በኢትዮጵያ የፋይናንስ አገልግሎት መድብል ለማዘጋጀት መነሻ የሚሆን የፖሊሲ ጥናት ቀርቦ ውይይት ተካሄደ

Policy Study Discussion Held as a Starting Point for the Development of Financial Services Framework in Ethiopia

በኢትዮጵያ የፋይናንስ አገልግሎት መድብልን ለማዘጋጀት የሚረዳ የፖሊሲ ጥናት ላይ የግብዓት ማሰባሰቢያ ውይይት ተካሄዷል፡፡

በመድብሉ ከተካተቱት ሁለት መሠረታዊ ጉዳዮች መካከል አንዱ በሆነው የባንክ ስራ ሕግ ማሻሻያ ላይ የተደረገውን የፖሊሲ ጥናት ያቀረቡት ፕሮፌሰር ቤንጃሚን ጌቫ ሲሆኑ በበየነ መረብ ባቀረቡት ገለጻቸው በማሻሻያ ህጉ ውስጥ ሊካተቱ ወይም በጥልቀት ሊመረመሩ ይገባሉ ያሏቸውን መሠረታዊ የባንክ ስራ ፍሬ ነገሮችን አንስተው አብራርተዋል፡፡

በገለጻቸው የመድብሉ ስያሜ ምን መሆን አለበት፤ የባንክ ስራ ህጉ ተፈጻሚነት ወይም ስፋቱ እስከ ምን ድረስ መሆን አለበት በሚሉ እና በሌሎች መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገው ገለጻ ሰጥተዋል፡ የባንክ አገልግሎት አይነቶች፣ ገንዘብ ማስተላለፊያ መንገዶች፣ የተቀማጭ ገንዘብ ደኅንነት፣ ዲጂታል ከረንሲ እና ሌሎች ዝርዝር በጥናቱ የተቀመጡ ጉዳዮች የሕግ ማዕቀፍ ወጥቶላቸው እንዴት በስራ ላይ መዋል እንደሚችሉ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ፕሮፌሰር ቤንጃሚን ከባንክ ስራ ጋር በተያያዘ የሌሎች ሀገራትን ልምዶች በስፋት ማካፈልም ችለዋል፡፡

የቀረበውን ሰነድ አስመልቶ ማብራሪያ የሰጡት የኢፌዲሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ የባንክ እና ኢንሹራንስ ህጉ በሀገራችን ከ60 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ በመሆኑ ለዘመኑ የሚመጥን እና አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ሊያሰራ የሚችል ሕግ ሊኖር ስለሚገባ ጥናት መደረጉን ገልጸው በጥናቱ ላይ ባለድርሻ አካላት እና የንግዱ ማኅበረሰብ መሳተፋቸውን ጠቁመዋል፡፡

አክለውም በቀረበው ጥናታዊ ጽሁፍ ላይ የውይይት ሀሳብ ያቀረቡ ሲሆን የጥናት ሀሳቡ ወደ ረቂቅ ሕግ ከመቀየሩ በፊት የሚሰጠው ግብዓት ወሳኝ በመሆኑ ተገቢው ትኩረት ተሰጥቶት ውይይት ሊደረግበት ይገባል ብለዋል፡፡ አክለውም በመድረኩ ከተገኙ ተሳታፊዎች በተጨማሪ በጉዳዩ ላይ ያገባኛል ያለ ሁሉ የሚሰጠው ግብዓት በቀጣይ የሚረቀቀውን መድብል ምልዑ ያደርገዋል ብለዋል፡፡

አቶ በቃሉ ጥላሁን በበኩላቸው የኢንሹራንስ ሕግ ማሻሻያ ወሰን እና ከፖሊሲ ጋር የሚገናኙ መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ በማሻሻያ ሂደቱ ሊሻሻሉ ስለሚገባቸው እና የማይገባቸውን ጉዳዮች በተመለከተ የፖሊሲ ጥናት ግኝቱን መሠረታዊ ጉዳዮች በዝርዝር ያቀረቡ ሲሆን በቀረበው ሰነድ ላይ የኢፌዲሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አለም አንተ አግደው የውይይት መድረኩን መርተዋል፡፡ ሚኒስትር ዴዔታው የጥናት ሰነዱ ለሁሉም እንዲደርስ የሚደረግ መሆኑን በማስታወስ የሚመጡ አስተያየቶችን ተቀብሎ ለማስተናገድ ዝግጁነቱ እንዳለ አረጋግጠዋል፡፡በውይይቱ የተገኙ የውይይቱ ተሳታፊዎችም በቀረቡት የባንክ ስራ እና ኢንሹራንስ ፖሊሲ ጥናት ሰነዶች ላይ አስተያየታቸውን ሰጥተው ውይይት ተካሂዷል፡፡ በውይይቱ የመድብሉ ስያሜ እና የተፈጻሚነት ወሰን በአጀንዳነት ተይዘው በስፋት ውይይት ከተደረጉባቸው ጉዳዮች መካከል ዋነኞቹ ነበሩ፡፡

Tagged Under: alema ante amendment bank regulation Banking dr. gideon timotheos financial financial inclusion financial sector reform Financial Services framework Insurance law Legal Reform Policy Policy discussion policy review professor Regulatory Framework Services Stakeholder Consultation study
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች

ተመሳሳይ ዜናዎች

No data was found