በኢትዮጵያ የሽግግር ፍትህ የህግ ረቂቆች ላይ ያተኮረ አለም አቀፍ ኮንፍረስ መካሄድ ጀመረ

International Conference on Transitional Justice Draft Laws Begins in Ethiopia

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር ከInstitute for Security Studies (ISS) ጋር በመተባበር የሽግግር ፍትሕን ለማስፈፀም እንዲያገለግሉ ታስቦ በተዘጋጁ የሕግ ረቂቆች ላይ ትኩረቱን ያደረገ ዓለም ዓቀፍ ኮንፍረስ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡

ለሁለት ቀናት የሚካሄደውን ይህን ዓለም አቀፍ ኮንፍራንስ ከተለያዩ የአለም አካባቢዎች ማለትም ከደቡብ አፍሪካ፣ ከኮሎንቢያ፣ ሴራሊዮን፣ ሱዳን፣ አሜሪካ፣ እንግሊዝ እና ከሌሎች በርካታ ሀገራት የተውጣቱ በሰብዓዊ መብት እና በሽግግር ፍትሕ ላይ ከፍተኛ የትምህርት ዝግጅትና የስራ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች እየታደሙት ይገኛል፡፡

መድረኩን በንግግር የከፈቱት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር ሚንስትር ክብርት ወ/ሮ ሀና አርአያስላሴ ሲሆኑ ሚኒስትሯ በመልዕክታቸው በሽግግር ፍትሕ ላይ ያላቸውን ልምድ ለማካፈል ከተለያዩ ዓለም ሀገራት የመጡትን ባለሙያዎች እንኳን ደህና መጣችሁ ካሉ በኋላ ባለሙያዎቹ ኢትዮጵያን ወደ ፊት ለማሻገር ታልሞ በመተግበር ላይ በሚገኘው የሽግግር ፍትሕ ሂደት ሙያዊ አበርክቶ ለማድረግ ያላቸውን ፍላጎት እና ላሳዩት በተግባር የተገለጸ ቁርጠኝነት ምስጋናቸውን ገልፀዋል፡፡

ሚንስትሯ አያይዘውም ፍትሕ ሚኒስትቴር ካለፉት ሁለት አመታት ወዲህ በሀገሪቱ በዘርፉ የዳበረ እውቀት እና ልምድ ያላቸውን ባለሙያዎችና አማካሪዎች በማሰባሰብ በተደረገ ጥረት መሠረት ተጎጂዎችን ማዕከል ያደረገ፣ አሳታፊና ተዓማኒነት ያለው የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ተዘጋጅቶ በሚኒስትሮች ምክር ቤት እንዲጸድቅ መደረጉን አስታውሰው በቀጣይም ፖሊሲውን በማስተግበር ባለፉት ዘመናት የተፈጸሙ ጉልህ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እልባት በመስጠት ዘላቂ ሰላም እና ዴሞክራሲን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ስራዎች ይሰራሉ ብለዋል፡፡

በዚህም መሠረት ባለሙያዎቹ በሽግግር ፍትሕ ዙሪያ ያላቸውን እውቀት እና ልምድ በማካፈል ለረቂቆቹ ጥራት እና ምልዑነት ተገቢውን ሙያዊ ድጋፍ እንዲያደርጉ እና ለኮንፈረንሱ ግብ መሳካት የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በዚህ ለሁለት ቀናት በሚካሄደው አለም በዚህ አቀፍ ኮንፍረንስ ላይ ከተለያዩ የአለም ሀገራ የመጡት ባለሙያዎችና ተመራማሪዎች እንደ ሙያ መስካቸውና የትምህርት ዝግጅታቸው በቡድን ተከፋፍለው በእውነት እና እርቅ ኮሚሽን ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ፣ በልዩ ዐቃቤ ሕግ ተቋም ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ እና በዓለም ዓቀፍ ወንጀል ረቂቅ ሕግ፣ በተቋማት ማሻሻያ ኮሚሽን ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ፣ በሽግግር ፍትሕ ልዩ ችሎት ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ፣ በተዘጋጁት የመጀመሪያ ረቂቆች ላይ ከተወያዩ በኋላ ባለሙያዎቹ የሚሰጡት ሀሳብና አስተያየት ተሰብስቦ የተዘጋጁት ረቂቅ ህጎችን ለማዳበር ጥቅም ላይ እንዲውል እንደሚደረግ ከመድረኩ ለመረዳት ተችሏል፡፡

Tagged Under: International Conference Legal Drafts transitional justice
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች