ፍትህ ሚኒስቴር የታክስና የጉሙሩክ ወንጀሎችን ለመከላከልና አጥፊዎችን በህግ ተጠያቂ ለማድረግ የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ

Ministry of Justice Signs Agreement to Combat Tax and Customs Crimes

ፍትሕ ሚኒስቴር የታክስና የጉሙሩክ ወንጀሎችን ለመከላከልና አጥፊዎችን በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የታክስና የጉሙሩክ ወንጀሎችን ለመከላከልና አጥፊዎችን በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ የሚያስችለዉን ስምምነት ከጉሙሩክ ኮሚሽን፣ከገቢዎች ሚኒስቴርና ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በዛሬዉ እለት ሐምሌ ዐ1 ቀን 2ዐ14 ዓ.ም ተፈራርሟል፡፡

ስምምነቱን የፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ፣ የጉሙሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቃበታ፣ የገቢዎች ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ተስፋዬ ቱሉ እና የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ተፈራርመዋል፡፡

በስምምነቱ ወቅት የፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ ዉጤታማ የታክስ አስተዳደር ለአንድ አገር እድገት ትልቅ ፋይዳ እንዳለዉና ገቢ ሰብስቦና በጀት በጅቶ ለልማት ማዋል የሚቻለዉ ገቢ ሲኖር መሆኑን በመግለፅ ይህን ገቢ ለማስገኘትም ግብራቸዉን በታማኝነትና በሀቀኝነት የሚከፍሉና ሕግ የሚያከብሩ አካላት እንዳሉ ሁሉ የግብር መከፍል ግዴታቸዉን በአግባቡ የማይወጡ አካላትን ለሕግ ማቅረብ አስፈላጊ ጉዳይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

አያይዘዉም ይህ እዉን እንዲሆን በዛሬዉ እለት የተደረገዉ ስምምነት ትልቅ ፋይዳ እንዳለዉ በመጠቆም ስራዎችን በተናበበና በተቀናጀ መልኩ መሥራት ከተቻለ ዉጤታማ ስራ መሥራት እንደሚቻል ያላቸዉን እምነት በመግለፅ የስምምነት ሰነዱ በጥናት ላይ ተመስርቶ እንደተዘጋጀና ለዛሬዉ እለት እንዲደርስ ላደረጉ የተቋሙ የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታና የኢኮኖሚ ወንጀሎች ዳይሬክቶሬት ላበረከቱት አስተዋፅ ምስጋናቸዉን አቅርበዋል፡፡

ቀጥሎም ስምምነቱን የተፈራረሙት የየተቋማቱ አመራሮች መልእክት ያስተላለፉ ሲሆን የጉሙሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቃበታ በተለይም ከለዉጡ ወዲህ በኢኮኖሚ ሴክተሩ ላይ ተጋርጦ የነበረን አደጋ ለመቀልበስ የፍትሕና የፀጥታ አካላት በጋራ በሰሩት ስራ ሊደርሱ የሚችሉ ከባባድ አደጋዎችን ማስቀረት መቻሉን በመጠቆም ወደ ፊትም የበለጠ ተቀናጅቶ በመሥራት የተሻለ ዉጤት ለማምጣት ስምምነቱ ትልቅ ፋይዳ እንዳለዉ ያላቸዉን እምነት ገልፀዋል፡፡

የስምምነቱ ዋና ዓላማም የታክስና የጉሙሩክ ሕግ እንዲከበር በማድረግ የታክስ አስተዳደሩን የበለጠ ዉጤታማ በማድረግ ኢኮኖሚዉ የሚያመነጨዉን ገቢ በብቃት መሰብሰብ እና ኮንትሮባንድንና ህገ ወጥ ንግድን መቆጣጠር፣ፈጣንና የተደራጀ የመረጃ ቅብብሎሽ ሥርዓት እንዲፈጠርና እንዲጠናከር በማድረግ የሕግ ተገዥነትን ማጠናከና የተቋማቱን የሕግ ማስከበርና የሕግ ማስፈፀም አቅም ማጠናከር መሆኑ ተገልጧል፡፡

Tagged Under: Legal Accountability Tax Evasion
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች