የፍትሕ ሚኒስቴር በሴቶች እና ሕፃናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች የመዝገብ እና ወሲባዊ ጥቃት አድራሾች ብሔራዊ የመረጃ አስተዳደር ሶፍትዌር ለማበልፀግ የሚያስችለውን የስራ ውል ስምምነት ከድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ጋር እንዲሁም አብሮ ለመሥራት የሚያስችለውን የስራ መግባቢያ ሰነድ ደግሞ ከሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በዛሬው እለት በድሬድዋ ዩኒቨርሲቲ በመገኘት ተፈራርመዋል።
የስምምነት ፊርማው በፍትሕ ሚኒስቴር በኩል የተቋም ግንባታና ሪፎርም ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ክቡር ዶ/ር ኤርምያስ የማነብርሃን፣ በድሬድዋ ዩኒቨርሲቲ በኩል የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር መገርሳ ቃሲም ፣ በሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ደግሞ በሚኒስትር ዲኤታ ማዕረግ የሚኒስትር አማካሪ አቶ ጌታቸው በዳኔ አማካኝነት ተፈፅሟል።
በዚህ ወቅት ሚኒስትር ዲኤታው ክቡር ዶ/ር ኤርምያስ የማነብርሃን እንደገለፁት በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን አስመልክቶ የመረጃ ሥርዓት መገንባት አስፈላጊ ከመሆኑ ባለፈ ካለመረጃ ተወዳዳሪ መሆን እንደማይቻልና እውነትና ፍርድ የሚበየነው ዳታ ሲኖር መሆኑን አፅንኦት ሰጥተው ወንጀልን ለመከላከል ብሎም ጥቃት አድራሾችን በተመለከተ ክትትል ለማድረግና አስፈላጊውን ቅጣት እንዲያገኙ ለማስቻል የመረጃ ስርአቱ የሚኖረው ጠቀሜታ የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።
አያይዘውም ይህንን የመረጃ ሥርዓት ለማበልፀግ የተስማማውን የድሬድዋ ዩኒቨርሲቲ በተያዘለት ጊዜ እንዲያስረክብና ስራውን ለሚሰሩት ባለሙያዎች አስፈላጊውን የአመራር እገዛ እንዲያደርግ አደራ ብለዋል።
የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር መገርሳ ቃሲም በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ከተሰጠው ተልእኮና የትኩረት መስክ ውስጥ አንደኛው የቴክኖሎጂ ዘርፍ መሆኑንና ይህንን ተከትሎም ከፍትሕ ሚኒስቴር ጋር በጋራ ለመሥራት ስምምነት በመፈረማቸው መደሰታቸውን ገልፀው ለስራው እውን መሆን ድርሻቸውን በመወጣት የራሳቸውን አሻራ የሚያሳርፉ መሆኑን አረጋግጠዋል።
የመረጃ አስተዳደር ስርአቱ አስፈላጊነት ወሲባዊ ጥቃትን በመከላከልና አስፈላጊውን ምላሽ ለመስጠት በተለይም ፓሊሲና የሕግ ማሻሻያዎች ለማድረግ የሚያስፈልጉ ግብአቶችን ለማግኘት፣ወሲባዊ ጥቃት ፈፃሚዎች ተጠርጣሪ ሆነው ከተያዙበት ጊዜ ጀምሮ በሕግ አግባብ ተጠያቂ ከሆኑና ቅጣታቸውን ፈፅመው ወደ ማህበረሰቡ ከተቀላቀሉ በኋላ በሴቶችና ሕፃናት ላይ ወንጀሉን በድጋሚ እንዳይፈፅሙ ቁጥጥር ለማድረግ ብሎም ህብረተሰቡን ለማስተማርና ማህበረሰቡን ከወሲባዊ ጥቃቶች መጠበቅ ነው።
የመረጃ አስተዳደር ሶፍትዌሩን በአምስት ወራት ውስጥ አበልፅጎ ለማስረከብ በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በኩል የተገለፀ ሲሆን ስራው በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ እንዲጠናቀቅም የሶስቱም ተቋማት የስራ ሀላፊዎች አስፈላጊው ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርጉ ተጠቁሟል።