላፊን ለመለየት የአንድ ሰው ችሎታ መኖር ወይም አለመኖር ማወቅ አስፈላጊ ነው።
ሰዎች ችሎታ የሚያጡበት ሁኔታ
በፍትሐብሄር ሕግ ቁጥር 193 ስር እንደተደነገገው ጠቅላላ የችሎታ ማጣት ሁኔታ የሚያስከትሉ ምክንያቶች ዕድሜ ወይም የሰው አእምሮ ሁኔታ ወይም በተሰጠ የፍርድ ቅጣት ናቸው። በተጨማሪም የፍትሐብሔር ህጉ የተለየ የችሎታ ማጣት ሁኔታን የያዘ ሲሆን ይኸውም የተለየ ችሎታ ማጣትን ለመወሰን በግምት ውስጥ ለማስገባት የሚቻለው የሰውዬውን ዜግነት በመመልከት ወይም የሚያከናውነውን ሥራ መሠረት አድርጎ በመያዝ ነው። የችሎታ ማጣት አስረጂን በተመለከተ ሰው ሁሉ ችሎታ እንዳለው የሚገመት ሲሆን ይህ ሰው ችሎታ የሌለው ነው ብሎ ማስረዳት የሚገባው ሰውዬው ችሎታ የለውም ብሎ የሚከራከር ወገን ነው (የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 196)። ከተፈጥሮ ሰዎች በተጨማሪ የሰውነት መብት የተሰጣቸው ድርጅቶችና ለልዩ አገልግሎት የተመደቡ ንብረቶች ችሎታ ያላቸው መሆኑ የሚረጋገጠው እንደ አይነታቸው ለነዚሁ የሰውነት መብት በሚሰጧቸው ድንጋጌዎች መሠረት ነው። ችሎታ የሚያሳጡ ሁኔታዎችን እንደሚከተለው በዝርዝር እንመለከታለን።
በእድሜ ምክንያት ችሎታ ማጣት (Minors)
በእድሜያቸው ምክንያት ችሎታ የሌላቸው ሰዎች ወይም አካለመጠን ስላልደረሱ ሰዎች ሁኔታ በፍትሐብሔር ህጉ የተደነገጉት ድንጋጌዎች የተሻሻለው የፌደራል የቤተሰብ ሕግ ተፈፃሚ በሚሆንባቸው መስተዳድሮች ተፈፃሚ እንደማይሆን በቤተሰብ ህጉ አንቀጽ 319 ስር ተደንግጎ ይገኛል። በመሆኑም በቤተሰብ ህጉ አንቀጽ 215 ስር እንደተደነገገው በእድሜያቸው ምክንያት ችሎታ ያጡ ሰዎች ወይም አካለመጠን ያልደረሰ ሰውን በተመለከተ ትርጉም የሰጠ ሲሆን በትርጉሙ መሠረት አካለመጠን ያልደረሰ ሰው ማለት ጾታ ሳይለይ እድሜው አሥራ ስምንት ዓመት ያልሞላው ልጅ ነው። በእድሜው ምክንያት ችሎታ ያጣ አካለመጠን ያልደረሰ ሰው ህጋዊ ግንኙነቶቸን በራሱ ማከናወን ህጉ ስለማይፈቅድለት ስለመልካም አስተዳደጉና ደህንነቱ ጉዳይ በአሳዳሪው የሚጠበቅ ሲሆን ንብረት ነክ ጥቅሞቹንና በአጠቃላይ የንብረቱን አስተዳደር በሚመለከት በሞግዚት ይወከላል (የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 216)። ስለአሳዳሪ እና ሞግዚት አስተዳደር በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ ከአንቀጽ 215 እስከ 318 በዝርዝር ተደንግጎ ይገኛል።
በአእምሮ ሁኔታ ችሎታ ማጣት
