የመክሰር ሕግ በኢትዮጵያ

ማውጫ

ይህን ጽሑፍ ያጋሩ

በአሁኑ ጊዜ በኪሳራ ምክንያት የንግድ ድርጅትን መዝጋትና ንብረቱን ሸጦ ለገንዘብ ጠያቂዎች ማከፋፈል የመጨረሻ እንጂ የመጀመርያ አማራጭ አይደለም። ይህ ሀሳብ በሀገራችን አዲሱ ንግድ ሕግ አንድ የንግድ ድርጅት ኪሳራ ሲገጥመው ከተቻለ ድርጅቱን ለማትረፍ፣ ካልተቻለም የተገኘውን ያክል ንብረት ከብክነት በመታደግ ለገንዘብ ጠያቂዎች በፍትሐዊ መንገድ ለማከፋፈል ስለሚቻልበት ሁኔታ የሚደነግጉ የኪሳራ እና የመጠባበቂያ ስምምነትን የሚመለከቱ ድንጋጌዎች ስር ተካቶ ይገኛል፡፡ ይህ ጽሁፍ ስለ መክስር ሥነ ሥርዓት እና አፈፃፀሙን የሚዳስስ ነው፡፡

የመክሰር ትርጉምና ታሪካዊ አመጣጥ

የመክሰር ሕግ ታሪካዊ አመጣጥን ዕድገቱ ከሰው ልጆች የግብይት ስርዓት ማደግ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ እንደሆነና ከጥንት ሮማውያን ጀምሮ ቀስ በቀስ የሀቀኛ ተበዳሪ መክሰርንና ለሌላ ቅጣት ከመዳረግ ይልቅ ዕዳው በንብረቱ ላይ እንዲፈፀም የማድረግ እና የገንዘብ ጠያቂዎችን የንብረት መብት ለማስጠበቅ ታስቦ የመጣ የሕግ ማዕቀፍ መሆኑ ይገለፃል፡፡ የመክሰር ሕግ የራሱ የሆነ ጤናማ የኢኮኖሚ ግንኙነት የመፍጠርና ግንኙነቱ ሲደፈርስም ስርዓት ባለው መንገድ አንዱ የሌላውን ሀብት በመውሰድ እንዳይበለፅግና ሁሉም በሀብት ላይ ያለውን የተጠቃሚነት መብቱን እንዲሰራበት ለማስቻል የሚወጣ ሕግ ነው፡፡

የመክሰር ትርጉምን በሚመለከት የተለያዩ ፃህፍት እየተረጎሙት የመጡ ሲሆን ለግንዛቤ ይረዳን ዘንድ እነዚህ ቀጥሎ ያለዉን ትርጓሜ ለማስፈር ተሞክሯል፡፡ የሀገራችን የ1952 ቱ የንግድ ሕግ ቁጥር 969 ስለመክሰር የሚያስፈልግ ሁኔታ በሚል ስር “ማንኛውም ከንግድ የተያያዘውን ዕዳውን መክፈል ያቋረጠና መክሰሩ በፍርድ የተወሰነ ሁሉ የከሰረ ሆኖ የሚቆጠር ነው” በማለት ይደነግጋል፡፡ ከዚህ ትርጓሜ መገንዘብ እንደሚቻለው መክሰር ዕዳን ለመክፈል ካለመቻልና ይሄውም በፍርድ ቤት ከሰሯል የሚል ውሳኔ ሲሰጥበት አንድ ሰው ከስሯል ሊባል እንደሚችል ነው፡፡ በሌላ አባባል አንድ ሰው ዕዳውን መክፈል አለመቻሉ ብቻ እንደከሰረ እንደማያስቆጥረውና ከስሯል ብሎ የመወሰን ሥልጣን ለመደበኛ ፍርድ ቤት የተሰጠ መሆኑን ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ብዙ አገሮች መክሰር “Bankruptcy” ከንግድ ጋር ብቻ ተያይዞ መታየት የለበትም ከሚል አመለካከት በመነሳት መክሰር በማንኛውም ዕዳውን ለመክፈል ባልቻለ ግለሰብም ተፈፃሚነት እንዲኖረው የሚያስችል ሕግ በማውጣት ላይ ናቸው፡፡

