የአስፈፃሚ አካላትን ሥልጣን እና ተግባር ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 1263/2014 ዓ.ም መሠረት የንግድ ውድድር እና ሸማቾች ጥበቃ ዳኝነት ችሎት ከ የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ወደ ፍትሕ ሚኒስቴር የተዛወረ ሲሆን በአዋጅ ቁጥር 813/2006 የተቋቋመው ችሎት ዓላማውም የንግድ ስራ ሀገሪቱ በምትከተለው የነጻ ገበያ ኢኮኖሚ ፖሊሲ መሠረት ህጋዊ የሆነ አሠራርን ተከትሎ እንዲሄድ ለማድረግ፣ የንግዱን ህበረተሰብ ከጸረ- ውድድር እና ተገቢ ካልሆኑ የገበያ ተግባራት ለመከላከል እንዲሁም ሸማቹ ህብረተሰብ ላወጣው ዋጋ ተመጣጣኝ የሆኑ የንግድ ዕቃዎች እና አገልግሎቶች ማግኘት እንዲችሉ ለማድርግ የተቋቋመ አስተዳደራዊ ፍርድ ቤት ነው።
ለችሎቱ ክስ የሚያቀርበው በቀድሞ የንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን በአሁኑ የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ሲሆን የገበያ የበላይነትን ያለአግባብ መጠቀም፣ በነጋዴዎች መካከል የሚደረጉ ጸረ- ውድድር ስምምነቶች፣ ተገቢ ያልሆኑ የንግድ ውድድር ተግባራት፣ ህገወጥ ውህደት በፈጸሙ ነጋዴዎች ላይ ወይም ነጋዴ ባልሆኑ ሰዎች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ እና ቅጣት እንዲጣል ወደ ችሎቱ ክስ ያቀርባል፡፡
በዚህም መሠረት የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስተር የንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 813/2006 አንቀጽ 8 ስር የተደነገጉ ድንጋጌዎችን በመተላለፍ ሁአሼንግ ኬብልስ ማኑፋክቸሪንግ ኃ/የ/የግ/ማህበር ከደረጃ በታች የሆነ የኤሌክትሪክ ገመድ በማምረት እና ባመረተው ምርት ላይ ለተጠቃሚ የተዛባ መረጃ በመስጠት በተወዳዳሪ ነጋዴ ላይ እንዲሁም በሸማቾች ላይ ጉዳት የሚያደርስ ተግባር በመፈፀሙ እንዲሁም ሰሂማ ጀማል ሰዒድ የተሰኘው ድርጅት ተመሳስሎ የተሰራ የውበት መጠበቂያ ምርት ከውጭ ሀገር አስገብቶ ገበያ ላይ በመሸጥ የተወዳዳሪ ነጋዴ የንግድ ጥቅም የሚጎዳ ተግባር በመፈፀሙ ድርጅቶች ላይ የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስተር በንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ ዳኝነት ችሎት ክስ አቅርቦ በክርክር ላይ የነበሩ ሲሆን ችሎቱም ጉዳዩን በማስረጃ ካጣራ በኋላ ተከሳሾቹ የአዋጁን ድንጋጌ በመተላለፍ ተገቢ ያልሆነ የንግድ ውድድር ተግባር መፈፃማቸውን አረጋግጦ በአዋጁ አንቀጽ 42/3/ መሠረት ከዓመታዊ የሽያጭ ገቢያቸው ላይ 5 በመቶ እንዲቀጡ ውሳኔ ሰጥቷል ፡፡
ከሳሽ የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር በውሳኔው መሠረት እንዲፈጽሙ ለችሎቱ የአፈጻጸም ክስ ያቀረበ ሲሆን ችሎቱም ተከሳሾቹ በውሳኔው መሠረት እንዲፈጽሙ በሰጠው ትእዛዝ መሠረት ሁአሼንግ ኬብልስ ማኑፋክቸሪንግ ኃ/የ/የግ/ማህበር 17 ሚሊዮን 733 ሺ 946 ፣ ሰሂማ ጀማል ሰዒድ 424 ሺ 370 ብር በአጠቃላይ 18 ሚሊዮን 158 ሺ 317 ብር በቅጣት ወደ መንግሥት ገቢ ተደርጓል፡፡