አዕምሮዋቸው ስለ ጎደለ ሰዎች፡- የፍትሐብሔር ህጉ ትርጉም የሰጠ ሲሆን አዕምሮው ጎደሎ ነው የሚባለው በተፈጥሮ ዕውቀቱ ያልተስተካከለ በመሆኑ ወይም በአእምሮ መናወጥ ወይም በእርጅና ምክንያት የሚሰራውን ሥራ የሚያደረሰውን ለማወቅ የማይችል ነው። የአእይምሮ ደካሞች ሰካራም ወይም በመጠጥ አፍዛዥ በሆኑ ነገሮች ልማድ የተመረዙና ገንዘብ ያለ አግባብ የሚያባክኑ ሰዎች አእምሮዋቸው እንደጎደለ ሰዎች ይቆጠራሉ (የፍ/ሕ/ቁ. 339)።
በግልፅ ስለታወቀ የአእምሮ ጉድለት ያለበት ሰው፡- የአእምሮ ጉድለት ያለበት ዕብደቱ በግልፅ እንደ ታወቀ ሰው ሆኖ በሕግ የሚቆጠረው ይህ የተባለው ሰው በሆስፒታል ውስጥ ወይም በአንድ የአእምሮ ጉድለት ያለባቸው ሰዎች መኖሪያ ቦታ ውስጥ በአእምሮው ሁኔታ ምክንያት በአንድ የጤና ጥበቃ ቤት ውስጥ ተዘግቶበት በዚህ በተዘጋበት ቦታ እስከሚቆይበት ጊዜ ነው (የፍ/ሕ/ቁ. 341)። በግልፅ የታወቀ እብድ የሚሰራቸውን ሥራዎች በተመለከት እብደቱ ግልፅ በሆነበት ጊዜና ቦታ ላይ የሠራቸውን ሥራዎች እርሱ ወይም ወኪሎቹ ወይም ወራሾቹ ሊቃወሟቸው ይችላሉ (የፍ/ሕ/ቁ. 343)። ተቃራኒ የሚሆን አስረጂ ከሌለ በቀር የነዚህ ሰዎች ሥራና ፈቃድ የውለታን ፈራሽነት የሚያስከትል ጉድለት ያለበት ነው ተብሎ ይገመታል። እንዲሁም በስህተት መገኘት ምክንያት የሥራዎችና የውሎች መፍረስ የሚመለከቱት የፍትሐብሔር ሕግ ደንቦች በተመሳሳይ ተፈፃሚዎች ይሆናሉ (የፍ/ሕ/ቁ. 344)። ይሁንና የአእምሮ ጉድለት ያለበት ሰው ከእርሱ ጋር የተደረጉት ውሎች በመፍረሳቸው ምክንያት በቅን ልቡና በተዋዋዮች ሦስተኛ ወገኖች ላይ ለሚደርሰው ጉዳት ሀላፊ ይሆናሉ። በሌላ በኩል ከውል ውጪ ኃላፊነትን በተመለከተ ለጤናማ ሰው እንዳለው ኃላፊነት የሚኖርበት ከመሆኑ በተጨማሪ ይህ የአእምሮ ጉድለት ያለበት ያለ አግባብ ካገኘው ብልፅግና የተነሳ ላሉት ግዴታዎች ጤናማ ለሆነ ሰው ያሉበት ግዴታዎች ይኖሩበታል (የፍ/ሕ/ቁ. 350)።
የአእምሮ ጉድለት ያለበቱ በግልፅ ስላልታወቀ ሰው፡- የአእምሮ ጉድለቱ በግልፅ ያልታወቀ ሰው የፈፀማቸው የሕግ ሥራዎች ውሎች በዚሁ ሰው የአእምሮ ጉድለት ምክንያት ሊሻሩ አይችሉም። ሆኖም የአእምሮ ጉድለት ያለበት ሰው እነዚህን ውሎች በፈፀመበት ጊዜ ጉድለት የሌለበት ፈቃድ ለመስጠት በማይችልበት ሁኔታ እንደ ነበረ ለማስረዳት ከቻለ ውሎቹን ለማፍረስ ይችላል (የፍ/ሕ/ቁ. 347)። የአእምሮ ጉድለቱ በግልፅ ያልታወቀ ሰው ወራሾች ወይም ባለገንዘቦች ይህ ሰው ለፈፀመው ውል ጉድለት የሌለበት ፈቃድ ቃል አልሰጠበትምና ውሉ ሊፈርስ ይገባዋል ሲሉ የአእምሮ ጉድለት ያለበቱን ምክንያት በማድረግ የውሉን መፍረስ ለመጠየቅ አይችሉም። ይሁንና የውል አድራጊው የአእምሮ ጉድለት ከተደረገው የውል ቃል የሚታወቅ እንደሆነ ይህ ደንብ ተፈፃሚ አይሆንም (የፍ/ሕ/ቁ. 348 እና 349)።
በፍርድ የሚደረግ ክልከላ (Judicial interdiction)
መከልከሉ ለጤናውና ለጥቅሙ የሚያስፈልግ ሆኖ ሲገኝ አእይምሮው የታወከ ሰው/የፍትሐብሔር ህጉ እንደሚያስቀምጠው እብድ ሰው/ እንዲከለከል(እንዲጠበቅ) ዳኞች ፍርድ ለመስጠት ይችላሉ (የፍ/ሕ/ቁ.351)። እንዲሁም ስለ ዕብዱ ሰው ወራሾች ጥቅም ዳኞች የእብዱን መከልከል ሊፈርዱ ይችላሉ። በፍርድ ስለሚደረግ ክልከላ የክልከላ ውሳኔ እንዲሰጥ ዕብድ የሆነው ሰው ወይም ከባልና ሚስት አንዱ ወይም ከስጋ ወይም ከጋብቻ ዘመዶች አንዱ ወይም ዐቃቤ ሕግ ሊጠይቅ ይችላል። ዳኞች የክልከላ ፍርድ ሲሰጡ በሚሰጠው ውሳኔ ውስጥ ጊዜውን በመወሰን የተባለው ሰው ዕብደት የጀመረው ከእንደዚህ ያለው ጊዜ ጀምሮ ነው ሲሉ ለማስታወቅ ይችላሉ። በተሰጠው ውሳኔ ውስጥ የተቆጠረው ቀን ስለ ክልከላው ከቀረበው ጥያቄ በፊት ከሁለት ዓመት የበለጠ ጊዜ ሊኖረው አይችልም (የፍ/ሕ/ቁ.352)።
በሌላ በኩል ዳኞች የክልከላ ፍርድ ሲሰጡ ወይም ውሳኔ ከሰጡ በኋላ የክልከላውን ውጤቶች ማጥበብ የሚችሉ ሲሆን ለተከለከለው ሰው እርሱ ራሱ እንዳንዶቹን ውሎች እንዲያደርግ ሊፈቅዱለት ይችላሉ። የተከለከለ ሰው የፈፀማቸውና ከስልጣኑ በላይ የሆኑት ሥራዎች መቃወም ይቻላል። እንዲሁም የተከለከለ ሰው ችሎታ የሌለው መሆኑን ከማያውቅ ቅን ልቦና ካለው ሰው ጋር ያደረገ እንደሆነ ውሉ በመፍረሱ ምክንያት በዚህ በቅን ልቡና በተዋዋለው ሰው ላይ ስለሚደርስ ጉዳት የተከለከለው ሰው አሳዳሪ በሀላፈነት ይጠየቃል (የፍ/ሕ/ቁ.374)።
በፍርድ የተከለከለ ሰው ጥበቃን በተመለከተ ለአካለመጠን ስላልደረሰ ሰው የሚደረግ ጥበቃ ማለትም በአሳዳሪና በሞግዚት የሚተዳደርበት ሕግ ተፈፃሚ ይሆናል። በፍርድ ስለተከለከለ ሰው ክልከላ የማሳወቅ ግዴታ የአሳዳሪው ሲሆን ይህም የተከለከለው ሰው በሚኖርበት ቦታ ወይም ተቀማጭ ሆኖ እንዲኖር በተጠራበት ስፍራ ይሆናል። የተከለከለው ሰው አሳዳሪ ይህ የተከለከለ ሰው ችሎታ የሌለው ለመሆኑ በሕግ መሠረት ማስታወቂያ በወጣበት ቦታ ተቀማጭ ሆኖ እንዲኖር መጠበቅ አለበት (የፍ/ሕ/ቁ.362)። የመኖሪያ ቦታውንም የለወጠ እንደሆን በአዲሱ መኖሪያ ማስታወቂያ እንዲወጣ ማድረግ አለበት። ይህን በፍርድ ከተከለከለ ሰው ጋር ህጋዊ ግንኙነት መፈፀም የሚፈልጉ ሰዎች ስለ ሁኔታው እውቀት እንዲኖራቸው እና አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ይረዳቸዋል።
በፍርድ የተከለከለ ሰው ህጋዊ ግንኙነቶች
ስጦታ
የተከለከለ ሰው ሞግዚት በተከለከለ ሰው ስም ለተከለከለው ሰው ተወላጆች ልጆች ስጦታ ለማድረግ የሚችሉ ሲሆን እነዚህ ስጦታዎች በተከለከለው ሰው ቤተ ዘመድ ምክር ጉባኤ የተፈቀዱ ካልሆኑ በቀር ፈራሾች ናቸው (የፍ/ሕ/ቁ.367)።
ኑዛዜ
