ቅርስ የአንድ ሕዝብ የዘመናት የኑሮ እንቅስቃሴ የሥራ እና የፈጠራ ክንውን መዘክር ስለሆነ፤
ስለሰው ፡ ስለሌላውም ምድራዊ ሕይወት ዝርያ አመጣጥ ፡ እንዲሁም ስለተጓዘበት የለውጥና የእድገት ሂደት በማጤን ተፈጥሮንና አካባቢን ይበልጥ ለመረዳት ለሚደረግ ጥናትና ምርምር ቅርሶች ምትክ የሌላቸው የመረጃ ምንጮች ስለሆኑ፤
ቅርስ ለሳይንስ እድገትና እንዲሁም በጠቅላላ የሰውን ዘር በሚመለከት እውቀት ላይ ያለው ድርሻ የጎላና ዓለም አቀፋዊ ስለሆነ፤
ኢትዮጵያ የየራሳቸው ታሪክና ባህል ያላቸው ብዙ ብሄር ብሄረሰቦችና ሕዝቦች የሚገኙባት ፡ ሕዝቦቿም ባሳለፉት የረጅም ዘመን ታሪክ በዓለም የባህል ቅርስነት የተመዘገቡትን ጨምሮ የበርካታ ቅርሶች ባለቤት ለመሆን የቻሉ ስለሆኑ፤
ተተኪው ትውልድ ስለ ማንነቱ መገለጫ ለሆነው ታሪኩና ባህሉ ጥልቅና ሰፊ ግንዛቤ ይበልጥ እንዲኖር ቅርስ ከፍተኛ ሚና ስለሚጫወት ቅርስን መንከባከብና መጠበቅ የእያንዳንዱ ዜጋ ፡የኀብረተሰቡና የመንግሥት ግዴታ በመሆኑ፤
ለቅርስ የሚያስፈልገው እንክብካቤና ጥበቃ የሚሟላበትን መንገድ መቀየስ እና በነዚሁ ላይ በማናቸውም ደረጃ የሚደረግ የጥናትና የምርምር ሥራ ሥርዓት በያዘና የሀገሪቷንና የዜጎቿን መብትና ጥቅም በሚያስጠብቅ መልክ እንዲከናወን ማድረግ ስለሚገባ ፤
በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 55(1) መሠረት የሚከተለው ታውጇል።