በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የኢኮኖሚ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ የጉሙሩክ ስነ-ስርዓት ያልተፈፀመበትን ወርቅ ይዞ ሲገባ በተያዘው አወል ሟኔ ላይ ምርመራ በማጣራት ክስ መስርቶበት በጽኑ እስራት እና በገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ አድርጓል፡፡
የዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው አወል ሟኔ የተባለው ተከሳሽ የጉሙሩክ ስነ-ስርዓት ያልተፈፀመበት እቃ መሆኑን እያወቀ ከተባበሩት አረብ ኢምሬት ሀገር ዱባይ ከተማ በመነሳት የካቲት 14 ቀን 2014 ዓ.ም አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም ዓቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የገቢ መንገደኞች የጉሙሩክ ፍተሻ ቦታ ደርሶ በተደረገው ዝርዝር አካላዊ ፍተሻ የጉሙሩክ ስነ-ስርዓት ያልተፈፀመበትን 2 ኪሎ ግራም ያልተዘጋጀ (ጥፍጥፍ) ወርቅ መንግሥት ከቀረጥና ታክስ ማግኘት ያለበትን 6 ሚሊዮን 282 ሺ 419 ብር በእለቱ በለበሰው ጫማ ሶል ስር ደብቆ ወደ ሀገር ውስጥ ሲያስገባ በመያዙ በፈፀመው የጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 859/2006 (በአዋጅ ቁጥር 1160/2011) እንደተሻሻለው አንቀጽ 168/1 ስር የተመለከተውን በመተላለፍ በኮንትሮባንድ ወንጀል ተከሷል፡፡
በዚህም ምክንያት ዐቃቤ ሕግ ተከሳሹ በፈፀመው ወንጀል ክስ መስርቶበት ሲከራከር ቆይቷል፡፡
ክስ እና ማስረጃዎችን የመረመረው የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ 9ኛ ወንጀል ችሎት ታህሳስ 25 ቀን 2015 ዓ.ም ባስቻለው ችሎት ተከሳሹ በተከሰሰበት ክስ የጥፋተኛነት እና የቅጣት ውሳኔ በማሳለፍ በአጠቃላይ በተከሳሹ ላይ በ5 ዓመት ከ6 ወር ጽኑ እስራትና በ76 ሺ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ሲል ተከሳሽ በሌለበት ወስኖበታል፡፡
አወል ሟኔ በምስሉ ላይ ያለው ግለሰብ ሲሆን ወንጀል መፈጸሙን አውቆ ለጊዜው ተሸሽጎ ያለ ቢሆንም በሌለበት የክስ ውሳኔ ተላልፎበታል በመሆኑም ተከሳሹ አዲስ አበባ አራዳ ክ/ከ ወረዳ 10 ነው መኖሪያ የተመዘገበው እድሜው የ30 ዓመት ወጣት ነው፤ ከህብረተሰቡ አይሰወርምና አወል ሟኔን የሚያውቅ ወይም ያየ ለሕግ አካላት በመጠቆም እንዲያሲዘው አሳሰብን ቸር እንሰብት፡፡