በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የንቃተ ሕግ ትምህርት እና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት በድሬዳዋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት አዲስ ለተቀጠሩ ዐቃብያነ ሕግ በተቋማዊ አሠራርና አደረጃጀት፣ በወንጀል ምርመራ፣ ክስ ዝግጅትና ችሎት ክርክር እንዲሁም በዐቃብያነ ሕግ ሙያዊ ስነ-ምግባር ዙሪያ ከህዳር 2 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ አምስት ቀናት በድሬዳዋ ከተማ ሥልጠና እየተሰጠ ይገኛል፡፡
በሥልጠናው ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ቃሲም አማን እንደተናገሩት ተቋሙ ጽ/ቤቱ ከዚህ ቀደም የነበረበትን የሰው ኃይል እጥረት በመረዳት በርካታ ባለሙያዎችን በመመደብ ችግሩ እንዲቀረፍ በማደረጉ ምስጋናቸውን አቅርበው “ሁሌም የሕግ ሰው መማር አለበት” በማለት የሥልጠናውን አስፈላጊነት አስረድተዋል፡፡ አያይዘውም ሥልጠናው ባላችሁ እውቀት ላይ ክህሎትን በመጨመር ወደፊት አንድ እርምጃ ከፍ የሚያደርግ የስራ ላይ ትውውቅ በመሆኑ ለሥልጠናው ትኩረት ሰጥቶ መከታተል እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
የተቋም ግንባታና ሪፎርም ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ መዝሙር ያሬድ በበኩላቸው ሥልጠናው የተሰጠበት ዋና ዓላማ አዲስ የተቀጠሩ ዐቃብያነ ሕግ በተቋሙ ውስጥ ያለውን አሠራር እና አደረጃጀት ተቋሙ ከተሰጠው ሀገራዊ ተልዕኮና ራዕይ አንጻር ምን እንደሚመስል በውል ተረድተው ወደ ስራ ለመግባት ያስችላል ብለዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ውስጥ ዐቃብያነ ህጉ በዕለት ተዕለት ተግባራቸው ያላቸውን ሚና በሚገባ ጠንቅቀው እንዲረዱ ለማሳወቅ እንዲሁም ከወንጀል ምርመራ፣ ክስ አዘገጃጀትና ጥራት እንዲሁም በክርክር ክህሎት ዙሪያ በተግባር ያለውን አሠራር ጠንቅቆ ለማወቅ የሚረዳ የቅድመ ስራ ላይ ሥልጠና መሆኑን በንቃተ ሕግ ትምህርት እና ሥልጠና ዳሬክቶሬት ረዳት ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የሆኑት አቶ ዮሀንስ ግርማ አስረድተዋል። አክለውም በአሠራር ላይ ሊያጋጥሟቸው የሚችሉ ተግዳሮቶችን በብቃት ለመወጣት የሚያስችል ሥልጠና እንደሆነም አብራርተዋል፡፡
በመጨረሻም የሕግ ሙያ ከሌሎች የሙያ ዘርፎች በተለየ ሁኔታ ከፍተኛ ሥነ-ምግባር የሚጠይቅ በመሆኑ ሰልጣኞች በመዛግብት ውሳኔ አሰጣጥ፣ በወንጀል ምርመራና ክርክር ስራዎች ላይ የዐቃብያነ-ህጎች ስነ-ምግባር ምን እንደሚመስል በሥልጠናው በዝርዝር ተካትቷል። ሥልጠናው ከህዳር 2 እስከ 6 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ የሚሰጥ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