የመክሰር ሕግ ተፈፃሚነት

የተለያዩ አገሮች የተለያዩ የመክሰር ሕግ (Bankruptcy Law) ያላቸው ሲሆን እንደ አካሄድም የተለያየ አሠራርን የሚከተሉ ናቸው፡፡ በአንዳንድ ሀገራት የመክሰር ሕግ ተፈፃሚነት እስከ ግለሰብ የሚዘልቅ ነው፡፡ በሌሎች ሀገራት የሕግ ማዕቀፍ የተወሰኑ ልዩነቶችን ብቻ በመፍጠር የመክሰር ሕግን በግለሰቦች፣ ነጋዴዎችም ሆኑ ነጋዴ ባልሆኑ ላይ ተፈፃሚነት ያለው ነው፡፡ የሀገራችን ሕግ ሲታይ አዲሱ የንግድ ሕግ ስንመጣ በዚህ ሕግ አንደኛ መፅሐፍ በቁጥር 5 መሠረት ነጋዴ በሆኑ ሰዎችና በዚህ ሕግ አንደኛ መፅሐፍ በቁጥር 234 መሠረት የእሽሙር ማህበር ከሆኑት በቀር በንግድ ማህበሮች ሁሉ ላይ ተፈፃሚዎች ይሆናሉ፡፡ ይህ ማለት ግለሰቦች ሆነው በአዲሱ የንግድ ሕግ አንቀጽ 5 ላይ የተዘረዘሩ ተግባራትን የሚያከናውኑ ከሆነ ከእሽሙር ማህበር በስተቀር ሌሎች የንግድ ማኅበራት በመክሰር ሕግ የሚዳኙ መሆናቸውን የሚደነግግ ነው፡፡

የመክሰር ሥነ-ሥርዓት ስለ መክፈት

በአዲሱ የንግድ ሕግ አንቀጽ 705 መሠረት የመክሰር ሥነ ሥርዓት የሚከፈተዉ ክፍያዎችን ያቋረጠ ባለዕዳ አቤቱታ ሲያቀርብ ነዉ፡፡ ባለዕዳዉ በዚህ መጽሐፍ ርዕስ ሦስት መሠረት መልሶ የማደራጀት ሥነ-ሥርዓት ለመክፈት አስቀድሞ አቤቱታ ያቀረበ ካልሆነ በስተቀር ክፍያዎችን ያቋረጠዉ ባለዕዳ በጣም ቢዘገይ በ45 ቀናት ዉስጥ የመክሰር ሥነ-ሥርዓት ለመክፈት ለፍርድ ቤት አቤቱታ ማቅረብ አለበት፡፡ ይህ ግዴታ በኅብረት የሽርክና ማኅበር ዉስጥ በእያንዳንዱ ማኅበርተኛ ላይ እንዲሁም ሁለት ዓይነት ኃላፊነት ባለበት የሽርክና ማኅበር ዉስጥ ኃላፊነታቸዉ ባልተወሰነ ማኅበርተኞች ላይ ተፈፃሚ ይሆናል፡፡ ጊዜው ያልሞላዉ እና የኢኮኖሚ ወይም የፋይናንስ ችግር በተጨባጭ ያጋጠመዉ ወይም ያጋጥመዋል ተብሎ የሚጠበቅ ባለዕዳ ሲያመለክት ብቻ ነዉ፡፡ ባለዕዳዉ የቅርብ ጊዜ የሒሳብ መግለጫዎችን፣ የገንዘብ ችግሮችን ሁኔታ እና የሚፈቱበትን መንገድ የሚያስረዳ ጽሁፍ እንዲሁም የገንዘብ ፍሰት ቅድመ ትንበያ ኪሳራን ለሚመለከተዉ ፍርድ ቤት የሚያቀርብ ሲሆን ፍርድ ቤቱ አስፈላጊ ናቸዉ ብሎ የሚያምናቸዉን ሌሎች ማናቸዉም ሰነዶች እና መረጃዎች ባለዕዳዉ እንዲያቀርብ ትእዛዝ ሊሰጥ ወይም እንደባንኮች እና የታክስ ባለሥልጣን አካላት ያሉ 3ኛ ወገኖችን እንዲያቀርቡ ትእዛዝ ሊሰጥ ይችላል፡፡ አስገዳጅ የሆኑ የኢትዮጵያ ሕጎች እንደተጠበቁ ሆነዉ ዕዳን መልሶ የማዋቀር የባለዕዳዉን ንብረቶች እና እዳዎች ወይም ሌላ ማንኛዉንም የባለዕዳዉን የካፒታል መዋቅር ክፍል አወቃቀር፣ ሁኔታዎች ወይም መዋቅር መቀየርን ወይም የንግድ ሥራዉን ንብረቶች ወይም ክፍሎች ወይም አጠቃላይ የንግድ ሥራ እንቅስቃሴዉን በመንቀሳቀስ ላይ እንዳለ የንግድ ሥራ መሸጥን እንዲሁም አስፈላጊ የሆኑ ማናቸዉንም የሥራ ሂደት ለዉጦችን ማድረግን ወይም ከእነዚህ ዉስጥ የተወሰኑትን ወስዶ ማቀናጀትን ሊያካትት ይችላል፡፡

