በወንጀል ምርመራ፣ በክስ አዘገጃጀት እና የችሎት ክርክር ክህሎትን ለማዳበር የሚያስችል 2ኛ ዙር ስልጠና መሰጠት ተጀመረ

Second Round of Training Begins to Enhance Skills in Criminal Investigation, Case Preparation, and Court Litigation

በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የንቃተ ሕግ ፣ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት በወንጀል ምርመራ፣ በክስ አዘገጃጀት እና የችሎት ክርክር ክህሎትን ለማዳበር የሚያስችል 2ኛ ዙር ሥልጠና በዛሬው ዕለት መሰጠት ጀምሯል፡፡

በሥልጠና መድረኩ ተገኝተው የሥልጠናውን መድረክ የከፈቱት በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ዘርፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ በረከት ማሞ እንዳሉት በ2015 ዓ.ም እና በ2016 ዓ.ም ፍትሕ ሚኒስቴርን ለተቀላቀሉና ለተሾሙ ዐቃቤያነ ሕግ የወንጀል ምርመራ ፣ የክስ አዘገጃጀት እና የችሎት ክርክር ክህሎትን በተመለከተ ተግባር ተኮር ዳዮችን መሠረት ያደረገ እና በተግባር እየተሰራበት ያለ ጉዳይ ላይ ያተኮረ መሆኑን ገልፃዋል፡፡

ሥልጠናው የሰልጣኞችን ተሳትፎ እንደሚፈልግ ያወሱት አቶ በረከት በ2015 ዓ.ም እና በ2016 ዓ.ም በክረምት ወቅት ለሶስት ሳምንት ሲሰጥ የነበረው ሥልጠና በስራ ላይ ምን ውጤት እንዳመጣ የፋይዳ ዳሰሳ ጥናት በንቃተ ሕግ ፣ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት በኩል እንደተሰራና በዚህም ብዙ የሥልጠና ፍላጎቶች እንዳሉና ዛሬ የጀመረው ይህ ሥልጠናም የዚሁ አንድ አካል መሆኑን አውስተዋል፡፡

በሁለት ዓመት የስራ ቆይታ በወንጀል ምርመራ ፣በክስ አዘገጃጀት እና የችሎት ክርክርን አስመልክቶ የተለያዩ ጉዳዮች ሲያጋጥሙ እንደነበሩ ጠቅሰው በተለይ ከዚህ በፊት በነበረው አሠራር ተቋሙን ስንቀላቀል ነባር ዓቃብያነ ሕግ አሰራሮችን እያሳዩን እኛም ግልፅ ያልሆነልንን ጉዳይ እየጠየቅንና በተግባር እያሳዩን በሙያው ብቁ እንድንሆን ትልቅ አስተዋፅኦ አጎናፅፎናል ያሉት አቶ በረከት ሆኖም ግን ባለፉት 2 አመታት እንዲህ ያሉ በርካታ ዕውቀት የሚቀሰምባቸው የልምድ ልውውጦች እየተቀዛቀዙ መምጣታቸውን አውስተው በቀጣይ ሊሻሻል እንደሚገባ በአንክሮ ገልጸዋል፡፡

አያይዘውም ከዚህ በፊት ሥልጠናዎች ተግባር ተኮር ሳይሆኑ በንድፈ-ሀሳብ ላይ የተመረኮዙና ወደ ተግባር ሲገባ ክፍተቶች የሚስተዋሉበት እንደነበረ በዚህም ሥልጠናዎች ውጤታማ እንዳልነበሩ ያወሱት ኃላፊው አሁን ግን ከወንጀል ምርመራ ጀምሮ እስከ ውሳኔ አሰጣጥ ያለውን ሂደት በተግባር የሚታይበት መሆኑን አውስተዋል፡፡የሥልጠናው ተሳታፊዎች በሥልጠናው የሚነሱ ጉዳዮችን መነሻ በማድረግ በቀጣይ በስራ ቦታ ላይ የዕርስ በዕርስ ንግግርና ውይይት በማድረግ ክህሎታቸውን እንዲያሳድጉና ብሎም ለሌሎች ባለሙያዎች ልምድ እንድትሰጡ ሲሉ አሳስበዋል፡፡

ሥልጠናው የወንጀል ምርመራ አጀማመር እና አጠቃላይ ሂደት ፣ዓቃቤ ሕግ በምርመራ መዝገቦች ላይ የሚሰጣቸው ውሳኔዎች ፣ክስ አመሰራረት ፣በክስ አመሰራረት እና ውሳኔ አሰጣጥ አከራካሪ የሆኑ ጉዳዮች፣የክስ አሰማም ስርዓት ፣መክፈቻና መዝጊያ ንግግሮች ፤ የቅጣት አስተያየቶች እና የይግባኝ ስርዓት ላይ ያተኮረ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

ሥልጠናው ለአምስት ተከታታይ ቀናት የሚሰጥ ሲሆን በፍትሕ ሚኒስቴር መካከለኛ አመራሮች የሚሰጥ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

Tagged Under: Criminal Investigation • Legal Training • Prosecution
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች

ተመሳሳይ ዜናዎች