የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅ መሰረታዊ ይዘቶች

Basic Contents of the Draft Asset Recovery Proclamation

በወንጀል የተገኘ ሃብት ማስመለስን በተመለከተ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የሕግ ማዕቀፎች ውስጥ እራሱን የቻለና ወጥ የሆነ የሕግ ማዕቀፍ የሌለ በመሆኑ በሕግ ማስከበር ሂደት በጣም ሰፊ ሊባል የሚችል ክፍተት ፈጥሯል፡፡ ይህም ጉዳይ ዐቃቤ ሕግ ወደ ፍርድ ቤት የሚወስዳቸው የንብረት ማስመለስን የተመለከቱ የክርክር መዛግብት ላይ እየታየ የሚገኝ ችግር ስለመሆኑ የፍትሕ ሚኒስቴር እና በሌሎች ባለሙያዎች በተደረገ ጥናት የተለየ ነው፡፡ በሌላ በኩል በተለያዩ አዋጆች ስር የተሸፈኑ የንብረት ማስመለስ ሥነ-ሥርዓትን የሚያስቀምጡ ድንጋጌዎችን ስንመለከት በራሳቸው የተሟሉ ካለመሆናቸው ባለፈም አንዱን ከሌላው ጋር እያስማሙ ለመተግበር አስቸጋሪ የሚያደርጓቸው ድንጋጌዎችን የያዙ እና ተፈጻሚነታቸውም ውስን የሆኑ ወንጀሎችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ የተቀረጹ በመሆኑ ሁሉን አቀፍ እና ወጥ በሆነ መልኩ ሁሉም አይነት ወንጀሎች ላይ ተግባራዊ ለማድረግ አልተቻልም፡፡ በዚህም ወንጀል ፈፃሚዎች ከወንጀል ድርጊት ያገኙትን ንብረቶች በማስመለስ ረገድ ከፍተኛ የሆነ የሕግ እና አሠራር ክፈተቶች እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል። ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት ፍትሕ ሚኒስቴር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የሀብት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅ ያዘጋጀ ሲሆን፥ ረቂቁ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ታይቶ በአሁኑ ሰዓት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እየተመረመረ ይገኛል።

በረቂቅ አዋጁ ከተካተቱ የንብረት ምርመራ፣ ማገድ፣ መያዝ፣ ማስተዳደር እና ውርስ በተጨማሪ ምንጩ ያልታወቀ ንብረትን የተመለከቱ ድንጋጌዎችን አካቷል፡፡ የተለያዩ ሀገሮች ከወንጀል የተገኘ ንብረትን ለማስመለስ እራሱን የቻለ የሕግ ማዕቀፍ እንዲሁም ጠንካራ አስፈፃሚ ተቋማት እየገነቡ ይገኛሉ፡፡ ምንጩ ያልታወቀ ንብረትንም በተለመከተ የተለያዩ ሀገራት ሕግ በማውጣት ተግባራዊ እያደረጉት ሲሆን ይህም ንብረት የማጣራት ወይም ንብረት የሚወረስበት አግባብ የሚመለከት ነው፡፡ ሀገሮች በህጋቸው ውስጥ ምንጩ ያልታወቀ ንብረት ላይ የወንጀል ወይም የፍትሐ-ብሔር ኃላፊነት የሚያስቀምጡ ሲሆን በዋናነት የአውስትራሊያ፣ የኬንያ፣ ሩዋንዳ እና ሞርሺየስ እንደምሳሌ ይጠቀሳሉ፡፡ በሀገራችን ኢትዮጵያም ይህን በተመለከተ ለመጀመሪያ ጊዜ የተደነገገው በ1996 በወጣው የወንጀል ሕግ ላይ ሲሆን በዚህ ወቅት ድንጋጌው ሙሉ በሙሉ የመንግሥት ሠራተኞችን ብቻ የሚመለከት በመሆኑ በግሉ ዘርፍ የተሳተፉ ሰዎች በተመሳሳይ ሁኔታ ምንጩ ያልታወቀ ንብረት ሲያፈሩ ተጠያቂ የሚሆኑበት ሕግ አልነበረም፡፡ ይህንን ችግር በሚቀርፍ ሁኔታ ተግባራዊ የተደረገው አዋጅ ቁጥር 657/2002 ሲሆን በዚህ አዋጅ ውስጥ ምንጩ ያልታወቀ ንብረት በሁሉም ላይ ተፈፃሚነት እንዲኖረው እና የወንጀል ኃላፊነትን በሚያመጣ አግባብ የተቀመጠ ቢሆንም የሀገሪቱ ኢኮኖሚ የጥሬ ገንዘብ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ የሁሉንም ሰው የገቢ ምንጭ ማጣራት አዳጋች በመሆኑ ይህ አዋጅን ያሻሻለው አዋጅ ቁጥር 780/2005 የሁሉም ሰው ላይ ያለውን ተፈፃሚነት አስቀርቷል፡፡ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ውስጥ የተካተቱ ድንጋጌዎች ያስቀመጡትን መስፈርት እና ምክረሃሳብ መሠረት በማድረግ ምንጩ ያልታወቀ ንብረትን በሚመለከት ተጠያቂነት ለማካተት በ2007 ዓ.ም የወንጀል ህጉ በሙስና ወንጀሎች አዋጅ ቁጥር 881/2007 ተሻሽሎ ከቀረበ በኋላ ከመንግሥት ሰራተኞች በተጨማሪ የህዝባዊ ድርጅት ሰራተኞችም ተጠያቂ የሚሆኑበትን ድንጋጌ ይዞ ቀርቧል፡፡ ይሁን እንጂ ከእነዚህ ሕግጋት በኋላ ያለው የሕግ ማስከበር አፈጻጸም ምንጩ ያልታወቀ ንብረት ከመንግሥት እና የህዝባዊ ድርጅት ሰራተኞች ውጪ ያሉ ሰዎችን የማይመለከት በመሆኑ ሰፊ በሚባል ደረጃ ምንጩ ያልታወቀ ንብረት የማፍራት ሁኔታ ተስተውሏል፡፡ ለዚህም ቀዳሚ ምክንያት ተብሎ የሚታሰበው ከመንግሥት ሰራተኞችና ከህዝባዊ ሰራተኞች ውጪ ያለውን የህብረተሰብ ክፍል በሚመለከት ምንጩ ያልታወቀ ሃብት መቆጣጠር የሚያስችል የሕግ ስርዓት ባለመኖሩ ግለሰቦች ያለምንም ሕጋዊ ውጤት ውስብስብ በሆኑ በርካታ ሕገ-ወጥ ተግባራት ውስጥ በመሰማራት በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ሀብት እና ንብረት እንዲያፈሩ አስቻይ ሁኔታዎችን ፈጥሯል።

በተጨማሪም የዚህ ሕግ አለመኖር ሌሎች የመንግሥትና ሕዝባዊ ድርጅት ሰራተኞች በቀላሉ በሕገ-ወጥ መልኩ ያፈሩትን ንብረት በእነዚህ ሰዎች ስም ማፍራት እና መደበቅ እንዲችሉ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል። በዋናነት የዚህ ረቂቅ ሕግ መውጣትም ዜጎች በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ እንዲኖራቸው የሚፈለገውን እኩል ተጠቃሚነት የሚያጎለብት እና የግለሰቦችን በሕጋዊ መንገድ ብቻ ንብረት የማፍራት ባህልን በማሳደግ ጠንካራ የሆነ የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን ከፍተኛ አስተዋዕፆ ይኖረዋል። እነዚህን አዎንታዊ ውጤቶችን መሠረት በማድረግ ህጉ በማህበረሰቡ ውስጥ የመብት ጥሰቶች እንዳይገጥሙ ከግምት በማስገባት በረቂቅ ህጉ ውስጥ የተለያዩ የመብት መጠበቂያ ድንጋጌዎችን (Safeguarding Provisions) በማስገባት የግለሰቦችን ሕገ-መንግስታዊ መብቶችን ባጣጣመ መልኩ ተቀርጿል፤ ለዚህም እንደ ማሳያነት ሊጠቀሱ የሚችሉ ምሳሌዎች ውስጥ የቅድመ ክስ ሥርአት መዘርጋቱ፣ የወንጀል ጥርጣሬን መሠረት ማድረጉ፣ የንብረቱን ምንጭ እንዲያስረዳ የተጠየቀ ግለሰብ የሚያቀርበው ማስረጃ የወንጀል ክስ ለማቅረብ ተቀባይነት የማይኖረው መሆኑ እና ተመሳሳይ ድንጋጌዎችን ባካተተ መልኩ ተረቋል፡፡

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅ በወንጀል የተገኘ ንብረት የሚመለስበትን ዝርዝር ድንጋጌ የያዘ ሲሆን ምን አይነት ሁኔታ ላይ ንብረት እንደሚታገድ፣ እንደሚያዝ እንዲሁም የሚታገድ እና የማይታገዱ ንብረቶች በመለየት በዝርዝር ያስቀመጠ ሲሆን ለምሳሌ ለሙያ ስራ፣ ለግል አገልግሎት የሚውልና የቤት ቅሳቁስን እና የመሳሰሉትን በመለየት በዝርዝር አስቀምጧል፡፡ በተጨማሪም ንብረት ለምን ያህል ግዜ፣ በማን ይታገዳል የሚለውን በግልፅ የሚያስቀምጥ ረቂቅ በመሆኑ ለአመታት እግድ ሳይነሳ የሚቆዩ ንብረቶችን ለመከላከል የሚረዳ ከመሆኑ በተጨማሪ የሚያዝ ንብረት በአግባቡ ባለመተዳደሩ ምክንያት ይባክን የነበረበትን ስርዓት በሚቀርፍ አግባብ ንብረት የሚተዳደርባቸውን ዝርዝር ድንጋጌዎች የያዘ ሲሆን ይህም በመጨረሻ ውሳኔ በሚሰጥበት ግዜ ንብረቱ ለባለቤቱ ወይም ለመንግሥት ወይም ለተጎጂ በሚመለስበት ግዜ በተገቢው ይዞታ እና አገልግሎት መስጠት በሚችልበት አግባብ ንብረት ሳይባክን፣ ሳይበላሽ የሚቆይበትን ሥርዓት የዘረጋ ነው፡፡

በአጠቃላይ በወንጀል የተገኘ ንብረትን ጨምሮ ምንጩ ያልታወቀ ንብረትን እና ሌሎች የኢኮኖሚ ወንጀሎችን ለመለየት፣ ለማገድ ፣ ለመያዝ በንብረት አስተዳደር ስር እንዲቆይ ለማድረግ፣ ለመውረስና ዓለም-ዓቀፍ ትብብር ለማድረግ የሚያስችል አንድ ወጥ ሕግ የሚያስፈልግ በመሆኑ ይህንን ረቂቅ አዋጅ ማዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑን ከረጅም ጊዜ ጥናት እና የሕግ ረቂቅ ዝግጅት ሂደት በኋላ የፍትሕ ሚኒስቴር ለፓርላማ ያቀረበው ረቂቅ አዋጅ ነው፡፡

Relevant Departments and People
Tagged Under: Anti-Corruption • asset • asset management • Asset Recovery • confiscation • constitutional rights • Cooperation • criminal • draft • Draft proclamation • Due Process • Economic Crimes • ethiopian law • forfeiture • international • International Cooperation • laundering • law • legal framework • money • Money Laundering • proclamation • property seizure • recovery • unexplained • unexplained wealth • wealth
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች

ተመሳሳይ ዜናዎች