አምራች እና አስቻይ የኢንቨስትመንት መስኮችን ጨምሮ በሁሉም የኢኮኖሚ ዘርፎች የግሉን ዘርፍ ሚና በማሳደግ በማበረታታት እና በማስፋፋት የአገሪቱን የኢኮኖሚ ልማት ማፋጠን፣ የእድገቱን ዘላቂነት ማረጋገጥ፣ የአገር ውስጥ የማምረት አቅምን ማጠናከር እና የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ማሻሻል አስፈላጊ መሆኑን በመገንዘብ፤
የአገራዊ ኢኮኖሚውን ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነት የሚያፋጥን፣ የወጪ ንግድን የሚያስፋፋ፣ ሰፊ እና ጥራት ያለው የሥራ ዕድል የሚፈጥር፣ እንዲሁም በተለያዩ ዘርፎች መካከል ዘላቂ እና ተመጋጋቢ ትስስርን የሚያሳልጥ የኢኮኖሚ ሥርዓት መዘርጋት በማስፈለጉ፤
ወደ አገር ውስጥ የሚገባውን የውጭ ባለሀብቶች ኢንቨስትመንት መጠን እና የተሳትፎ መስክ በማስፋት የዕውቀት፣ የክህሎት፣ እና የቴክኖሎጂ ሽግግር እና ስርጸትን ማፋጠን ተገቢ መሆኑን በመገንዘብ፤
በውጭ እና የአገር ውስጥ ኢንቨስትመንቶች መካከል ትስስርን ማስፋት፣ የኢንቨስትመንት ክልላዊ ስርጭትን ማሻሻል፣ እንዲሁም የውጭ ካፒታል በመጠቀም የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን ተወዳዳሪነት ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑን በመገንዘብ፤
ኢንቨስትመንቶች በአገራዊ የኢንቨስትመንት ዓላማዎች የተመለከቱ ግቦችን ማሳካታቸውን እንዲሁም በሕግ አግባብ መከናወናቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችል የቁጥጥር እና የክትትል ሥርዓት መዘርጋት ተገቢ መሆኑን በመገንዘብ፤
የኢንቨስትመንት ፍሰት፣ መስፋፋት፣ እና ቆይታን ማሳደግ እንዲቻል ኢንቨስትመንት የሚመራበትን ሥርዓት ይበልጥ ግልጽ፣ ተገማች፣ እና ቀልጣፋ እንዲሆን ማድረግ በማስፈለጉ፤
እነዚህን ዓላማዎች ከግብ ለማድረስ በሥራ ላይ ያለውን የኢንቨስትመንት ሕግ ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤
በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 55 (1) መሠረት የሚከተለው ታውጇል።
•
•