የጥብቅና ፈቃድ እና የጠበቆች ሙያዊ ግዴታ

ማውጫ

ይህን ጽሑፍ ያጋሩ

መግቢያ

ሰዎች በእለት ተዕለት የማኅበራዊ ህይወት መስተጋብር የሚገጥሟቸውን አለመግባባቶች በፍርድ ቤት ወይም በሌሎች አማራጭ የሙግት መፍቻ መንገዶች ለመፍታት ጥረት ያደርጋሉ፡፡ በዚህ ሂደትም የሕግ ባለሞያዎችን እገዛ የሚያስፈልጋቸው በመሆኑ በጠበቆች ተወክለው ክርክራቸውን ያደርጋሉ፡፡ በዚህ ጽሑፍ ከፌደራል ጥብቅና አገልግሎት ፈቃድ አሰጣጥ እና አስተዳደር አዋጅ 1249/2013 አንፃር የጠበቃን ምንነት፣ የጥብቅና ፈቃድ ለማግኘት ሊሟሉ የሚገባቸውን መስፈርቶች እንዲሁም ጠበቆች ያለባቸውን ኃላፊነት በአጭሩ እንመለከታለን፡፡

የጠበቃ ምንነት

በፌደራል ጥብቅና አገልግሎት ፍቃድ አሰጣጥ እና አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1249/2013 አንቀጽ 2(1) መሠረት ጠበቃ ማለት የግል የጥብቅና አገልግሎት ለመስጠት ፍቃድ የተሰጠው ሰው ሲሆን በአዋጁ አንቀጽ 8 ላይ ለተደነገገው በውጭ ሀገር ሕግ መሠረት የጥብቅና አገልግሎት ፍቃድ የተሰጠውን ሰውም ያካትታል፡፡ በተመሳሳይ የጥብቅና ድርጅት ማለት ሁለት እና ከዚያ በላይ የሆኑ የፀና የጥብቅና ፈቃድ ባላቸው ጠበቆች የጥብቅና አገልግሎት ለመስጠት ማቋቋም ድርጅት ነው፡፡

በተጨማሪም የጥብቅና ሙያ አገልግሎት ማለት የገንዘብ ክፍያ በመቀበል ወይም ወደፊት የሚገኝ ቀጥተኛ ወይም ቀጥተኛ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት ሲባል ወይም ያለ ክፍያ በጠበቃ ወይም በጥብቅና ድርጅት የሚሰጥ ማንኛውም የሕግ አገልግሎት ሲሆን በሕግ ጉዳዮች ምክር መስጠት፣ ከወንጀል ጉዳዮች ወጪ የማደራደር ሥራ መሥራት፣ የሕግ ሰነድ ማዘጋጀት ወይም በደንበኛ ስም ሰነድ ማቅረብ፣ በፍርድ ቤት፣ በአስተዳደራዊ ጉባኤዎች፣ ከፊል የዳኝነት ሥልጣን ባላቸው አካላት፣ በግልግል ዳኝነት ጉባኤዎች እና በሌሎች አማራጭ የሙግት መፍቻ መድረኮች ደንበኛን ወክሎ መቅረብና መከራከርን እንደሚያጠቃልል በአዋጁ አንቀጽ 2(5) መረዳት ይቻላል፡፡

