አለማቀፋዊና አህጉራዊ ስምምነቶች ሲፈረሙ ሊፈፀሙ ከሚገቡ ግዴታዎች ውስጥ አንደኛው የአፈፃፀም ሪፓርቶችን ማቅረብ መሆኑ ተመላከተ

It Was Indicated That Submitting Implementation Reports is One of the Obligations to be Fulfilled When International and Regional Agreements are Signed

በፍትሕ ሚኒስቴር አስተባባሪነት የአለም አቀፉ የኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊ እና ባህላዊ መብቶች ቃል ኪዳን ስምምነትን አስመልክቶ በተዘጋጀው 4ተኛው እና 5ኛው የተጠቃለለ ወቅታዊ አገራዊ አፈፃፀም ረቂቅ ሪፓርት ላይ ባለድርሻ አካላት ከሆኑ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት የተውጣጡ ተሳታፊዎች በተገኙበት ግንቦት 21/2017 ዓ.ም በአዳማ ከተማ ውይይት ተካሂዷል።

ሀገራችን ሰብዓዊ መብቶች በህገ-መንግስቱ እውቅና እንዲያገኙ ከማድረግ ባለፈ በተለይም ባሁኑ ወቅት የሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶችን ማረጋገጥ፣ ማክበርና ማስከበር ለሀገራችን እድገትና ሰላም ወሳኝ መሆኑን በማመን ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ እንደሚገኝ የገለፁት በፍትሕ ሚኒስቴር የመንግሥት ሕግና ፍትሕ አገልግሎት ሚኒስትር ዲኤታ ፅ/ቤት ሃላፊ አቶ እያሱ ቀለሜ፣የእነዚህ መብቶች አከባበር ወደተሻለ ደረጃ ለማድረስ ከተወሰዱ ርምጃዎች ውስጥም ዓለም ዓቀፍና አህጉራዊ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶች አባል መሆንና ተግባራዊ ማድረግ አንደኛው መሆኑን ገልፀዋል።

እነዚህ ስምምነቶች በአባል አገራት ላይ ሁለት ግዴታዎችን የሚጥሉ መሆኑን ያስታወሱት ሃላፊው የመብቶቹን አከባበር ለማሳደግ በስምምነቶቹ ላይ የተቀመጡትን ተግባራት መፈፀም አንደኛው ግዴታ ሲሆን የሰብዓዊ መብቶችን አፈፃፀም ማሻሻል እና የስምምነቶችን የአፈፃፀም ደረጃ የሚገልፅ ሪፓርት አዘጋጅቶ ማቅረብ ደግሞ ሌላኛው መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም መሠረት ኢትዮጵያ ከዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶች መካከል አንዱ የሆነው የአለም አቀፉ የኢኮኖሚ፣ማኅበራዊ እና የባህል ስምምነትን እ.ኤ.አ በ1993 አፅድቃ የመነሻ፣ሁለተኛና ሶስተኛ ወቅታዊ የአፈፃፀም ሪፓርት እ.ኤ.አ በ2009 ያቀረበች ሲሆን አራተኛ እና አምስተኛውን ወቅታዊ ሪፓርት መነሻ ሪፓርት መዘጋጀቱም ተጠቁሟል።

ሪፓርቱ ከአስር ዓመት በላይ የተከናወኑ ተግባራትን የሚያጠቃልል እና በመብቶቹ ዙሪያ በርካታ ውጤቶች የተመዘገበ መሆኑን የሚያሳይ ሲሆን፣ በሌላ በኩል መረጃዎችን አደራጅቶ በማቅረብ ረገድ ባለው ክፍተት ምክንያት ብዙ ጉዳዩችን ማካተት ያልተቻለበት ሁኔታ በመፈጠሩ ይህን ክፍተት ለመሙላት የባለድርሻ አካላት የውይይት መድረኩ መዘጋጀቱ በመድረኩ ተጠቁሟል።

በማስከተልም ረቂቅ ሪፓርቱን አስመልክቶ ማብራሪያ በፍትሕ ሚኒስቴር በሕግ ጉዳዮች ዓለም አቀፍ ትብብር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ የሱፍ ጀማው አማካኝነት የቀረበ ሲሆን፣ ቀጥሎም አጠቃላይ አገራዊ ሪፓርቱ ላይ በየዘርፉ በመሆን የቡድን ውይይት ተካሂዷል።

በመድረኩ ረቂቅ ሪፖርቱን ላዘጋጁ ባለሙያዎች፣ስራውን ለደገፉ አካላት በተለይም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እና የተ.መ.ድ የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር የምስራቅ አፍሪካ ጽ/ቤት እንዲሁም መድረኩን በማዘጋጀት ሂደት ትብብር ላደረገው ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች ህብረት ላደረጉት ድጋፍ ምስጋና ቀርቧል፡፡

Tagged Under: adama • agreements • civil and political rights • cultural • Economic • human • Implementation • international • international human rights treaties • National • obligations • periodic reporting • Regional • report drafting • reporting • reporting requirements • reports • requirements • Rights • social • stakeholder consultations • treaties
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች