ነሃሴ 2፣ 4 እና 6 ቀን 2016 ዓ.ም የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ዳኞችና የስራ ሃላፊዎች የተሳተፉባቸው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሶስት የውይይት መድረኮች ተካሂደዋል፡፡ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮቹ ዓላማ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ጸድቆ ወደ ተግባር በገባው የኢፌዲሪ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ዙሪያ የዳኞችን እና የፍርድ ቤት የስራ ኃላፊዎችን ግንዛቤ ማሳደግ ነበር፡፡
በዚህ በሶስት ዙር በተካሄደው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ በመጀመሪያው ዙር የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞችና የስራ ሃላፊዎች፣ በሁለተኛው ዙር የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞችና የስራ ሃላፊዎች እንዲሁም በሶስተኛው ዙር የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዳኞችና የስራ ሃላፊዎች ሲሆኑ በድምሩ 240 የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ዳኞች እና የስራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል፡፡
ሥልጠናው በርዕሰ ጉዳዩ ላይ በቂ እውቀት እና የረጅም ጊዜ ልምድ ባላቸው እንዲሁም የቀድሞው የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ዝግጅት የባለሙያዎች ቡድን አባል በነበሩ ባለሙያዎች የተሰጠ ሲሆን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምሕረትን ጨምሮ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የስራ ኃላፊዎች በመድረኮቹ ላይ ተገኝተው መልዕክቶቻቸውን አስተላልፈዋል፡፡
መድረኮቹን የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከአውሮፓ ህብረት የወንጀል ፍትሕ ማሻሻያ ስርዓት ፕሮጀክት ጋር በመተባበር አዘጋጅቶታል፡፡