የተከለከለ ሰው ክልከላው በፍርድ ከተነገረ በኋላ ኑዛዜ ለማደረግ የማይችል ሲሆን ከተከለከለበት ቀን በፊት የተናዘዘው ኑዛዜ ይፀናል። ነገር ግን የኑዛዜው ቃላት ለርትዕ ተቃራኒ መስለው ለዳኞች የታዩ እንደሆነና የተናዘዘውም የጤናው ሁኔታ ያስደረገው መስሎ የታያቸው እንደሆነ ዳኞቹ ኑዛዜውን በሙሉ ወይም በከፊል ፈራሽ ሊያደርጉት ይችላሉ(የፍ/ሕ/ቁ.368)።
ጋብቻ
በፍርድ የተከለከሉ ሰዎች ፍርድ ቤት ካልፈቀደ በቀር የጋብቻ ውል መዋዋል አይችሉም። ከፍርድ ቤት ፍቃድ ውጪ የተደረገ የጋብቻ ውል በማንኛውም ጥቅሜ ይነካል በሚል ወገን ተቃውሞ ሊቀርብበት ይችላል (የፍ/ሕ/ቁ.369)። ፍቺና ልጅ መካድን በተመለከተ
ያሳዳሪው ፍቃድ አስፈላጊ እንደሆነ የፍትሐብሔር ህጉ ይደነግጋል።
የክልከላ መቅረት
ስለክልከላ የተሰጠው ፍርድ ሲሻር የችሎታ ማጣት ፍፃሜ ሲሆን የክልከላው ውሳኔ መቅረት አካለመጠን ያልደረሰ ልጅ ከሞግዚት አስተዳደር መውጣት ያለው ውጤት ይኖረዋል። ይህም የሚሆነው ክልከላው እንዲወሰን ያደረጉት ምክንያቶች በቀሩ እና የተከለከለው ሰው ንብረቱን ለመምራት እና ለማስተዳደር ሲችል ነው። አእምሮው ከጎደለው ሰው በቀር ስለ ክልከላው ፍርድ እንዲሰጥ ለመጠየቅ የሚችሉ ሰዎች በማናቸውም ጊዜ የክልከላው ውሳኔ እንዲቀር ጥያቄ ለማቅረብ የሚችሉ ሲሆን አሳዳሪው ወይም ሞግዚቱም የክልከላው ውሳኔ እንዲቀር ለመጠየቅ ይችላሉ (የፍ/ሕ/ቁ.377)።
በሕግ የተከለከሉ ሰዎች
በሕግ የተከለከለ ሰው ማለት አንድ በወንጀል የተቀጣ ሰው በመቀጣቱ ምክንያት ንብረቶቹን እንዳያስተዳድር ሕግ የከለከለው ሰው እንደሆነ የፍትሐብሔር ህጉ ቁጥር 380 የሚደነግግ ሲሆን አንድ ሰው በሕግ እንደ ተከለከለ ሆኖ የሚቆጠርባቸው ሁኔታዎች በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ተወስነዋል።
በሕግ የተከለከለ ሰው አሳዳሪ የማይኖረው ሲሆን የንብረቶቹ አስተዳደር ዳኞች ለመረጡት ሞግዚት ይሰጣል(የፍ/ሕ/ቁ.382 እና 383)፡፡ በሕግ የተከለከለ ሰው በፍርድ ከተከለከለ ሰው በተቃራኒ ጋብቻን ማድረግ፣ ፍቺ መጠየቅ፣ ልጅነት መቀበልና መካድ የሚችል ሲሆን ሞግዚቱ በሕግ በተከለከለው ሰው ስም እነዚህን ሥራዎች መፈፀም አይችልም(የፍ/ሕ/ቁ.386)። በሕግ የተከለከለው ሰው ያደረጋቸው ሥራዎች ወይም ውሎች ከስልጣኑ በላይ የሆኑ እንደሆነ ፈረሽ ናቸው። በሕግ የተከለከለ ሰው ችሎታ ማጣትን ያስከተለው ቅጣት በተፈፀመ ጊዜ በሕግ የተወሰነበት ክልከላ ቀሪ ይሆናል(የፍ/ሕ/ቁ.388)።
በአጠቃላይ ችሎታ ህጋዊ ግንኙነትን ለማከናወን መሠረታዊ ጉዳይ ሲሆን ማንኛውም ሰው ህጋዊ ግንኙነቶችን ከሰዎች ጋር ከመፈፀሙ በፊት የሚዋዋለው ሰው ችሎታ ያለው መሆኑን ማረጋገጥ በኃላ ላይ ሊከሰቱ ከሚችሉ እንደ ውል መፍረስ ካሉ ችግሮች የሚታደገው ስለሆነም ተገቢው ጥንቃቄ ማድረግ እጅግ አስፈላጊ ነው።
በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