ከ86 ሺ በላይ ሀሰተኛ የአሜሪካን ዶላር ለመመንዘር ይዞ የተገኘው ግለሰብ በእስራት ተቀጣ

Individual Sentenced to Imprisonment for Possessing Over 86,000 Counterfeit US Dollars for Exchange

በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የኢኮኖሚ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ 86ሺ 600 ሀሰተኛ የአሜሪካን ዶላር እንደ እውነተኛ አስመስሎ ሊመነዝር ሲል እጅ ከፍንጅ በተያዘው ታደሰ ኃ/ማርያም ላይ ክስ መስርቶበት በ10 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ አድርጓል፡፡

የዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው ተከሳሹ ለጊዜው ካልተያዘው ግለሰብ ጋር በመሆን ህዳር 5 ቀን 2015 ዓ.ም በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 09 ዲአፍሪክ ሆቴል ተብሎ ከሚታወቀው አካባቢ ኦዚ ካፌ ውስጥ 86ሺ 600 ሀሰተኛ የአሜሪካን ዶላር እንደ እውነተኛ አስመስሎ በመመንዘር እንዲዘዋወሩ ለማድረግ ሲል እጅ ከፍንጅ የተያዘ በመሆኑ ሀሰተኛ ገንዘብ ይዞ መገኘት ወንጀል በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ወንጀል ሕግ አንቀጽ 359 ስር የተመለከተውን በመተላለፍ ክስ የቀረበበት ሲሆን እንዲሁም በዚሁ ቀን በአዲስ አበባ ከተማ በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 09 ፖሊስ መምሪያ ተጠርጥሮ በሕግ አግባብ ተይዞ ታስሮ ካለበት የማቆያ ቤቱን በር በመገንጠል ከእስር ቤቱ ያመለጠ በመሆኑ ከእስር ማምለጥ ወንጀል የወንጀል ሕጉን አንቀጽ 461/2/ ስር የተመለከተውን በመተላለፍ ሁለት ተደራራቢ ክሶች ቀርበውበታል።

በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 11ኛ ወንጀል ችሎት የቀረበው ተከሳሽ የተከሰሰበት ክስ በችሎት ተነቦለት የወንጀል ድርጊቱን አልፈፀምኩም ጥፋተኛም አይደለሁም በማለት ክዶ የተከራከረ በመሆኑ ዐቃቤ ሕግ ማስረጃዎችን አቅርቦ በማሰማት ተከሳሹ የወንጀል ድርጊቱን ስለመፈጸሙ በበቂ ሁኔታ በማስረዳቱ ፍርድ ቤቱ ተከሳሽ እንዲከላከል ብይን ቢሰጠውም የመከላከያ ምስክር የለኝም በማለት ማቅረብ ባለመቻሉ በተከሰሰበት የሕግ ድንጋጌ ስር የጥፋተኛነት ፍርድ በመስጠት በ10 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ሲል ወስኗል፡፡

Tagged Under: addis_abeba • counterfeit_us_dollars • currency_counterfeiting • economic_crime • economic_crimes_directorate • Forgery • Fraud • imprisonment
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች