የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሐና አርዓያስላሴ የሲንጋፖር ሪፐብሊክ የሕግሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ኤድዊን ቶንግ እና የልዑክ ቡድናቸውንጋር በሕግ ነክ ሁለትዮሽ የትብብር ጉዳዮች ዙሪያ ሚያዝያ 20 ቀን 2018 ዓ.ም ውይይት አድርገዋል፡፡
ኢትዮጵያ እና ሲንጋፖር ሪፐብሊክ በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚያዊና ዲሞክራሲያዊ የሁለትዮሽ ጉዳዮች ዙሪያ ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረ ግንኙነት ያላቸው መሆኑን ያወሱት ክብርት ወ/ሮ ሐና አርዓያስላሴ፣ ሲንጋፖር በተለያዩ ጉዳዮች በተለይም በግልግል ዳኝነት ማዕከልነት ረገድ የተሻሉ ተሞክሮዎች ያሏት በመሆኑኢትዮጵያ ተሞክሮዎችን ማግኘት እንደምትፈልግ አንስተው በምስራቅ አፍሪካ የመጀመሪያ የሆነ ኤንባሲዋን በአዲስ አበባ ላይ መክፈቷ እንዲሁ ግንኘነቱን የበለጠ ለማጠናከር ዕድሉን እንደሚከፍት ገልፀዋል፡፡
ክቡር ኤድዊን ቶንግ በበኩላቸው በሁለቱ አገራት መካከል የእርስ በርስ ግንኙነቱን የማጠናከር ፍላጎት መኖሩ የሕዝብ ለህዝብ ግንኘነቱን የበለጠ የሚያስተሳስረው መሆኑን አንስተው፤ ኢትዮጵያ እና ሲንጋፖር ያሏቸው ሕብረ ብሔራዊነት፣ የባህልና ሐይማኖቶች ብዝሀነት የሚያመሳስላቸው በመሆኑ የስነልቦና ቅርበትን የሚፈጥር መሆኑን ገልፀው፤ ሲንጋፖር ከማህበራዊ ሚድያ ጋር የተያያዙ ወንጀሎችና በእርቅና ሽምግላና የማስማማት ጉዳዮች ላይ ጥሩ የሚባሉ ተግባራትን ያከናወነች በመሆኑ በዚህ ዙሪያ ተሞክሮን የመለዋወጥ ፍላጎት እንዳለት ገልጸዋል፡፡
ከልዑክ ቡድኑ ጋር ተደረገ የጋራ ውይይት ማጠቃለያ ላይም በኢትዮጵያ በኩል በሕግና ፍትሕ በተለይም ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በመከላከል፣ ባሕላዊ የፍትሕ ማዕከላትን በማጠናከር በሌላም በኩል ሲንጋፖር ያላትን አለም ዓቀፍ የግልግል ዳኝነት ማዕከል የመሆን ልምድን በመውሰድ ኢትዮጵያን የግልግል ዳኝነት መዳረሻ ለማድረግ መስራት፣ በአቅም ግንባታ ረገድ በጋራ የመስራትና የሁለትዮሽ ትብብሩን የማጠናከር ፍላጎት እንዳለ ተመላክቶ ውይይቱ ተጠናቋል፡፡