የጥብቅና ፈቃድ አይነቶችና ፈቃድ ለማግኘት ሊሟሉ የሚገባቸው መስፈርቶች

በአዋጁ አንቀጽ 11 መሠረት ሶስት ዓይነት የጥብቅና ፍቃዶች አሉ፡፡ የመጀመሪያው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የጥብቅና ፍቃድ ሲሆን ይህም በመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ሥልጣን ሥር ለሚታዩ ጉዳዮች የጥብቅና አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ነው፡፡ ሁለተኛው የፌደራል ማናቸውም ፍርድ ቤት የጥብቅና ፍቃድ ሲሆን ይህም ከፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ጀምሮ እስከ ፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሚታዩ ጉዳዮች የጥብቅና ፈቃድ መስጠት የሚያስችል ነው፡፡ ሶስተኛው የፌደራል ልዩ ጥብቅና ፍቃድ ሲሆን ለህብረተሰቡ አጠቃላይ መብት እና ጥቅም መከበር በነፃ አገልግሎት ለሚሰጥ ሰው ወይም ድርጅት እንዲሁም አቅም ለሌላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ለሚሰጡ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሕግ ትምህርት ቤቶች እና የሕግ መምህራን የሚሰጥ ፈቃድ ነው፡፡

እነዚህ ፈቃዶች እያንዳንዳቸው እንደየባህሪያቸው የሚጠይቋቸው ተጨማሪ መስፈርቶች ቢኖሩም የትኛውንም የጥብቅና አገልግሎት ፍቃድ ለማግኘት በመሠረታዊነት መሟላት ያለባቸው መስፈርቶች በአዋጁ አንቀጽ 6 ተመልክተዋል፡፡ እንዚህም

  • የኢትዮጵያ ዜግነት ያለው ወይም ትውልደ ኢትዮጵያዊ መሆን
  • እውቅና ካለው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ቢያንስ በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪ ያለው መሆን
  • ለመጨረሻ ጊዜ ይሰራበት ከነበረበት ተቋም ድርጅቱን ከመልቀቁ በፊት ባሉት ሁለት ዓመታት ውስጥ በከባድ ዲስፕሊን ጥፋት ያልተቀጣ እና የመልካም ሥነ-ምግባር ማረጋገጫ ማቅረብ መቻል
  • በሕግ ሙያ የሚፈለገውን የሥራ ልምድ ያሟላ መሆን እና
  • እንደ አስፈላጊነቱ ፍቃድ ለማግኘት የሚሰጠውን የሙያ መግቢያ ፈተና ያለፈ መሆን ናቸው፡፡

እንዚህን መስፈርቶች የማያሟላ ሰው የጥብቅና ፈቃድ ሊሰጠው አይችልም፡፡ በተጨማሪም ታስቦበት በሚፈፀምና ከሙያ ሥነ ምግባር ጉድለት ጋር በተያያዘ 3 ዓመትና ከዚያ በላይ ፅኑ እስራት በሚያስቀጣ ወንጀል ተከሶ ጥፋተኛ የተባለና አግባብነት ባለው ሕግ ያልተሰየመ ወይም በሕግ አገልግሎት እንዳይሰማራ በሕግ ወይም በፍርድ ቤት የከተከለከለ ሰው የጥብቅና ፈቃድ ሊሰጠው እንደማይችል በአዋጁ አንቀጽ 7 ተደንግጓል፡፡

የጠበቆች ሙያዊ ግዴታዎች

ጠበቃዎች በአዋጁ የተመለከቱ የጠበቆች የሙያ ግዴታን ማክበር ይጠበቅባቸዋል፡፡ እነዚህም ግዴታዎች በአዋጁ ከአንቀጽ 22 እስከ 24 እንዲሁም በአንቀጽ 26 እና 31 የተደነገጉ ሲሆን ማንኛውም ጠበቃ ወይም የጥብቅና ድርጅት፡-

