የሰነድ ማረጋገጥ ሥራ እምነት የሚጣልበት ማስረጃ የሚያስገኝና በአገርና በዓለም አቀፍ ደረጃ በሰዎችና በድርጅቶች መካከል የሚደረጉ የውልና ሌሎች ግንኙነቶችን የሚያመቻች በመሆኑ ፣ የሰነዶች ምዝገባ ሥራ ሰነዶች ምንጊዜም ሲፈለጉ እንዲገኙ አስተማማኝ ሁኔታ የሚፈጥር በመሆኑ፤
የሰነዶች ማረጋገጥና ምዝገባ ሥራ በአገሪቱ ውስጥ በፍርድ ቤቶችና በሌሎችም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ልምድን መሠረት በማድረግ ሲካሄድ የቆየ በመሆኑና የዚህን ሥራ ተግባራትና ሥራውን የሚያከናውኑ ተቋማትን ሥልጣንና ተግባር የሚወስን አንድ ወጥ የፌዴራል ሕግ ባለመኖሩ፤
የሰነዶች ማረጋገጥና ምዝገባ ሥራ በመላ አገሪቱ ተፈጻሚነት በሚኖረው አንድ ወጥ የፌዴራል ሕግ ቢመራ በዜጎች መካከል የሚከናወኑ የንግድና ሌሎችንም የኢኮኖሚ ግንኙነቶች በማቀላጠፍ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው በመሆኑ፤
የሰነዶች ማረጋገጥና ምዝገባ ሥራ የሚያከናወኑ ተቋማትን ተግባርና ኃላፊነት በሕግ መወሰን አስፈላጊ በመሆኑ፤
በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 55(1) መሠረት ከዚህ የሚከተለው ታውጇል፡፡
•
•
•