በእንስሳት መኖ እና የመኖ ጥሬ ዕቃ ንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩና የሚሰማሩ ድርጅቶች የሚያመርቱትን፣ከዉጭ ወደ ሀገር የሚያስገቡትን የሚያከፋፍሉትን፣ከሀገር ወደ ውጭ የሚልኩትን እና የሚቸረችሩትን መኖና የመኖ ጥሬ ዕቃ ጥራትና ደኅንነት በማረጋገጥ የቀጥተኛ ተመጋቢዉን እንስሳ እንዲሁም የእንስሳት ምርት ተጠቃሚዉን ህብረተሰብ ጤና መጠበቅ አስፈላጊ በመሆኑ፤
ወደ ሀገር የሚገባ መኖ እና የመኖ ጥሬ ዕቃ ጥራቱና ደህንነቱ የተረጋገጠና አስፈላጊ መስፈርቶችን ያሟላ መሆኑን ማረጋገጥ አስፈላጊ በመሆኑ፤
በእንስሳት መኖ እና የመኖ ጥሬ ዕቃ ላይ በቂና ሕጋዊ ቁጥጥር ለማካሄድ የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋት አስፈላጊ በመሆኑ፤
በመኖ እና የመኖ ጥሬ ዕቃ ንግድ ሥራ ላይ ለሚሰማራ ማንኛውም ድርጅት የብቃት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት መስጠት፣መከታተልና መቆጣጠር አስፈላጊ የንግድ አሠራር ሥርዓት ሆኖ በመገኘቱ፤
የመኖ እና የመኖ ጥሬ ዕቃ ንግድ ሥራ ምዝገባና ፈቃድ አሰጣጥ ሥራዎችን ግልጽና ተጠያቂነት በሰፈነበት አሠራር ለማካሄድ እንዲቻልና ተገልጋዮችም ይህንን አውቀው መደረግ የሚገባውን ቅድመ ዝግጅት በማሟላት የአገልግሎት ጥያቄአቸውን በአግባቡ እንዲያቀርቡ ለማስቻል፤
በእንስሳት መድኃኒትና መኖ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን አዋጅ ቁጥር 728/2004 አንቀጽ28 ንዑስ አንቀጽ2 ለባለሥልጣኑ በተሰጠው ተግባርና ኃላፊነት መሠረት ይህ የመኖ አምራች አስመጪ፣ጅምላ አከፋፋይ፣ላኪ እና ችርቻሮ ንግድ ድርጅቶች የምዝገባና የሥራፈቃድየብቃትማረጋጋጫመስጫ አሠራር መመሪያ ተሻሽሎ ወጥቷል፡፡
ይህ መመሪያ ቀደም ሲል ተዘጋጅቶ ለተገልጋዮች ከተሰራጨዉ መመሪያ ቁጥር 03/2007 የሚለየዉ በንግድ ሚ/ር የመመሪያ ዝግጅት አሠራር መሠረት እንዲሁም የመኖ ችርቻሮ ንግድ ሥራን በማካተት የተዘጋጀ መሆኑ ነዉ።