የፍትህ ሚኒስቴር በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገራት ተሳትፎ ባደረገባቸው የፍትሐብሄር ጉዳዮች የህዝብ እና የመንግስትን የፍትሐብሔር ጥቅም በተሻለ ማስከበር መቻሉ ተገለጸ

Ministry of Justice's Participation in Domestic and International Civil Cases Effectively Safeguarded Public and Government Civil Interests

በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የፍትሐብሄር ፍትሕ አስተዳደር ዳሬክቶሬት ጄነራል በ2017 የመጀመሪያው ሩብ ዓመት የተከናወኑ ተግባራትን አስመልክቶ ገለጻ ያደረጉት ዳይሬክተር ጄነራሉ አቶ ሄኖክ ተስፋዬ የሕዝብ እና የመንግሥትን የፍትሐብሄር ጥቅም በማስጠበቅ ረገድ ከ 5 ቢሊየን ብር፣ ከ46 ሚሊዮን ዩሮ እና ከ 246 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ የገንዘብ መጠን በያዙ የተለያዩ የፍትሐብሔር ጉዳዮች ዙሪያ የፍትሕ ሚኒስቴር ተሳትፎ አድርጓል ብለዋል።

የፍርድ ማስፈጸምን ጨምሮ በፍትሐብሄር በቀጥታ ክስ እና በይግባኝ ደረጃ በሩብ አመቱ በታዩ 213 የክርክር መዛግብት ላይ ተሳትፎ መደረጉን ገልጸው በ34 መዛግብት ላይ ውሳኔ ተሰጥቶ ከእነዚህ መካከል በ31 መዛግብት ላይ በመርታት የሕዝብና የመንግሥትን ጥቅም በተሻለ ማስከበር መቻሉን ገልጸዋል።

በሌሎች የፍትሐብሄር አገልግሎቶችም እንዲሁ በሩብ አመቱ የተሻለ አፈጻጸም መመዝገቡን

አቶ ሔኖክ ባደረጉት ገለጻ አስታውቀው በተለይ የመንግሥት ተቋማት እርስ በእርስም ሆነ ከሌሎች ድርጅቶች/ግለሰቦች ጋር በነበራቸው የፍትሐብሄር መስተጋብር የተፈጠሩ አለመግባባቶችን ከፍርድ ቤት ውጭ ባለ አማራጭ በመፍታት አላስፈላጊ ከሆነ የጊዜ እና የገንዘብ ብክነት ተቋማቱን መታደግ ተችሏል ብለዋል። በሩብ አመቱ በአማራጭ የሙግት መፍቻ መንገድ ከታዩት 9 ጉዳዮች መካከል 6ቱን በስኬት ማጠናቀቅ የተቻለ ሲሆን የተቀሩት 3 መዛግብት በሂደት ላይ ይገኛሉ።

አቶ ሔኖክ አክለውም የመንግሥት ተቋማት እርስ በርስ የሚገቡባቸውን የፍትሐብሄር አለመግባባት ፍትሕ ሚኒስቴር ተመልክቶ ውሳኔ እንዲሰጥበት በአዋጅ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት በሩብ አመቱ አመርቂ ውጤት መመዝገቡን አውስተዋል። ይህንኑ ሥልጣን ግልጽነት እና ተጠያቂነት ባለው መንገድ ተግባራዊ ማድረግ እንዲያስችል መመሪያ ተዘጋጅቶ እንዲጸድቅ መደረጉን እና ይህንኑ ተከትሎ በተለያዩ የመንግሥት ተቋማት መካከል የተፈጠሩ የፍትሐብሄር አለመግባባቶችን የያዙ 12 ጉዳዮች በሩብ አመቱ ታይተው በ03 መዛግብት ላይ ውሳኔ መስጠት ተችሏል ብለዋል።

የገንዘብ አቅም የሌላቸው ዜጎች ያቀረቧቸውን ጨምሮ ከተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ለቀረቡ 448 የሕግ ድጋፍ ጥያቄዎች ሙሉ በሙሉ ምላሽ መስጠት የተቻለ ሲሆን ድጋፍ ከተደረገላቸው መካከል 290 ሴቶች፣ 12 አካል ጉዳተኞች፣ 11 አረጋውያን እና ሌሎች አካላትም ይገኙበታል ብለዋል። የመንግሥት ተቋማት የሚዋዋሏቸው ከፍተኛ ገንዘብ የያዙ ውሎች የሕዝብና የመንግሥትን ጥቅም ያስከበሩ እንዲሆኑ ከማድረግ አንጻርም በሩብ አመቱ ለ08 የተለያዩ ተቋማት የውል ሰነዶች ምርመራ እና የረቂቅ ዝግጅት ማከናወን መቻሉን አቶ ሔኖክ አክለው ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ሀገራችን በተከሰሰችባቸው በተለያየ ደረጃ ላይ በሚገኙ 04 አለማቀፍ የኢንቨስትመንት የግልግል ዳኝነት ጉዳዮች ላይ ሀገራችንን በመወከል ተሳትፎ መደረጉን አቶ ሔኖክ ገልጸዋል።

የግልግል ዳኝነት አሠራር በሀገራችን እንዲስፋፋ ለማድረግ እና ሀገራችንን የግልግል ዳኝነት ማእከል ለማድረግ በማለም እንደተቋም እቅድ ተይዞ ሰፊ ስራ እየተከናወነ መሆኑን የገለጹት አቶ ሔኖክ በዚሁ ሩብ ዓመት ከአጋር አካላት ጋር በመቀናጀት የ East Africa International Arbitration Conference/EAIAC/ በአዲስ አበባ በተሳካ ሁኔታ እንዲካሄድ ማድረግ መቻሉንም አክለዋል።

በሩብ አመቱ የተገኘውን ውጤት በማሻሻል እና አጠናክሮ በማስቀጠል በተያዘው በጀት ዓመት የሕዝብና የመንግሥት የፍትሐ ብሄር መብትና ጥቅም በተሻለ እንዲከበር ከፍተኛ ጥረት የሚደረግ መሆኑን ገልጸው እስካሁን ለተመዘገበው አመርቂ ውጤት አስተዋጾ ለነበራቸው የተቋሙ አመራሮች እና ሠራተኞች፣ የሌሎች ተቋማት አመራሮች እና የሕግ ባለሞያዎቻቸው እንዲሁም በግሉ ዘርፍ ለሚሰሩ ጠበቆችና ሌሎች ድርጅቶች ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

Relevant Departments and People
Tagged Under: Arbitration Civil law Legal representation Public interest
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች