ሐጎስ እና መሰለ ስራ ተቋራጭ የሽርክና ማህበር ከ200 ሺ ብር በላይ የንግድ ትርፍ ግብር እና የተጨማሪ እሴት ታክስን አሳውቆ ባለመክፈሉ እና ኃላፊነታቸውን ያልተወጡት የማህበሩ ስራ አስኪያጅና የኮንስትራክሽን ባለሙያ በእስራት እንዲቀጡ ተወሰነ

Hagos and Messele Construction Partnership Punished, Managers Imprisoned for Over 200,000 Birr Tax Evasion and Negligence

በኢፌዲሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የኢኮኖሚ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ ሐጎስ እና መሰለ ስራ ተቋራጭ የሽርክና ማህበር ከ200 ሺ ብር በላይ የንግድ ትርፍ ግብር እና የተጨማሪ እሴት ታክስን አሳውቆ ባለመክፈሉ እና ኃላፊነታቸውን ባልተወጡ የማህበሩ ስራ አስኪያጅና የኮንስትራክሽን ባለሙያው ላይ ክስ አቅርቦባቸው በ1ኛ ተከሳሽ ማህበሩ ላይ የ100 ሺ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ፣ እንዲሁም ደግሞ በ2ኛ እና በ3ኛ ተከሳሾች በእያንዳንዳቸው ላይ በ3 ዓመት ከ5 ወር ጽኑ እስራት እና የ50 ሺ ብር የገንዘብ መቀጮ ቅጣት እንዲጣልባቸው አድርጓል፡፡

የዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው እንደየወንጀል ተሳትፎ ደረጃቸው አራት ተደራራቢ ክሶች የቀረበባቸው ተከሳሾች 1ኛ ሐጎስ እና መሰለ ስራ ተቋራጭ የሽርክና ማህበር፣ 2ኛ ሐጎስ ሽብሩ (የማህበሩ ስራ አስኪያጅ)፣ 3ኛ መሰለ አሰኔ (የማህበሩ የኮንስትራክሽን ባለሙያ) ናቸው፡፡

በ1ኛ እና በ2ኛ ክስ ላይ የታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/2008 አንቀጽ 116/2/ እና 125/1/ን በመተላለፍ ሁለቱ ክሶች የቀረቡት በ1ኛ ሲሆን ተከሳሹ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በህጋዊነት ተመዝግቦ የንግድ ስራ ሲሰራ የቆዬ የሽርክና ማህበር ሲሆን በግብር ስወራ ወንጀል ተጠርጥሮ በተደረገው የኢንቨስትጌሽን ኦዲት በ2011 የግብር ዘመን ከአንድ ግለሰብ ጋር በተደረገ የመኖሪያ ቤት ግንባታ ውል መሠረት ለተፈጸመለት ክፍያ 1 ሚሊዮን 160 ሺ ደረሰኝ ባለመቁረጥ በነጭ ወረቀት ላይ ለተፈፀመው ክፍያ የመተማመኛ ሰነድ በሚል ብቻ በመፈራረም በግብር ዘመኑ ምንም አይነት ገቢ እንዳላገኘ በማሳወቅ በ2011 የግብር ዘመን አሳውቆ መክፈል የሚጠበቅበትን የንግድ ትርፍ ግብር ፍሬ ግብር 54 ሺ 48 ብር አሳውቆ ባለመክፈሉ በፈጸመው የንግድ ትርፍ ግብር ስወራ ወንጀል፤ እና

በተመሳሳይ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከመጋቢት 1 ቀን 2006 ዓ.ም ጀምሮ በተጨማሪ እሴት ታክስ ቁጥር ተመዝግቦ የንግድ ስራ ሲሰራ የቆዬ የሽርክና ማህበር ሲሆን በግብር ስወራ ወንጀል ተጠርጥሮ በተደረገው የኢንቨስትጌሽን ኦዲት በ2011 ከአንድ ግለሰብ ጋር በተደረገ የመኖሪያ ቤት ግንባታ ውል መሠረት ለተፈጸመለት ክፍያ የተጨማሪ እሴት ታክስን ጨምሮ 1 ሚሊዮን 160 ሺ ብር የተቀበለ ቢሆንም በ2011 የግብር ዘመን አሳውቆ መክፈል የሚጠበቅበትን የተጨማሪ እሴት ታክስ ፍሬ ግብር 173 ሺ 987 ብር አሳውቆ ባለመክፈሉ በፈጸመው የተጨማሪ እሴት ታክስ ስወራ ወንጀል ተከሷል፡፡

በ3ኛ እና በ4ኛ ክስ ላይ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32/1/ሀ/፣ የታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/2008 አንቀጽ 125/1/ እና 132/1/ን ተላልፈዋል በሚል በ2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች ላይ ክስ የቀረበ ሲሆን 2ኛ ተከሳሽ የ1ኛ ተከሳሽ የሽርክና ማህበር ስራ አስኪያጅ እንዲሁም 3ኛ ተከሳሽ የሽርክና ማህበሩ ሸሪክ እና በተግባር ውሎችን በመፈራረምና ክፍያ በመቀበል የስራ አስኪያጅነትን ተግባር በማከናወን እንደ ስራ አስኪያጅ ሲሰሩ ድርጅታቸው ግብር እንዳይሰውር የሚያስችለውን አሠራር የመዘርጋት ኃላፊነት በሕግ የተጣለባቸው ቢሆንም ይህንን ኃላፊነታቸውን ባለመወጣታቸው ምክንያት ህጉ ከስራ አስኪያጅ የሚጠበቀውን ኃላፊነት እና ግዴታ ያልተወጡ በመሆኑ በፈፀሙት የንግድ ትርፍ ግብር ስወራ እና የተጨማሪ እሴት ታክስ ስወራ ወንጀል ዐቃቤ ሕግ ክስ መስርቶባቸዋል፡፡

ጉዳዩን የተመለከተው የፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 8ኛ ወንጀል ችሎትም ተከሳሾች በሁሉም በቀረቡባቸው ክሶች ጥፋተኛነታቸውን በማረጋገጥ የቅጣት ውሳኔ አስተላልፏል፡፡

በዚህም መሠረት ፍርድ ቤቱ 1ኛ ተከሳሽ በሕግ እውቅና ያገኘ ሰው ወይም ድርጅት በመሆኑ በ100 ሺ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ፣ እንዲሁም ደግሞ በ2ኛ እና በ3ኛ ተከሳሾች እያንዳንዳቸው በ3 ዓመት ከ5 ወር ጽኑ እስራት እና የ50 ሺ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ሲል ወስኗል፡፡

Tagged Under: added • Auditing • case • company • construction • Criminal Code • evasion • federal • federal first instance court • fine • first • imprisonment • Income • Income Tax • legal • legal case • negligence • partnership • Tax • tax administration • Tax Evasion • Tax law • value • value-added tax (vat) • vat
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች