በመርሀ ግብሩ ላይ ተገኝተው ችግኞችን ከተከሉ በኋላ መልዕክት ያስተላለፉት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ ከወራት በፊት በዚህ አካባቢ ከነበረው የሰላም እጦት እና አለመረጋት ወጥተን እንዴ ባለ ፍጹም ሰላማዊ ሁኔታ በአረንጓዴ አሻራ ችግኝ የማኖር መርሀ ግብር ላይ ተገኝተን አብሮነታችንን መግለጽ በመቻላችን ደስታ ተሰምቶኛል ብለዋል።
ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው በጸረ-ሰላም ሀይሎች ህገ- ወጥ ድርጊት ምክንያት በአካባቢው ተፈጥሮ የነበረውን ሁከት እና ብጥብጥ ለመቆጣጠር የፌዴራል እና የክልል ጸጥታ ተቋማት ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር በመቀናጀት በሰሩት የሕግ ማስከበር ሥራ አካባቢው ፍጹም ሰላማዊ መሆኑን በተጨባጭ አረጋግጠናል ብለዋል።
አክለውም ይህንን ሰላም ዘላቂነቱን ለማስጠበቅ እና ነዋሪዎቹም ከስጋት ተላቀው በነጻነት መኖር እንዲችሉ ከጸጥታ ተቋማቱ ጋር አብረን መሥራት ይጠበቅብናል ያሉ ሲሆን ይህን እውን ከማድረግ አንጻር ፍትሕ ሚኒስቴር ከፌዴራል እና ክልል የጸጥታ ተቋማት ጋር በቅንጅት ለመሥራት ሁሌም ዝግጁ መሆኑን ገለጸዋል።
በተለይም ለሁከቱ እና ብጥብጡ ምክንያት የሆኑ ግለሰቦችን በሕግ እንዲጠየቁ በማድረግ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ተገቢውን ጥረት እናደርጋለን ያሉት ሚኒስትሩ ማህበረሰቡም ሰላምን በማረጋገጥ ሂደት ውስጥ አይተኬ ሚናውን እንዲጫወት እጠይቃለሁ ብለዋል።