በፌደራል ደረጃ በተለያዩ የሙስና ወንጀሎች ተከሰው ፍርድ ቤት ከቀረቡ ተከሳሾች መካከል 175 የሚሆኑት በፍርድ ቤት ጥፋተኛ ተብለው ቅጣት እንደተወሰነባቸው በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀኔራል አቶ ዘላለም ፈቃዱ ገለፁ፡፡
ባለፉት ስድስት ወራት የተለያዩ የሙስና ወንጀሎችን የፈፀሙ ተከሳሾች በ191 መዝገቦች ክስ ተመስርቶባቸው፣ አጠቃላይ በክርክር ላይ ከነበሩ 489 መዛግብት መካከልም በ100 መዝገቦች የተከሰሱ 175 ተከሳሾች ጥፋተኛ ተብለው እስከ 19 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት እንደተወሰነባቸው ዳይሬክተር ጀኔራሉ ገልፀዋል፡፡
በተለይም ከአገልገሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ የሚፈፀም ጉቦና የማይገባ ጥቅም መቀበል፣ በመንግሥት አሠራር ላይ የሚፈፀም በሥልጣን አላግባብ መገልገል፣ ከመሬት እና ካሳ ክፍያ ጋር በተያያዘ የሚፈፀም ሙስና፣ ሃሰተኛ መንግስታዊ ሰነዶችን ከማዘጋጀትና ከመጠቀም እንዲሁም ከባንክ ደንበኞች እውቅና ውጪ በሃሰተኛ ሰነዶችና በሞባይል ባንኪንግ የባንክ ሒሳብን በማንቀሳቀስ ከሚፈፀም ምዝበራ ጋር በተያያዘ በርካታ የሕግ ማስከበር ሥራዎች ተሰርተዋል ብለዋል፡፡
ዳይሬክተር ጀኔራሉ በኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት መስሪያ ቤት ከፓስፖርትና ሌሎች አገልግሎቶች አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ሲፈፀም በነበረ ስር የሰደደ የሙስና ወንጀል ላይ በተሠራው የሕግ ማስከበር ሥራ ኢትዮጵያውያን ዜጎች ብቻ ማግኘት የሚገባቸውን የኢትዮጵያ ፓስፖርት በሺዎች የሚገመት ዶላርና የኢትዮጵያ ብር በመቀበል ኢትዮጵያዊ ላልሆኑ የውጭ ሀገር ዜጎች ፓስፖርት በመስጠት፣ ከእያንዳንዱ አገልግሎት ፈላጊ ከ10 ሺ ብር እስከ 300 ሺ ብር በማስከፈል ጉዳያቸውን በሕገ-ወጥ መንገድ በመጨረስ ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከሕገ-ወጥ ደላሎችና ጉዳይ አስፈፃሚዎች ጋር ትስስር በመፍጠር ለተለያዩ የውጭ ሀገራት ዜጎች እንዲሁም ለትውልደ ኢትዮጵያዊያን በሕገ-ወጥ መንገድ የቱሪስት ቪዛ በማውጣትና በማሳደስ፣ የአገር ውስጥ የሥራ እና የመኖሪያ ፈቃዶችን በሕገ-ወጥ መንገድ ለውጭ ሃገራት ዜጎች በማውጣት እና በማሳደስ፣ በሕገ-ወጥ መንገድ ሃብት በማፍራት እንዲሁም በሌሎችም ሕገ-ወጥ ድርጊቶች የተጠረጠሩ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ሠራተኞችና ከእነርሱ ጋር የጥቅም ትስስር ያላቸዉ ግለሰቦች ላይ ምርመራ ተጣርቶ በድምሩ 60 ተጠርጣሪዎች ላይ 15 ተደራራቢ ክሶች የቀረቡ ሲሆን በሌሎች 6 መዝገቦች ላይም በተመሳሳይ ክስ መመስረቱን ገልፀዋል፡፡
ከዚሁ ክስ ጋር በተያያዘ ተከሳሾች በወንጀል ድርጊቱ ያፈሩትን ሀብት በተመለከተ ሰፊ የምርመራ ሥራ እየተሠራ የሚገኝና በሌሎች ተጠርጣሪዎች ላይም የወንጀል ምርመራ ሥራው እንደቀጠለ ሲሆን ቀሪ የወንጀል ምርመራው እንዳለቀም ተገቢው ውሳኔ የሚሰጥበት ይሆናል ብለዋል፡፡
በተመሳሳይ ከመሬት ጋር በተያያዘ መብት ሳይኖራቸው በተጭበረበረ መንገድ ከ82 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ምትክ ቦታና ካሳ በወሰዱና በሰጡ፣ የመሬት ጉዳይን እናስፈፅማለን በማለት ከ8 ሚሊዮን ብር በላይ በተቀበሉና በሌሎች የመሬት ሙስና ጉዳዮች በድምሩ በ48 ተከሳሾች ላይ ከባድ የሙስና ወንጀል እንዲሁም በሕገ-ወጥ መንገድ የተገኘ ንብረትን ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ወንጀል ክስ የቀረበባቸው መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በባንኮች ላይ ከሚፈፀም ምዝበራና ማጭበርበር ጋር በተያያዘ ሃሰተኛ ሰነዶችን በመጠቀም፣ ለረጅም ጊዜ ሳይንቀሳቀሱ የቆዩ የባንክ ሂሳቦችን በማንቀሳቀስ ያለደንበኞች እውቅናና ፈቃድ በሕይወት ከሌሉ፣ ውጪ ሀገር ከሚኖሩና ከሌሎችም ደንበኞች አካውንት ላይ ገንዘብ ወጪ አድርጎ በመውሰድ፣ የባንክ ደንበኞች የሞባይል ባንኪንግና የኤቲኤም ተጠቃሚ ለመሆን ባልጠየቁበትና ፈቃዳቸውን ባልሰጡበት ሁኔታ እንደጠየቁ አስመስለው ተጠቃሚ በማድረግ በተጭበረበረ መንገድ ከደንበኞቹ ሂሳብ ላይ ገንዘብ ወጪ አድርገው በመውሰድና በሌሎችም ህገወጥ መንገዶች ከተለያዩ ባንኮች ከ68 ሚሊየን ብር በላይ በወሰዱ የባንክ ሰራተኞችና ሌሎች ግለሰቦች ላይ በ23 የተለያዩ መዛግብት ክስ የቀረበ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ተገቢውን ክፍያ ሳይከፍሉ እንደከፈሉ አስመስለው ሃሰተኛ የባንክ ደርሰኞችን አዘጋጅቶ ለኢትዮ-ቴሌኮም በማቅረብ ከኢትዮ-ቴሌኮም ላይ ከ1.5 ሚሊየን ብር በላይ በማጭበርበር ለግል ጥቅማቸው ባዋሉ ግለሰቦች ላይ ክስ ቀርቧል ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል በሀገራችን በስፋት ከሚፈፀሙ ወንጀሎች ውስጥ አንዱ ከሆነው ሀሰተኛ መንግሥትና የህዝባዊ ድርጅቶች ሰነዶችን ከማዘጋጀትና ከመገልገል ጋር በተያያዘ ሀሰተኛ የመንግሥትና የህዝባዊ ድርጅቶች ሰነዶችን በማዘጋጀት ለተለያዩ የመንግሥት ተቋማትና ድርጅቶች በማቅረብ ከ48 ሚሊየን ብር በላይ በወሰዱ ግለሰቦች ላይ በ12 መዝገቦች ክስ የቀረበ ሲሆን፣ እንደዚሁም በተሰጣቸው ኃላፊነት ህገ-ወጥ ድርጊት ለመፈፀም በማሰብ ከ3.2 ሚሊየን ብር በላይ ጉቦ በተቀበሉና ባቀባበሉ ግለሰቦች ላይ በ4 የተለያዩ መዝገቦች ክስ የቀረበ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
እንደ ዳይሬክተር ጀነራሉ ገለፃ ከውጪ በእርዳታ የተገኘና በተለያዩ ክልሎች ለሚገኙ ተረጂዎች የተላከን የእርዳታ እህል ከመሸጥና ለግል ጥቅም ከማዋል ጋር በተያያዘ የምርመራና የዐቃቤ ሕግ ቡድን ተዋቅሮ ድርጊቱ በተፈፀመባቸው ክልሎች የእርዳታ እህሉን ለግል ጥቅማቸው አውለዋል የተባሉ ግለሰቦችና ድርጅቶች ላይ የወንጀል ምርመራ ስራ እየተሰራ የሚገኝ ሲሆን፣ በተመሳሳይ በፌደራል ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ከሚፈፀሙ የሙስና ወንጀል ጋር በተያያዘም በተወሰኑ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ላይ ምርመራ የተጣራና የወንጀል ክስም የቀረበ ሲሆን በቀጣይም በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ከግዢና የውስጥ ገቢ ማመንጫ ስራዎች ጋር በተያያዘ የተፈፀሙ የሙስና ወንጀሎችን ከፌደራል ዋና ኦዲተር እና ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የሕግ ማስከበር ስራው የሚቀጥል መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ 6 ወር ውስጥ የሙስና ወንጀል ክስ ቀርቦባቸው በፍርድ ቤት ክርክር ላይ ከነበሩ ጉዳዮች መካከል የልማት ተነሺ ሳይሆኑ እንደሆኑ በማስመሰል በተጭበረበረ መንገድ ከ65 ሚሊዮን ብር በላይ ካሳ በወሰዱና እንዲከፈል ባደረጉ የለሚ ኩራ ክ/ከተማ ወረዳ 06 ዋና ስራ አስፈፃሚን ጨምሮ በ19 ተከሳሾች ጥፋተኛ ተብለው እስከ 19 ዓመት የሚደርስ ፅኑ እስራት እንደተወሰነባቸው ገልፀዋል፡፡
በመጨረሻም በቀጣይ ከተለያዩ አካላት ጋር በመቀናጀት የጸረ-ሙስና የሕግ ማስከበር ስራውን በማጠናከር ከፍተኛ ምዝበራ የተፈፀመባቸው፣ በሀገር ፀጥታና ደኅንነት ላይ አደጋ የሚያስከትሉና ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ በተገልጋይ ህብረተሰቡ ላይ የሚፈፀሙ በመሬት አስተዳደር፣ ፍትሕና ፀጥታ ዘርፍ፣ የመንግሥት ገቢና ግዢ ስርዓት እንዲሁም የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ የሚፈፀሙ የሙስና ወንጀሎች ላይ ትኩረት በማድረግ የሕግ ማስከበር ስራዎች እንደሚሰሩ ዳይሬክተር ጀኔራሉ አክለው ገልጸዋል፡፡