14ኛዎ የፓን አፍሪካ ጠበቆች ህብረት (Pan African Lawyers Union) ኮንፈረንስ በአዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት አዳራሽ በትላንትናዉ እለት በተካሄደ የመክፈቻ ስነ ሰርአት ተጀምሯል።
በኮንፈረንስ መክፈቻ ላይ የፍትሕ ሚኒስትር ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስን ጨምሮ የጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንቶች ፣ የህብረቱ ከፍተኛ መሪዎች፣ የአፍሪካ ሃገራት የጥብቅና ድርጅቶች መሪዎች፣የሕግ ባለሙያዎች፣የሕግ ትምህርት ቤት ተማሪዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛል።
የፍትሕ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ ኮንፈረንሱን ሲከፍቱ ባደረጉት ንግግር የፓን አፍሪካ ጠበቆች ህብረት (Pan African Lawyers Union) እንደ ኤ.አ በ2002 በአዲስ አበባ ሲመሠረት ጀምሮ የኢትዮጵያ መንግሥት ያሳየዉ ቁርጠኝነት የጎላ እንደነበርና አስፈላጊዉን ድጋፍ ማድረጉን አስታዉሰዉ ህብረቱ በቋሚነት መቀመጫውን አዲስ አበባ እንዲያደርግ መንግሥት ፍላጎት እንዳለው አመላክተው ለዚህም መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ሲሉ ተናግረዋል።
እኛ አፍሪካውያን ስለ ፍትሕ እና የሕግ የበላይነት የምናስብበት መንገድ አፍሪካዊ ይዘት ሊኖረው ይገባል እናም ታሪካችንን፣ ወጋችንን እና ምኞታችንን የሚያንፀባርቅ መሆን አለበት ያሉት ክቡር ሚኒስትሩ ለዚህም ይረዳ ዘንድ ከኑሮ ልምዶቻችን እና እውነታዎች ጋር የተጣጣመ አፍሪካዊ የሕግ አስተሳሰብ እና ፍልስፍና የሚፈልቅበትን ሁኔታ መፍጠር አለብን ብለዋል።
በመጨረሻም ክቡር ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ያደረገችዉን የሕግና ፍትሕ ሪፎርም ተከትሎ የጠበቆች ማህበር መመሰረቱንና ይህ ማህበርም በርካታ ጠበቆችን በማቀፍ ስራዉን እየሰራ እንደሚገኝ አንስተዉ ኮንፈረንሱ አንዳቸዉ ከአንዳቸዉ ልምድ የሚለዋዉጡበትና ፍሬያማ ዉይይት የሚደረግበት እንዲሆን ተመኝተዋል፡፡
እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2002 በአዲስ አበባ የተመሠረተው የፓን አፍሪካ የጠበቆች ህብረት ሲመሠረት የኢትዮጵያ ሚና ከፍተኛ መሆኑንና በወቅቱ በኢትዮጵያዊ የሕግ ባለሙያ ሲመራ እንደነበር ያስታወሱትና ከረዥም አመታት በኋላ ይህንኑ የመሪነት ሚና ወደ አገራችን በመመለስ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ የገለፁት የኢትዮጵያ ጠበቆች ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ቴዎድሮስ ጌታቸዉ ኮንፈረንሱ በኢትዮጵያ አዲስ አበባ መካሄዱ አንዱ ማሳያ ነዉ ብለዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ አያይዘዉም የህብረቱ ኮነፈረንስ በቀጣዮቹ ሶስት ቀናት የሚካሄድ ሲሆን በእነዚህ ቀናቶች ከንግድና ኢንቨሰትመንት ጋር ተያያዠ የሆኑ ጉዳዮች ፣በሁለተኛ ደረጃ ከቢዝነስ ጋር የተያያዙና ከአገሪቱ ነፃ ቀጠናዊ የንግድ ትስስርና መሰል ጉዳዮች በሶስተኛ ደረጃ ደግሞ ድንበር ዘለል የሕግ አገልግሎት ላይ እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ሌሎች በርካታ ዘርፎች ላይ ተመስርተዉ የኮንፈረንሱ ተካፋዮች በሶስት ቡድን ተከፍለዉ እንደሚወያዩ ገልፀዋል፡፡
በተጨማሪም የሕግ ባለሙያዎች፣ጠበቆችና የጥብቅና ድርጅቶች ከአገራቸዉ ወጥተዉ እንዲሰሩ ማበረታታት የኮንፈረነሱ ሌላኛዉ ዓላማ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን ባለፉት ሁለት ቀናት የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ምርጫና የካዉንስሉ ስብሰባ የተደረገ ሲሆን በቀጣዮቹ ሶስት ቀናት ደግሞ የህብረቱ አጠቃላይ ኮንፈረንስ እንደሚካሄድና በርካታ ኢትዮጵያዉያን ባለሙያዎችም በፓናሊስትነት እንደሚሳተፉ ፕሬዝዳንቱ አያይዘዉ ተናግረዋል፡፡