የመክሰር ሥነ-ሥርዓት በማን ይከፈታል

  • ከባለዕዳዉ ጋር በአንድነትና በተናጠል ኃላፊ የሆኑ ሰዎች፣
  • በባለዕዳዉ ላይ ጊዜዉ የደረሰ እና መከፈል ያለበት የክፍያ ጥያቄ ያላቸዉ አንድ ወይም ከዚያ በላይ ገንዘብ ጠያቂዎች፣
  • ከመክሰር ሥነ-ሥርዓት ዉጭ ባለዕዳዉን ንብረት እንዲያጣራ የተሾመ ንብረት አጣሪ፣
  • ባለዕዳዉ የንግድ ሥራ ማቋረጡ ባለዕዳዉን ከሚመለከት የወንጀል ሥነ ሥርዓት ግልጽ በሚሆንበት ጊዜ ማንኛዉም ዐቃቤ ሕግ፣አቤቱታ በሚያቀርቡበት ጊዜም እንዲሁ ሊከፈት ይችላል፡፡
  • በተጨማሪም በባለዕዳዉ ላይ በመካሄድ ላይ ባለ ሥነ-ሥርዓት የተነሳ ባለዕዳዉ ክፍያዎችን ያቋረጠ መሆኑ ግልጽ በሚሆንበት ጊዜ ፍርድ ቤቱ በራሱ ተነሳሽነትም የመክሰር ሥነሥርዓት ሊያስጀምር ይችላል፡፡ ባለዕዳዉ ክፍያዎችን ያቋረጠ መሆኑን ያረጋገጠዉ ፍርድ ቤት ጉዳዩን በዚህ መጽሐፍ መሠረት የመክሰር ፍርድ ለመስጠት ሥልጣን ወዳለዉ ፍርድ ቤት ይልካል፡፡

ስለ መክሰር የሚሰጥ ፍርድ

ለመጀመሪያ ጊዜ ጉዳዩ በሚሰማበት ጊዜ ወይም አግባብ በሚሆንበት ጊዜ የኪሳራ መርማሪዉ ሪፖርት ሲደርሰዉ ፍርድ ቤቱ፡-

  • ባለዕዳዉ የከሰረ መሆኑን ያዉጃል፣
  • ተቆጣጣሪ ዳኛዉን ይሾማል፣
  • የመክሰር ሥነ-ሥርዓትን ለማከናወን የከሰረዉን ሰዉ ንብረት ጠባቂ ይሾማል፣
  • ክፍያዎች የተቋረጡበት ቀን መልሶ በማደራጀት ሥነ ሥርዓት ዉስጥ ያልተወሰነ ከሆነ ክፍያዎች የተቋረጡበትን ቀን ይወስናል፡፡

የመክሰርን ሥራ የሚያስፈጽሙ ሰዎችና አባላት

ፍርድ ቤት– የመክሰር ሥነ-ሥርዓትን በመክፈት ረገድ ፍርድ ቤት ሥልጣን እንዳለዉ ከአዲሱ የንግድ ሕግ አንቀጽ 604 እና አንቀጽ 715 መሠረት መረዳት ይቻላል፡፡

