በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች በ2017 በጀት ዓመት 9 ወራት 39,687 መዛግብት ላይ ውሳኔ ተሰጠ

Branch Offices of the Attorney General Sector of the FDRE Ministry of Justice Decide on 39,687 Cases in the First 9 Months of the 2017 Budget Year

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ እንዲሁም የድሬደዋ እና የሀዋሳ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች በ2017 በጀት ዓመት 9 ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ላይ በትላንትናው ዕለት ውይይት ተደርጓል፡፡

የፍትሕ ሚኒስቴር የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥና የህብረተሰቡን ጥቅሞች ለማስከበር ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል አንደኛው በሆነው የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የወንጀል ምርመራ፣ክስና ክርክሮችን በማከናወን ፍትሕ እንዲሰፍን ከማድረግ አኳያ በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ 9 ወራት የተከናወኑ ተግባራት አፈፃፀም ሪፖርት የሚመለከታቸው የቅርንጫፍ ጽ/ቤት የስራ ሀላፊዎችና የቡድን መሪዎች በተገኙበት የእቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጓል፡፡

በፍትሕ ሚኒስቴር በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች መከታተያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ጌቱ ታደሰ በውይይት መድረኩ ባደረጉት ገለፃ በበጀት አመቱ የወንጀል ፍትሕ አገልግሎት አሰጣጥ አቅምንና ተደራሽነትን ለማሳደግ፤ ምርመራቸው ተጠናቀው ለቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ለውሳኔ ቀርበው መወሰን ያለባቸውን 39,924 የምርመራ መዝገቦች ውስጥ 97% በሚሆኑ መዛግብት ላይ ውሳኔ ለመስጠት ታቅዶ በ39‚687 ወይም (99.4%) መዝገቦች ላይ በቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ውሳኔ መስጠት መቻሉና ይህም ከባለፈው ዓመት አንፃር 5,139(14.87%) መዛግብት ዐቃቤ ሕግ ጭማሪ ውሳኔ የሰጠባቸው መሆኑንና የውዝፍ ምጣኔውንም ከ1.4% ወደ 0.6% ማውረድ እንደተቻለ ጠቅሰዋል፡፡

በሪፖርቱ በኢኮኖሚ ፣በሙስና ፣ በተደራጁ እና ድንበር ተሻጋሪ ፣በልዩ ልዩ ወንጀሎች እንዲሁም በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች የምርመራ መዛግብት ላይ ውሳኔ በመስጠት ከማጥራት አኳያ የማጥራት ምጣኔ አፈፃፀማቸው ከተያዘው እቅድ አንፃር መልካም አፈፃፀም የተመዘገበባቸው እንደሆነ ማወቅ ተችሏል፡፡ በርካታ መዛገብት ላይ ዐቃቤ ሕግ ውሳኔ እንዲሰጥበት በማድረግ መልካም አፈፃፀም ማሰመዝገብ መቻሉ እንደ ጥንካሬ የሚጠቀስ መሆኑን እና የሚስተዋሉ የመረጃ አያያዝ ክፍተቶች ደግሞ በቀጣይ ትኩረት ተደርጎ ሊሰራባቸው እንደሚገባ በውይይት መድረኩ ተጠቁሟል፡፡

በቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች በሁሉም የወንጀል ክርክር መዛግብት የመርታት ምጣኔን በሪፖርታቸው ላይ እንዳብራሩት በክርክር ላይ ከነበሩት 30,290 መዛግብት እና 35,672 ተከሳሾች ውስጥ ፍርድ ቤት በ9,368 መዛግብት እና በ11,683 ተከሳሾች ላይ ውሳኔ የሰጠ ሲሆን፣ በ9,107 መዛግብት እና በ11,380 ተከሳሾች ላይ የጥፋተኝነት በ9,120 ላይ የጥፋተኝነ ፍርድ መሰጠት መቻሉ ተገልፆል፡፡

በፍትሀብሔር ጉዳዮች የሚሰጥ ፍርድ ማስፈፀምን በተመለከተ 32,789,345.39 ብር በዓይነት እና በገንዘብ የሚተመን በፍርድ ቤት ክርክር ተደርጎባቸው ለፍርድ ባለመብቶች እንዲወሰን በማድረግ ከተወሰነው ውሳኔ ውስጥ 15,314,030.64 ብር ለፍርድ ባለመብቶች እንዲከፈል መደረጉን በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡

የሰብዓዊ መብትን የማክበር አፈፃፀምን በሚመለከት በ9 ወራት ውስጥ፤ በአጠቃላይ ለ17‚432 ተጠርጣሪዎችን በማረሚያ ቤት ተገኝቶ በመጎብኘት የታዩ ችግሮች ተለይተው መፍትሔ እንዲሰጣቸው ለማድረግ የተቻለ መሆኑ በውይይቱ ወቅት የተመላከተ ሲሆን፤ በተያያዘም በተለያዩ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች አማካኝነት አዲስ አበባን ጨምሮ ድሬደዋ እና ሀዋሳ ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈፅመዋል በተባሉ አካላት ላይ ምርመራ እንዲደረግባቸው ውሳኔ መሰጠቱ ተገልፆል፡፡

በመጨረሻም በቀረበው ሪፖርት ላይ ሰፋ ያለ ውይይት የተደረገ ሲሆን፣ ዳይሬክተሩ ባስተላለፉት መልዕክት ሁሉም አካላት የተጣለባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ በማሳስብ እንዲሁም ቀጣይ የስራ አቅጣጫዎችን በመስጠት የእቅድ አፈፃፀም ውይይቱ ተጠናቋል፡፡

Tagged Under: addis ababa Attorney General budget year case management Case Resolution caseload Child Protection civil liberties Corruption court cases Criminal Investigations democratic Dire Dawa Economic Crimes ethiopian federal democratic republic federal federal democratic republic of ethiopia (fdre) fundamental rights Gender-Based Violence hawassa Human Rights Human Rights Violations judicial decisions office of the attorney general Performance Review prison conditions prosecutions republic Transnational crime
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች