ከኢኮኖሚ እንዲሁም ከታክስና ጉሙርክ ወንጀሎች ጋር በተያያዘ ባለፉት ስድስት ወራት በ1,380 መዝገቦች ላይ ክስ መመስረቱ ተገለጸ

Charges Filed in 1380 Cases Related to Economic, Tax, and Customs Crimes in the Past Six Months

በዚህ የክስ ሂደትም በ276 መዝገቦች 497 ተከሳሾች እንደ ክስ አመሰራረት ሂደቱ ወንጀሉን በመፈጸማቸው በፍርድ ቤት የጥፋተኝነት ፍርድ እንደተላለፈባቸው የተናገሩት አቶ ፍርዴ በ15 መዝገቦች 25 ተከሳሾች በነጻ ተሰናብተው 1100 መዝገቦች በክርክር ሂደት ላይ መሆናቸውን አክለዋል፡፡

የአኮኖሚ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት በተቋሙ ብሎም በዘርፉ ከተሰጡት ተግባርና ኃላፊነት አኳያ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመከታተል ወንጀል እንዳይፈፀም የመከላከል፣ ተፈጽሞ ሲገኝም ተገቢውን ምርመራ በማድረግና ክስ በመመስረት አጥፊዎች በሕግ እንዲጠየቁ እና ከድርጊታቸው እንዲማሩ እንዲሁም ሌሎች ተመሳሳይ ወንጀል የመፈፀም ሃሳብ ያላቸው ግለሰቦችም እንዲጠነቀቁ የማድረግ ኃላፊነት እንደተጣለበት ገልጸዋል፡፡ ዳይሬክተሩ አያይዘውም በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚፈጠር የኢኮኖሚ አሻጥርን በመከላከል እንደዚሁም የንግዱ ማኅበረሰብ የሸማቹን መብት ያከበረ የንግድ እንቅስቃሴ እንዲያደርግ ይህንን ተላልፎ ሲገኝም በሕግ ተጠያቂ የማድረግ ስራ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

በተለይም በዚህ ወቅት የሚታየውን ገበያን በበላይነት በመቆጣጠር የገበያ እጥረት የመፍጠር በአስመጭዎቻና በአከፋፋይ ነጋዴዎች ላይ የሚታዩ ችግሮች፣ የውጭ ምንዛሬን በህገ-ወጥ መንገድ እንዲዘዋወር በማድረግ የውጭ ምንዛሬ እጥረት በመፍጠር በሀገር ኢኮኖሚ ላይ እየተፈፀመ ያለው ወንጀል፤ መደበኛ የግብይት ሥርአቱን ባለመከተል በኮንተሮባንድ የሚደረጉ የንግድ እንቅስቃሴዎች እና ሌሎች ተመሳሳይ ጉዳዮች ላይ ልዩ ትኩረት በመስጠት ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ተፈጽመው የተገኙ ወንጀሎችን ከፌዴራልና ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በመተባበር የምርመራ ስራዎችን በመሥራት፤ አጥፊዎችን ወደ ሕግ የማቅረብ ስራውን እየሰራ እንደሚገኝ አውስተዋል፡፡ አክለውም ከገቢዎች ሚኒስቴር እና ከጉምሩክ ኮሚሽን ጋር በመቀናጀት ግብረ ኃይል በማቋቋም እና በክልል ቅርንጫፎችን በመክፈት ጭምር ስራዎችን በልዩ ክትትል ለመሥራት ጥረት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡

በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን በመከላከሉ ረገድም ከገቢዎች ሚኒስቴር፤ ከጉምሩክ ኮሚሽን፣ ከአዲስ አበባ እና ከፌደራል ፖሊስ ጋር ስራዎችን በጋራ ለመሥራት ስለሚቻልበት ሁኔታ በተለይም በክልል ያሉ የኢኮኖሚ ወንጀል ጉዳዮችን መከታተል በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ምክክር ተደርጎ ፍትሕ ሚኒስቴር ከተቋማቱ ጋር የመግባቢያ ስምምንት ሰነድ መፈራረሙን አቶ ፍርዴ ተናግረዋል፡፡ በተለይም የጉሙርክ ወንጀሎች በብዛት ይፈጸምባቸዋል በሚባሉት በአዳማ፣ በባህርዳር፣ በኮምቦልቻ፣ በጅግጅጋ እና በጎንደረር ከተሞች በዘርፉ የሚሰሩ ዐቃብያነ ሕግን በመመደብ እና የቅርንጫፍ ጽ/ቤቶችን በመከፈት ከጎንደር እና ጅግጅጋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ውጭ በሌሎቹ ቅርንጫፎች ወደ ስራ መግባቱን የገለጹት ዳይሬክተሩ የ6ወራት አፈጻጸማቸውን በተመለከተም እንደሚከተለው አብራርተዋል፡፡

በኢኮኖሚ ወንጀል ጉዳዮች የአዳማ ቅርንጫፍ ከታክስና ጉምሩክ ጋር ተያያዞ 46 የምርመራ መዝገቦች ቀርበው በ41 ላይ ዐቃቤ ሕግ ክስ መስርቶ በክርክር ሂደት ላይ እንደሚገኝ አውስተዋል፡፡

የባህርዳር ቅርንጫፍን በተመለከተም ከክልሉ የተለያዩ ዞኖች 26 መዛግብትን ዐቃብያነ ህጉ የተረከቡ ሲሆን አዲስ የቀረቡ 14 መዝገቦችን ጨምሮ በ40ዎቹ ላይ ክስ ተመስርቶ በ4 መዛግብት ላይ ዐቃቤ ሕግ በፍርድ ቤት ጥፋተኛ ያስደረገ ሲሆን ቀሪ 36 መዝገቦችም በክርክር ሂደት ላይ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

ከኮምቦልቻ ቅርንጫፍ ጋር በተያያዘም በኢኮኖሚ ወንጀሎች ዙሪያ በ16 መዝገቦች ላይ ክስ ተመስርቶ ፍርድ ቤቱ በ1 መዝገብ ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ ሰጥቶ 15 መዛግብት በክርክር ላይ መሆናቸውን በመግለጽ እነዚህ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ወደ ስራ ከገቡ ከ4 ወራት ያልበለጣቸው ቢሆንም ምርመራን በመምራትም ይሁን በፍርድ ቤት ክርክር አበረታች ውጤቶች እያስመዘገቡ እንደሆነ በማብራሪያቸው ላይ አክለዋል፡፡

በመጨረሻም የኢኮኖሚ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት በቀጣዮቹ 6 ወራት የሀገር ኢኮኖሚን በእጅጉ በሚጎዱ ሕገ-ወጥ የማዕድን ግብይትና ዝውውር፣ በወጭም ይሁን ገቢ ኮንትሮባንድ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን እና የሸማቹን መብት በሚጎዱ ሌሎች የኢኮኖሚ ወንጀል ጉዳዮች ዙሪያ በትኩረት እንደሚሰራ ያወሱት ዳይሬክተሩ በተቀመጡት የትኩረት አቅጣጫዎች መሠረትም ለላቀ አፈጻጸም በትኩረት እንደሚሰራ አመላክተዋል፡፡

Tagged Under: acquittal adama addis ababa police commission bahir dar Contraband conviction court cases Crimes customs customs commission Economic Economic Crimes Federal police financial Financial Crimes Fraud gondar Investigation jigjiga Justice Ministry kombolcha market manipulation Price Gouging Prosecution revenue ministry Tax tax crimes
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች