አሠሪና ሠራተኛ የሥራ ግንኙነታቸውን መሠረታዊ በሆኑ መብቶችና ግዴታዎች ላይ መስርተው የኢንዱስትሪ ሠላምን በመፍጠር ለአገራችን ሁለንታናዊ ዕድገትና ልማት በመተባበር በጋራ እንዲሰሩ ማድረግ ጠቃሚ በመሆኑ፤
ሠራተኞችና አሠሪዎች የየራሳቸውን ማኅበሮች በየግላቸው በማቋቋም በመረጡአቸው ሕጋዊ ወኪሎቻቸው አማካይነት ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ የኅብረት ድርድር የማድረግ መብት እንዲኖራቸው ፣ በመካከላቸውም የሚነሳ የሥራ ክርክር በተቀላጠፈ መንገድ መፍትሔ እንዲያገኝ የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤
የአሠሪና የሠራተኛ ጉዳይ አስተዳደርን በተለይም የሥራ ሁኔታን፣ የሙያ ደኅንነትን ፤ ጤንነትና የሥራ አካባቢን በተመለከተ በሕግ መሠረት ቁጥጥር የሚያደርግ አካልን ሥልጣንና ተግባር በማጠናከር በሕግ መወሰን በማስፈለጉ፤
እነዚህን ከላይ የተመለከቱትን ዓላማዎች በትክክል በተግባር ለማዋል እንዲቻል የአሠሪና ሠራተኛ ግንኙነት የሚመራበትን መሠረታዊ ሃሣቦች እና የሥራ ሁኔታዎችን የያዘ ከመንግሥት የፖለቲካ ፣ የኢኮኖሚና የሶሻል ፖሊሲ ጋር የተገናዘበ እና ኢትዮጵያ ከፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽኖችና ሌሎች ሕጋዊ ሠነዶች ጋር የተጣጣመ ሕግ ለማውጣት በሥራ ላይ ያለውን የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ ሕግ በተሻሻለ ሕግ መተካቱ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤
በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 55(1) እና (3) መሠረት የሚከተለው ታውጇል።