የግብርና ትራንስፎረሜሽን ምክር ቤት አገራዊ የምግብ ሥርዓት ዕድገት እና የምግብ ዋስትናን በቤተሰብ ደረጃ ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን በበቂ ሁኔታ ለአርሶ አደሩ ለማቅረብ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ምክር ቤቱ ሕዳር 27 ቀን 2010 ዓ.ም እርምጃ እንዲወሰድ መወሰኑ እና ታህሳስ 17 ቀን 2010 ዓ.ም በደብዳቤ ቁጥር መ30-815/60 ከጠቅላይ ሚ/ር ጽ/ቤት የተላከው የውሳኔው ቃለጉባኤ መሠረት ውሳኔ ተ.ቁ. 1.2. ላይ የግብርና ሜካናይዜሽን ማሽነሪዎች፣ የመስኖ ቴክኖሎጂዎች፣ የእንስሳት እና መኖ ልማት ማቀነባበሪያ ቴክኖሎጂዎች ላይ የተጣለውን ግብርና ታክስ ለማሻሻል የተጀመረው ስራ በገንዘብ ሚ/ር በኩል የተፋጠነ ውሳኔ እንዲያገኝ፣ ለጉዳዩም ልዩ ትኩረትና ቅድሚያ በመስጠት እንዲፈጸም በተገለጸው መሠረት፡-
ሚያዚያ 28 ቀን 2011 ዓ.ም. በቁ. ማኢ. 30/7/35 ከገንዘብ ሚኒስቴር በተጻፈ ደብዳቤ ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ ውሳኔ የተሰጠባቸው የግብርና ሜካናይዜሽን ማሽነሪዎች፣ የመስኖ ቴክኖሎጂዎች፤ የእንሰሳት እና መኖ ልማት ማቀነባበሪያ ቴክኖሎጂዎች በግብርና ሚኒስቴር ፍቃድና ቁጥጥር ሥር እንዲገቡ አፈፃፀሙንም ግብርና ሚኒስቴር በየስድስት ወሩ ሪፖርት እንዲያደርግ አያይዞም በአገር ውስጥ ተመርተው የሚገኙና የሚመረቱትን ቅድሚያ በመስጠት ጥቅም ላይ ማዋል የማይቻል ከሆነ ሪፖርት ማድረግን፣እንዲሁም እቃዎቹ ለታለመለት ዓላማ መዋላቸውን ቁጥጥር እንዲያደረግ፣እቃዎቹ የተሸጡበትን ዋጋ ሪፖርት እንዲያደረግ፣ማበረታቻው በግብርናው ዘርፍ ምርትና ምረታማነት ላይ ያስከተለውን ውጤት (Impact) በጥናት እንዲያሳወቅ በተሰጠው ውክልናና ኃላፊነት መሠረትና አያይዞም መስከረም 22 ቀን 2012 ዓ.ም በተፃፈ ደብዳቤ ሌሎች ተጨማሪ መሳሪያዎች ሲፈቀዱ ቀደም ብሎ በተላለፈው መመሪያ መሠረት የግብርና ሚኒስቴር ግዴታውን እንዲወጣ ጨምሮ ባስታወቀበት እና ጥቅምት 21 ቀን 2012 ዓ.ም በቁጥር አም.አ/58/9 13 ዓይነት በግብርና ሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂዎች የሚሰጡ የኪራይ አገልግሎቶች ከዕሴት ታክስ ነፃ መደረጋቸው ሲገለፅልን እነዚህ አገልግሎቶች ይህ መመሪያ ከመተላለፉ በፊት የነበራቸው የኪራይ ዋጋ እና ተጨማሪ እሴት ታክሱ ከአገልግሎቶቹ ላይ ከተነሳ በኋላ ያለውን ኪራይ በየጊዘው ሪፖርት እንደደረግለት መጠየቁ ይህ መመሪያ እንዲወጣ ተጨማሪ መነሻ ሆኖ ተገኝቷል፡፡
ለሀገሪቱ ዕድገትና ልማት መሠረት የሆነውን የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ ምርትና ምርታማነት በማሳደግ አርሶ አደሩ፣አርብቶ አደሩ፣ከፊል አርብቶ አደሩ ከዚህ ተጠቃሚ እንዲሆኑና የግብርናውን ዘርፍ ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የተለያዩ ማበረታቻዎች በጥራት፣ በዓይነት በበቂ መጠን እንዲቀርብ በማድረግ በዘርፉ ለተሰማራው ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ በማስፈለጉ የግብርናውን ምርትና ምርታማነት በማሳደግ ቀጣይነት ያለው ልማት በሀገሪቱ ለማረጋገጥ ለግብርና አገልግሎት የሚውሉ የቴክኖሎጅ ውጤቶችና ተዛማጅ እቃዎች ከውጭ ሀገር ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው እንዲሁም በሀገር ውስጥ ተመረተው ግብርናውን ለማዘመንና ምርታማነትን ለመጨመር ይረዳ ዘንድ ለነዚህ አገልግሎት ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡትን ቴክኖሎጂና ዕቃዎች እንዲሁም በከፊል በሀገር ውስጥ የሚገጣጠሙ ከማንኛውም ቀረጥ እና ታክስ ነፃ ሆነው ተጠቃሚ ለማድረግ እና ይህንኑ በሥርዓት አስተባብሮና አቀናጅቶ መምራት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፣በአጠቃላይ የአገሪቱን ወቅታዊና ዘላቂ የግብርና ልማት ፍላጎት ለሟሟላት የሚያግዝ የግብርና ቴክኖሎጂዎችንና ዕቃዎችን አግባብ ባላቸው ህጎች መሠረት ጥራታቸውን ጠብቀው ተደራሽ እንዲሆኑ እና ቴክኖሎጂዎቹና ዕቃዎቹ ለታለመላቸው ዓላማ መዋላቸውን ለመቆጣጠር እንዲቻል መመሪያ በማስፈለጉ ይህ የአፈፃፀም መመሪያ ወጥቷል፡፡