በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የተደራጁና ድንበር ተሸጋሪ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ ናይጀሪያዊ ታንዛኒያዊ እና ፖርቹጋላዊ ዜግነት ያለቸው ግለሰቦቦች በፈጸሙት አደገኛ ዕጾችን ማዘዋወር ወንጀል በ3 የተለያዩ መዝገቦች በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ወንጀል ችሎት ክስ መስርቶ የክርክር ሂደቱን ሲያካሂድ ቆይቷል፡፡
ተከሳሾች የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ525 (1(ለ)) ስር የተመለከተውን ድንጋጌ በመተላለፈድ ነው የወንጀል ድርጊቱን የፈጸሙት ፡፡
የዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገቦች ዋቢ አድርገን ባገኘነው መረጃ ኢንየቡቺ ጁዲ ናዲ የተባለውና የናይጀሪያዊ ዜግነት ያለው ተከሳሽ እጾችን የማምረት፣የመስራ፣የማዛወር ወይም የመጠቀም ልዩ ፈቃድ ሳይኖረው ጥቅምት 29/2015 ዓ.ም ከምሽ 1፡30 ሰዓት ሲሆን መነሻውን ከብራዚል ሳፖሎ ከተማ በማድረግ ወደ ጊኒ ኮናክሪ ከተማ ለመጓዝ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦሌ አለማቀፍ አየር ማረፊያ ለትራንዚት ባረፈበት ወቅት በተደረገ የኤክስሬይ ፍተሻ 12 እሽግ የሆነና ግራሙ 8863.11 ግራም የሚመዝን የኮኬይን እጽ በሻንጣው ውስጥ ደብቆ ይዞ ሲጓዝ የተገኘ በመሆኑ በፈጸመው አደገኛ እጾችን ማዛወር ወንጀል ዐቃቤ ሕግ ክስ የመሰረተበት ሲሆን፤ ተከሳሽ ወንጀሉን መፈጸሙንም በማመኑ ፍርድ ቤቱ ማስረጃ መስማት ሳያስፈልግ የጥፋተኝነት ፍርድ ሰጥቶ ታህሳስ 19 ቀን 2015 ዓ.ም ባስቻለው ችሎት በ11 ዓመት ጽኑ እስራትና በ20ሺ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ሲል ወስኖበታል፡፡
በተመሳሳይም ሶልማን ራጃቡ መውማ የተባለው የታንዛኒያ ዜግነት ያለው ተከሳሽ ከብራዚል ሀገር ሳፖሎ ከተማ በመነሳት የኢትዮጵያ አየር መንገድ በመጠቀም ወደ ቡሩንዲ ቡጅምቡራ ከተማ ለመሄድ ጥቅምት 19 ቀን 2015 ዓ.ም ከምሽቱ 2፡00 ሰዓት ሲሆን ቦሌ አለማቀፍ አየር ማረፊያ ለትራንዚት ባረፈበት ወቅት በሻንጣው ውስጥ አጠራጣሪ ነገር በመታየቱ በተደረገ ፍተሻ ሰባት እሽግ የሆነ እና ግራሙ 6336 የሚመዝን የኮኬይን አደገኛ ዕጽ የተገኘበት በመሆኑ በፈጸመው አደገኛ እጾችን ማዛወር ወንጀል ክስ ተመስርቶበት ወንጀሉን መፈጸሙን በማመኑ ፍርድ ቤቱ ጥፋተኛ ነህ በማለት ታህሳስ 19 ቀን 2015 ዓ.ም ባስቻለው ችሎት በ10 ዓመት ጽኑ እስራትና በ10ሺ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ሲል ወስኖበታል፡፡
በመጨረሻ የዜና ትየባችንም ማርኮ አሌክሳንደር ዳሲላቫ የተባለውና የፖርቹጋል ዜግነት ያለው ተከሳሽ ከብራዚል ሀገር ሳፖሎ ከተማ በመነሳት የኢትዮጵያ አየር መንገድ በመጠቀምዳ ሞዛምቢክ ማፑቶ ከተማ ለመሄድ ጥቅምት 21ቀን 2015 ዓ.ም ከምሽቱ 2፡20 ሰዓት ሲሆን ቦሌ አለማቀፍ አየር ማረፊያ ለትራንዚት ባረፈበት ወቅት በተደረገ ፍተሻ በሻንጣው ውስጥ ደብቆ 53 በባትሪ መልክ የተዘጋጀ እና ግራሙ 11840.4 የሚመዝን የኮኬይን አደገኛ ዕጽ የተገኘበት በመሆኑ ክስ ተመስርቶበት ወንጀሉን መፈጸሙን በማመኑ ፍርድ ቤቱ ጥፋተኛ ነህ ያለው ሲሆን ታህሳስ 19 ቀን 2015 ዓ.ም ባስቻለው ችሎት በ11 ዓመት ጽኑ እስራትና በ30ሺ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ሲል ወስኖበታል፡፡