የእንስሳት መድኃኒትና የሕክምና መሣሪያዎች ጥራታቸዉን ፈዋሽነታቸዉንና ደህንነታቸዉን ሊያጡና ሊለወጡ ይችላሉ፡፡ በዚህም ምክንያት በሰዉና በእንስሳት ሕይወት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርሱ ስለሚችሉ ከጥሬ ዕቃ ዝግጅት ጀምሮ በአመራረት፤ በክምችት አያያዝ፤ በማስመጣት፤ በማከፋፈልና በሚላክበት ወቅት
አስፈላጊዉ ጥንቃቄና ክትትል መደረግ አለበት፡፡ ከዚህ አንፃር የእንስሳት መድኃኒትና የሕክምና መሣሪያ የማስመጣት፣ በጅምላ የማከፋፈልና የመላክ ተግባር አግባብነት ባለዉ ባለሙያ እንዲሁም መስፈርቱን ባሟላ ተቋም እንዲከናወን ማድረግ ተገቢ ነው፡፡
በዚህም መሠረት የእንስሳት መድኃኒትና መኖ አስተዳደርና ቁጥጥርን ውጤታማ በሆነ መልኩ ሥርዓት ማስያዝ አስፈላጊ በመሆኑ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጥር ወር በቁጥር 728/2004 ባወጣው አዋጅ መሠረት የእንስሳት መድኃኒትና መኖ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 272/2005 ተቋቁሟል፡፡
በመሆኑም ደህንነቱ፣ ጥራቱና ፈዋሽነቱ የተጠበቀ የእንስሳት መድኃኒትና የእንስሳት ህክምና መሣሪያዎችን አቅርቦትና አጠቃቀም ቁጥጥርን በማሻሻል የእንስሳት ሀብት ልማትንና ጤንነት አጠባበቅን በማሳደግ ረገድ ባለስልጣኑ የተሰጠውን ተግባርና ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት ያስችለው ዘንድ የእንስሳት መድኃኒትና የህክምና መሣሪያዎች አስመጪ፣ ጅምላ አከፋፋይና ላኪ ድርጅቶችን የብቃት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት አሠጣጥና ቁጥጥር በሚመለከት በአዋጅ ቁጥር 728/2004 አንቀጽ 28 ንዑስ አንቀጽ 2 በተሠጠው ሥልጣን መሠረት ይህንን መመሪያ አውጥቷል፡፡