የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የፍትሕ ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሐና አርአያስላሴ የተመራ ልዑክ ቡድን በአዲስ አበባ የሚገኙ የፍትሕ ተቋማት የሥራ እንቅስቃሴ ጎብኝቷል። በመርሃ-ግብሩ በከተማ አስተዳደሩ ፍትሕ ቢሮ በኩል የፍትሕ አገልግሎትን ለማሻሻል እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች፣ በወንጀል ነክ ነገር ውስጥ ገብተው የተገኙ ሕፃናት ማቆያ ተሃድሶ ማዕከል እና በአዲስ ከተማ የማኅበረሰብ ፍትሕ አገልግሎት መስጫ ማዕከል እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች ተጎብኝተዋል።
የልዑክ ቡድኑ በመጀመሪያ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በወንጀል ነክ ነገር ውስጥ ገብተው የተገኙ ሕፃናት ማቆያ ተሃድሶ ማዕከልን ጎብኝተዋል። በጉብኝቱ ወቅት የመልሶ ማቋቋም መርሃ ግብሮችን፣ የመልሶ ማቋቋም ጥረቶችን እና የህጻናት ጥበቃ እርምጃዎችን ማየት እና መገምገም የቻለ ሲሆን፤ ከማዕከሉ አስተዳደር እና አገልግሎት ሰጪዎች ጋርም እያጋጠሙ ባሉት ተግዳራቶች እና ፍትሕ ሚኒስቴር እገዛ በሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ዙርያ ውይይት ተደርጓል።
ቡድኑ ከሥራ ጉብኝቱን በመቀጠል የአዲስ አበባ የፍትሕ ቢሮ የትራንስፎርሜሽን እቅድ በመተግበር ረገድ ያለውን እድገት ገምግሟል። የፍትሕ አገልግሎትን በቴክኖሎጂ ለመደገፍ እየተደረጉ ያሉ ጥረጦችን፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻያ ሥራዎችን፣ቅልጥፍናን፣ ግልጽነትን እና የፍትሕ ተደራሽነትን ለማሳደግ የታቀዱ ቀጣይ ተነሳሽነቶች ዙሪያ ውይይት ተካሂዷል። በውይይት ወቅትም ክብርት ሚኒስትር ቢሮው ላደረገው የማሻሻያ ጥረቶች አመስግነው በቀጣይ ቅድሚያ የሚሰጣቸው የፍትሕ አገልግሎት ማሻሻያ ሥራዎች ላይ ትኩረት በማድረግ በውጤት ላይ ያተኮረ ትግበራ አስፈላጊ መሆኑን አፅንዖት ሰጥተዋል።
በተጨማሪም በአዲስ ከተማ የማኅበረሰብ ፍትሕ አገልግሎት መስጫ ማዕከል ትግበራ እና በማዕከሉ ከሚያገለግሉ የሃገር ሽማግሎዎች ጋር ውይይት ተካሂዷል። ማኀበረሰብን መሰረት ያደረገ የፍትሕ አገልግሎቶችን በማጠናከር ከመደበኛ ፍትሕ አካላት ጫና ለመቀነስ እየተደረገ ያለው ጥረት በጎ ጅምር ላይ መሆኑን፣ ማህበራዊ ትስስርን በማሳደግ እና በአካባቢ ደረጃ የፍትሕ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ እየተደረጉ ያሉት ጥረቶች ጥሩ መሆናቸውን በውይይቱ ወቅት መረጋገጥ ተችሏል።
ጉብኝቱ በፍትሕ ሚኒስቴር እና በከተማ መስተዳደሩ የፍትሕ ተቋማት መካከል ያለውን ቅንጅት ለማጠናከር፣ ስኬታማ የማህበረሰብ ፍትሕ ሞዴሎችን በመላው አዲስ አበባ ለማስፋት በጋራ ለመስራት በመግባባት ተጠናቋል።