ተቆጣጣሪ ዳኛ– ስለተቆጣጣሪ ዳኛዉ ሹመት እና ሥልጣን አዲሱ የንግድ ሕግ 716 እና 717 ን መመልከት ይቻላል፡የከሰረ ሰዉ ንብረት ጠባቂ- በአዲሱ የንግድ ሕግ አንቀጽ 718 መሠረት ፍርድ ቤቱ የመክሰር ሥነ ሥርዓት እንዲከፈት በሚሰጠዉ ፍርድ ዉስጥ አንድ የከሰረ ሰዉ ንብረት ጠባቂ ይሾማል፡፡ በሥነ-ሥርዓቱ ወቅት በማናቸዉም ጊዜ የከሰረዉ ሰዉ ንብረት ጠባቂ በማንኛዉም ገንዘብ ጠያቂ፣ በገንዘብ ጠያቂዎች ኮሚቴ ወይም በዐቃቤ ሕግ በሌላ እንዲተካ ለፍርድ ቤቱ አቤቱታ ማቅረብ ይቻላል፡፡ ፍርድ ቤቱም በራሱ ሥልጣን የከሰረዉ ሰዉ ንብረት ጠባቂዉን በሌላ ሊተካ ይችላል፡፡ የከሰረሰዉ ንብረት ጠባቂ ሥልጣን እና ግዴታዎችም በአዲሱ የንግድ ሕግ አንቀጽ 720 ላይ ተመልክቷል፡፡

የገንዘብ ጠያቂዎች ኮሚቴ– ተቆጣጣሪ ዳኛዉ የመክሰር ሥነ ሥርዓት በተከፈተ በ10 ቀናት ዉስጥ ከፍተኛ መጠን ያላቸዉ የክፍያ ጠያቂዎች ካላቸዉ የገንዘብ ጠያቂዎች መካከል 5 አባላትን የያዘ የገንዘብ ጠያቂዎች ኮሚቴ እንደሚያቋቁም በአዲሱ የንግድ ሕግ አንቀጽ 722 ላይ ሰፍሯል፡፡ የኮሚቴዎች መብትና ግዴታም በዚሁ ሕግ ተደንግጎ ይገኛል፡፡

ዐቃቤ ሕግ– በመክሰር ሥነ ሥርዓት ዉስጥ ዐቃቤ ሕግ ሥልጣን ያለዉ ሲሆን ይህን ሥነ ሥርዓት ከማስፈጸም ጋር ግንኙነት ያላቸዉ ማናቸዉንም የባለቤትነት ማረጋገጫዎች መዛግብትና ሰነዶች ተቆጣጣሪ ዳኛዉ እንዲቀርበለት የማዘዝ መብት በአዲሱ የንግድ ሕግ አንቀጽ 724 መሠረት አለዉ፡፡ እንዲሁም የዐቃቤ ሕግ መብቶች በዚሁ ሕግ አንቀጽ 740 ሥር ሰፍሮ ይገኛል፡፡

የመክሰር ሥነ ሥርዓት የሚዘጋባቸዉ ምክንያቶች

በአዲሱ የንግድ ሕግ አንቀጽ 696 መሠረት የመክሰር ሥነ ሥርዓትን መልሶ መክፈት (እንደገና እንዲጀመር ለፍርድ ቤቱ ማመልከት) መቻሉ እንደተጠበቀ ሆኖ የመክሰር ሥነ ሥርዓት በሚከተሉት ምክንያቶች ሊዘጋ ይችላል፡-

  • ከንብረት ማጣራት የተገኘዉን ገንዘብ ጨርሶ በማከፋፈል፣
  • የሚበቃ ንብረት ባለመኖሩ እና
  • ከንብረቱ የሚፈለግ ዕዳ ባለመኖሩ ሲሆኑ 2ኛ እና 3ኛ ምክንያቶች ዝርዝራቸዉ በዚሁ ሕግ ከአንቀጽ 795 እሰከ 797 ድረስ ተደንግገዉ ይገኛሉ፡፡

የከሰረን ሰው ነፃ ስለመደረግ (Discharge)

ነባሩ የንግድ ሕግ የሚከስሩ ነጋዴዎች ከዕዳ ነፃ የሚወጡበት የሕግ ድንጋጌ አላካተተም። በዚህም ምክንያት ብዙ ነጋዴዎች የኪሳራን ሥነ-ሥርዓት ፈቅደው እንዳያመለክቱ ሊያደርግ ችሏል። ዘመናዊ የሆኑ የኪሳራ ሕጎች ንፁህ ነጋዴዎች በተወሰነ መልኩ የኪሳራ ሥነ-ሥርዓቱ ከተዘጋ በኋላ ነፃ የሚሆኑበትን ሁኔታ ይደነግጋሉ። አዲሱ የንግድ ህጋችን ነጋዴዎች የኪሳራ ሥነ-ሥርዓቱ በሕጉ መሠረት ካበቃ በኋላ ከዕዳ ነፃ የሚሆኑባቸውን የሕግ ድንጋጌዎች በመፅሐፍ ሦስት በርዕስ 5 አንቀጽ 799 ሥር አስቀምጧል። በዚህም መሠረት አንድ የኪሳራ ውሳኔ የተላላፈበት ነጋዴ የኪሳራው ብይን ከተሰጠበት ቀን አንስቶ ከሶስት ዓመት በኋላ ከዕዳ ነፃ ለመሆን ለፍ/ቤት ማመልከት እንደሚችል በአዲሱ የንግድ ሕግ ተካቷል።

ይህ መብት በዘፈቀደ ለሁሉም የሚሰጥ አይደለም። ንጹህ የሆኑ የተፈጥሮ ሰው ነጋዴዎችን ብቻ የሚመለከት ነው። እንደዚህም ሆኖ ከኪሳራ ጋር ተያያዠነት ያላቸውን ወንጀሎች ፈፅሞ የተፈረደበት፤ ንብረት ስለመደበቁ ወይም ማሸሹ ማስረጃ የቀረበበት፤ በኪሳራ ሥነ-ሥርዓት ሂደት ያልተባበረ ወይም ግዴታውን ያልተወጣ ነጋዴ ወይም ተደጋጋሚ የኪሳራ ውሳኔ በአምስት ዓመት ውስጥ ያስተናገደ ነጋዴ ይህን መብት አያገኝም። ከዕዳ ነፃ አይደረግም። በተጨማሪም የተወሰኑ ዕዳዎች ሌሎች ሕጎች በልዩ ሁኔታ ካልፈቀዱ በስተቀር ነፃ እንደማይደረጉ በአዲሱ የንግድ ሕግ ተካቷል።

ቀላል የኪሳራ ሥነ-ሥርዓት

ቀላል የኪሳራ ሥነ-ሥርዓት ዓላማ ሥነ-ሥርዓቱን ቀላል፤ ጊዜና ወጪ ቆጣቢ በማድረግ ለኪሳራ የተዳረጉ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች በሥነ-ሥርዓቱ ከንግድ ሥርዓቱ የሚወጡበትን ሥርዓት መዘርጋት ነው። ቀላል የኪሳራ ሥነ-ሥርዓት ሊከፍቱ የሚችሉት አነስተኛና መካከላኛ ኢንተርፕራይዞች ሲሆኑ እነሱም የሚከተሉትን መመዘኛዎች የሚያማሉ ከሆነ ነው፡- 1) ባለፉት 12 ወራት የሒሳብ ሚዛናቸው የሀብት መጠን ከ20 ሚሊዮን ብር ያነሰ ከሆነ፤ 2) የሠራተኛ ቁጥራቸው ከ10 ያነሰ ከሆነ፤ ወይም 3) ባለፉት 12 ወራት ዓመታዊ ሽያጫቸው ከ5 ሚሊዮን ብር ያነሰ ከሆነ ነው።

ይህን ሥነ-ሥርዓት ቀላል የሚያሰኙት ዋና ዋና ባህርያት የሚከተሉት ናቸው፡- 1) የሚቀርቡት ሰነዶችና አባሪዎች ዝርዝር አጭር መሆናቸው፤ 2) በፍ/ቤቱ ተቆጣጣሪነትና በንብረት ጠባቂው ኃላፊነት ብቻ (ተቆጣጣሪ ዳኛና የገንዘብ ጠያቂዎች ኮሚቴ ሳያስፈልግ) ሥነ-ሥርዓቱን ማከናወን መቻሉ፤ 3) የንብረት ማጣራትና መሸጥ ተግባራት የተንዛዛውን መደበኛ ሥነ-ሥርዓቶች የግድ አለመከተላቸው፤ 4) ንብረት ጠባቂው የባለዕዳውን ንብረት አጣርቶ፤ ሸጦ በአንድ ዓመት ውስጥ የማከፋፈል ግዴታ የተጣለበት መሆኑና ሥነ-ሥርዓቱም በአንድ ዓመት የጊዜ ገደብ የታጠረ መሆኑ፤ እና 5) በዚህ ሥነ-ሥርዓት ሥር አልፈው ፋይላቸው የተዘጋላቸው የተፈጥሮ ሰዎች ከዕዳ ነፃ ወዲያውኑ ሊታወጅላቸው መቻሉ፤ናቸው። ፍ/ቤቱም ቀላል የኪሳራ ሥነ-ሥርዓት ከተከፈተ ባንድ ዓመት ውስጥ መጠናቀቁን ማረጋገጥ ይኖርበታል፡፡

በንቃተ ሕግ፣ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት