በአንድ አገር ቴክኖሎጂዎችን የመማር፤ የማስገባት፤ የማላመድና የመጠቀም እንቅስቃሴ ውጤታማ እንዲሆን የተጠናከረ የምርምር ስርዓት ሊኖር ይገባል፡፡ በሃገራችን ውስጥ የሚደረግ ማንኛውም የምርምር ስራ የሃገሪቱን ዋና ዋና ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የሚፈታ፤ ለሃገራችን የልማት ግቦች መሳካት አስተዋፅዖ የሚያደርግና እዛው ሳለ የቴክኖሎጂ ፍላጎትን የሚያሟላ መሆን ይኖርበታል፡፡ ስለሆነም ሀገራዊው የምርምር ስርዓት ውጤታማ የሆኑ የውጭ ቴክኖሎጂዎችን በማፈላለግ፤ በመማር፤ በማላመድና በመጠቀም ረገድ የአገር ውስጥ የቴክኖሎጂ ፍላጎት ላይ እንዲያተኩር ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
አሁን በሀገራችን ባሉት የምርምር ተቋማትም ሆነ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚካሄዱ ምርምሮች ይህንን ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችል አደረጃጀት እንዲኖራቸው የማድረግና ተመራማሪዎቻችንም በዚህ ቅኝት ውስጥ እንዲገቡና ለሀገራዊ የልማት አጀንዳዎቻችን ስኬት የማይተካ ሚናቸውን እንዲወጡ የማድረግ ስራ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራ ይገባል፡፡ በመንግሥት የሚሰጡ የምርምር ድጋፎችም ይህንን እና ይህንን ብቻ እንዲያሳኩ በሚያስችላቸው መልኩ ተግባራዊ እንዲሆኑ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡
ከዚህ አንፃር በተበታተነ መልኩ እየተካሄዱ ያሉና ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የሚፈስባቸው የምርምር ስራዎች በተቀናጀ መልኩ እንዲመሩና አላስፈላጊ ድግግሞሽና የሃብት ብክነትንም ለማስቀረት፤ ብሎም የሀገሪቱን የምርምር አቅጣጫ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል አደረጃጀት፤ የአሠራር ደንቦችና መመሪያዎች ማውጣት ተገቢ ነው፡፡ በመሆኑም በየዘርፉ የምርምር ቅደም ተከተሎችን የሚያወጣ፤ በሀገሪቱ ውስጥ የሚካሄዱት ምርምሮች ከሀገሪቱ የልማት ፍላጎት ጋር የተጣጣመ መሆኑን የሚገመግም፣ በየዓመቱ የሚካሄዱትን ከሀገሪቱ የልማት ፍላጎት ጋር የሚጣጣም አዳዲስ የምርምር መስኮችን የሚለይና የሚወሰን፣ ለምርምር የሚያስፈልግ የበጀት ፍላጎት መርምሮ የውሳኔ ሃሳብ የሚያቀርብ፣ በምርምር ዙሪያ የሳይንስ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ምክር ቤትን የሚያማክር፣ አፈፃፀሙንም የሚከታተልና ፣የሚገመግም፤ የቅድሚያ ትኩረት በተሰጣቸው መስኮች ላይ የሚስተዋሉትን ክፍተቶች በመለየት አዳዲስ የምርምር ተቋማት እንዲቋቋሙ ለብሔራዊ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ምክር ቤት ምክረ ሐሳብ የሚያቀርብ አካል ብሔራዊ የሳይንስና
ቴክኖሎጂ የምርምር ካውንስል ተቋቁሟል፡፡
በዚህም መሠረት ብሔራዊ ካውንስሉ የተጣለበትን ተግባርና ኃላፊነት ለመወጣት እንዲረዳው ይህ አሠራር መመሪያ ረቂቅ ተዘጋጅቷል፡፡