ሃገራችን ከግበርና ወደ ኢንዱስትሪ የምታደርገውን መዋቅራዊ ሽግግር በተሟላ መልኩ ለመፈፀምና ቀጣይነት ያለው ልማት ለማረጋገጥ የቴክኖሎጂ አቅም መገንባት እጅግ ወሳኝና መሠረታዊ ነው፡፡ከዚህ አንፃር ቴክኖሎጂዎችን የመማር፤ የማስገባት፤ የማላመድና የመጠቀም እንቅስቃሴ ውጤታማ እንዲሆን የተጠናከረ የምርምር ስርዓት ሊኖር ይገባል፡፡ በሃገራችን ውስጥ የሚደረግ ማንኛውም የምርምር ስራ
የሃገሪቱን ዋና ዋና ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የሚፈታ፤ ለሃገራችን የልማት ግቦች መሳካት አስተዋፅዖ የሚያደርግና የቴክኖሎጂ ፍላጎትን የሚያሟላ መሆን ይኖርበታል፡፡
በመሆኑም በተበታታነ መልኩ እየተካሄዱ ያሉና ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የሚፈስባቸው የምርምር ስራዎች በተቀናጀ መልኩ እንዲመሩና አላስፈላጊ ድግግሞሽና የሃብት ብክነትንም ለማስቀረት፤ ብሎም የሀገሪቱን የምርምር አቅጣጫ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል አደረጃጀት፤ የአሠራር ደንቦችና መመሪያዎች ማውጣትና ይህንኑ በበላይነት የሚከታተልና የሚያስፈፅም ብሔራዊ የሳይንስና ቴክኖሎጂ
ምርምር ካውንስል ማቋቋም ተገቢ ይሆናል፡፡
የኢፌዲሪ አስፈፃሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 691/2003 ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከተሰጡት ተግባርና ሃላፊነቶች መካከል አንዱ በአንቀጽ 22(10) የተመለከተው የምርምር ስራዎችን ለማስተባበር የሚያግዙ ምክር ቤቶችን ያቋቁማል ፣ ያስተባብራል፣ይደግፋል በሚል የተሰጠው ሥልጣን ነው፡፡ ይህን መነሻ በማድረግ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ብሔራዊ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ምርምር ካውንስል ለማቋቋም የሚያግዝ ረቂቅ መመሪያ አዘጋጅቶ ለብሔራዊ የሳይንስ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ምክር ቤት ቀርቦ የምክር ቤቱን ይሁንታ አግኝቷል፡፡ ይህንኑ የብሔራዊ ሳይንስ፣ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ምክር ቤት ይሁንታን በመጠቀም የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር
የብሔራዊ ሳይንስና ቴክኖሎጂ የምርምር ካውንስል የማቋቋሚያና የአሠራር መመሪያ አወጥቷል፡፡
በፀደቀው መመሪያ መሠረት በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሰብሳቢነት ከግብርና ሚኒስቴር፤ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፤ ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ፤ ከገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር፤ ከትምህርት ሚኒስቴር ፤ከከፍተኛ ትምህርት ኮንሰርቲየም፤ ከግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፤ ከሳይንስ አካዳሚ፤ከቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ኤጀንሲ እንዲሁም ከንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት
የተውጣጡ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች አባል የሆኑበት ካውንስል ተቋቁሟል፡፡ ካውንስሉ ከተቋቋመ በኋላ የራሱን የምርምር ድጋፍ አሰጣጥ የውስጥ መመሪያ ያወጣ ሲሆን የዝግጅት ምዕራፍን የያዘ የእራሱን የ2006 በጀት ዓመት ቀሪ ወራት ዕቅድ አዘጋጅቶ ወደ ስራ ገብቷል፡፡ በዕቅዱ መሠረትም በ2007 በጀት ዓመት በምርምር ድጋፍ ዙሪያ ለሚሰራቸው ስራዎች የበጀት ዝግጅት አድርጎ ጥያቄውን በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በኩል ለገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር አቅርቧል፡፡
በዚሁ መሠረት ለካውንስሉ የምርምር ድጋፍ ከመንግሥት የሚመደበውን በጀት በካውንስሉ ውሳኔ መሠረት የመንግሥት የፋይናንስ ደንበ እና መመሪያን ተከትሎ ለመጠቀም እንዲቻል ከካውንስሉ የምርምር ድጋፍ አሰጣጥ የውስጥ መመሪያ በተጨማሪ ዝርዝር ጉዳዮችን የያዘ ይህ የምርምር ድጋፍ በጀት አጠቃቀምና አስተዳደር መመሪያ ተዘጋጅቷል፡፡