  • በደንበኛው፣ በፍርድ ቤት ወይም በማንኛውም አግባብ ባለው አካል የጥብቅና ፍቃድ እንዲያሳይ ሲጠየቅ የማሳየት ግዴታ አለበት፡፡ በተመሳሳይ አንድ ጠበቃ የጥብቅና ፍቃዱን በማንኛውም ሁኔታ ለሌላ ሰው መጠቀሚያ ወይም መገልገያ አሳልፎ መስጠት የለበትም፡፡
  • ለአጭር ጊዜ ከሚሰጥ የሕግ ምክር አገልግሎት ውጪ ከደንበኛው ጋር የሚያደርገውን የጥብቅና አገልግሎት ውል በጽሑፍ ማድረግ አለበት፡፡ ውሉ ደንበኛው ለጠበቃው የሚከፍለውን አጠቃላይ የገንዘብ ክፍያ፣ የአከፋፈሉን ስልት እና ጊዜ፣ ጠበቃው በጉዳዩ ላይ የሚሰጠውን የጥብቅና አገልግሎት የሚያካትት መሆን አለበት፡፡
  • ለጥብቅና አገልግሎት መስጫ የሚሆን ቢሮ የማሟላት፣ የጥብቅና ሥራን በአገናኝ አማካኝነት ያለመሥራት፣ የጥብቅና ውልን ያለበቂና ሕጋዊ ምክንያት ያለማቋረጥ እና በጥብቅና ውሉ ከተገለፀው የክፍያ መጠን በላይ ተጨማሪ ክፍያ ከደንበኛ ያለመጠየቅ ግዴታ አለበት፡፡
  • የአገልግሎት ሥራውን በታማኝነት መሥራትና የፍትሕ አጋር መሆን አለበት፡፡
  • ያለበቂ ምክንያት ጉዳይን ያለማጓተት፣ ምስክሮችን በሐሰት ያለማደራጀት፣ ሀሰተኛ ማስረጃ ያለማቅረብ ወይም ያለማስቀረብ፣ ተዘጋጅቶ የመቅረብና ተገቢውን ክርክር የማድረግ፣ የሕግ መሠረት የሌለውንና የማያዋጣ ጉዳይን ያለመያዝ፣ የደንበኛውን ወይም ባለጉዳዩን ምስጢር ያለማውጣት እና ሌሎች መሰል የሥነ-ምግባር ግዴታ አለበት፡፡
  • እንደጉዳዩ ክብደትና ቅለት እየታየ በዓመት ከሶስት ጉዳይ ያልበለጠ ነፃ የጥብቅና አገልግሎት የመስጠት ግዴታ አለበት፡፡ አገልግሎቱ የሚሰጠውም የመክፈል አቅም ለሌላቸው ሰዎች፣ ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች፣ ለሲቪክ ማኅበራት እና ለማኅበረሰብ ተቋማት፣ ፍርድ ቤት የጥብቅና አገልግሎት እንዲያገኙ ለሚጠይቅላቸው ሰዎች፣ ሕግን፣ የሕግ ሙያን እና የፍትሕ ሥርዓቱን ለማሻሻል ለሚሰሩ ኮሚቴዎች እና ድርጅቶች ነው፡፡
  • በዓመት ውስጥ በድምሩ ከ24 እስከ 30 ሰዓት የሚደርስ የሕግ ሥልጠና የመውሰድ ግዴታ አለበት፡፡

ከላይ የተጠቀሱትን ኃላፊነት ያልተወጣ ጠበቃ ወይም የጥብቅና ድርጅት እንደ ነገሩ ሁኔታ በአዋጁ አንቀጽ 84 እና 85 በቀላል እና በከባድ የዲስፕሊን ጥፋት ይቀጣል፡፡ ይህ ቅጣት የፍትሐብሔርና የወንጀል ተጠያቂነትን የሚያስቀር አይደለም፡፡

ማጠቃለያ

በአጠቃላይ ጠበቆች ለፍትሕ መስፈን የማይተካ ሚና ያላቸው በመሆኑ የሙያ ሥነ ምግባርን በማክበር ሀላፊነታቸውን ሊወጡ የሚገባ ሲሆን ህብረተሰቡም ለህጉ መከበር አስተዋፅኦ ከማድረግ በተጨማሪ በሕግ መሠረት ግዴታቸውን በማይወጡት ላይ ተጠያቂነት እንዲሰፍን የበኩሉን ሊያበረክት ይገባል፡፡

በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