የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት የመንግሥት ግዥ ሥርዓትን ለመወሰንና ተቆጣጣሪ ኤጀንሲውን ለማቋቋም የወጣው አዋጅ ሥራ ላይ በዋለባቸው ዓመታት በአፈፃፀም ያጋጠሙ ችግሮችን በማስወገድ የመንግሥት የግዥ ሥርዓት ይበልጥ ግልፅ፣ ቀልጣፋ፣ ፍትሃዊና አድልዎ የሌለበት እንዲሁም ለግዥ የሚውለው ከፍተኛ የመንግሥት ገንዘብ በተሻለ አኳኋን ቁጠባን እና ውጤታማነትን ማረጋገጥ በሚያስችል ሥርዓት ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤
ከጥቅል ግዥ የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እና ቀልጣፋ አሠራር ማረጋገጥ የሚያስችል አደረጃጀት እንዲኖር ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ፤
ከፍተኛ ሀብት የሚፈስበት የመንግሥት ንብረት ለመንግሥት የተሻለ ጥቅም በሚያስገኝ አኳኋን ጥቅም ላይ እንዲውል እና አስተዳደሩም ዘመናዊ እንዲሆን ለማድረግ የሚያስችል የተቀናጀ ሥርዓት ሊዘረጋ እንደሚገባ የታመነበት በመሆኑ፤
በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 55(1) መሠረት የሚከተለው ታውጇል፡፡