የፍትሕ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የተቀናጀ የወንጀል መዛግብት ስርአት ፕሮጀክት ዙሪያ ዉይይት አደረጉ

Ministry of Justice and Ethiopian Artificial Intelligence Institute Discuss Integrated Criminal Records System Project

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የተቋም ግንባታና ሪፎርም ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ኤርምያስ የማነብርሀን የተቀናጀ የወንጀል አስተዳደር ሥርዓትን ዘመናዊና በቴክኖሎጂ የተደገፈ ለማድረግ በ 3-አመቱ የፍትሕ ዘርፍ የትራንስፎርሜሽን ፍኖተ ካርታ ውስጥ ራሱን የቻለ አንድ አምድ በማድረግ አቅዶና ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት ላይ መሆን አንስተው ይህንኑ ስራ እዉን ለማድረግ የሚያስችል ዉይይት ከኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ጋር በዛሬዉ እለት አካሂደዋል።

የአለማችን ሁኔታ በአጭር አመታት ጊዜ ዉስጥ የፈጠረዉ አብዮትን ስንመለከት አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ በሀገራችን ያለዉ አስፈላጊነት እጅጉን ጉልህ መሆኑንና በተለይም ደግሞ ለፍትሕ ስርአቱ ውጤታማነትና ቀልጣፋ አገልግሎት፣ ለአገር ሰላምና ግንባታ የሚጫወተዉ ሚና እጅጉን የላቀ መሆኑን የገለፁት ሚኒስትር ዲኤታዉ በዚህ ዘርፍ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ እየሰራቸዉ ያሉ ተቋማዊ ስራዎች ትልቅ መሆናቸዉን ተናግረዋል፡፡

ከሕግና ከፍትሕ ስርአቱ ጋር በተገናኘም የተቀናጀ የወንጀል አስተዳደር ሥርዓትን በቴክኖሎጂ በማስደገፍ የተለያዩ ሲሰተሞችን አበልፅጎ መተግበር ሲቻል ማህበረሰቡ የሚፈልገዉን ሕግ ነክ መረጃና ምክር እንዲሁም ተያያዥ ጉዳዮች ባለበት ሁኖ የሚያገኘበትን ሁኔታዎች በማመቻቸት ጉልበትን፣ ገንዘብንና ጊዜን የሚቆጥብ ከመሆኑም በተጨማሪ የፍትሕ አገልግሎት አሰጣጥ ስርኣትን ሂደትን ቀልጣፋና ተገማች ለማድረግ ሁነኛ መፍትሄ ሊሆን እንደሚችል ያላቸዉን እምነት አፅንኦት ሰጥተዉ ገልፀዋል፡፡

የተቀናጀ የወንጀል አስተዳደር ሥርዓት (CRIMS) ተግባራዊ ማድረግ በዓቃቢያነ ሕግ ላይ ያለዉን በርካታ መረጃዎች በተገቢዉ መንገድ ለመያዝና ስራን የተቀላጠፈ ዘመናዊና በቴክኖሎጂ የተደገፈ ለማድረግ እጅግ ወሳኝ እንደሆነና ይህንኑ ፕሮጀክት በሚመለከት አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ላቀረበዉ አጠቃላይ የፕሮጀክት ገለፃ ምስጋናቸዉን ያቀረቡት ሚኒስትር ዲኤታዉ በተያያዘም በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ እየተሰራ ያለዉ አጠቃላይ ስራ እጅጉን የሚያስደስትና የሚደነቅ መሆኑን በጉብኝታቸው አንስተዋል።

የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ክቡር ዶ/ር ወርቁ ጋቸና በበኩላቸዉ በርካታ የፌዴራል ተቋማት ከአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ጋር በጋራና በትብብር እንደሚሰሩ አስታዉሰዉ ከዚህም ዉስጥ የፍትሕ ዘርፉ አንደኛዉ መሆኑንና የፍትሕ ሚኒስቴርም ከተቋማቸዉ ጋር በመስራቱ በመረጃና በማስረጃ ላይ የተመሰረተ ዉሳኔ ላይ ለመስጠት ሚናዉ የጎላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ቀጥሎም የተቀናጀ የወንጀል መከላከል አስተዳደር ሥርዓት (CRIMS) ምን ማለት እንደሆነ፣ ከዚህ በፊት በፍትሕ ሚኒስቴር ተሞክሮ የነበረዉ ፕሮጀክት የነበሩበት ክፍተቶች፣ እነዚሀን ክፍተቶች ለመሙላት የሚሰሩ ስራዎችና የመፍትሄ እርምጃዎች፣ ፕሮጀክቱ በምን ያክል ጊዜ ዉስጥ እንደሚያልቅና የሚያስፈልግ በጀት በሚመለከት አጠቃላይ የፕሮጀክቱ ገለፃ ስራዉን በሰሩት ባለሙያዎች ቀርቧል፡፡

በዉይይቱ ላይ በፍትሕ ሚኒስቴር በኩል የፍትሕ ሚኒስቴር የተቋም ግንባታና ሪፎርም ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ኤርሚያስ የማነብርሃንን ጨምሮ ሌሎች የስራ ሀላፊዎች የተገኙ ሲሆን በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ በኩል ደግሞ ዋና ዳይሬክተሩን ዶክተር ወርቁ ጋቸናን ጨምሮ ምክትል ዋና ዳይሬክተሮችና ሌሎች የስራ ሀላፊዎች ተሳትፈዋል፡፡

Tagged Under: artificial Artificial intelligence criminal crims decision digital digital transformation dr. ermias yemaneberhan Information technology integrated intelligence Justice Justice Sector Reform Legal technology management records reform sector system Technology transformation
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች

ተመሳሳይ ዜናዎች