የአዲስ አበባ ከተማን ሁለንተናዊ እድገት ለማፋጠን ሲባል በተካሄደው የልማት እንቅስቃሴ ምክንያት በግብርና ሥራ እየተዳደሩ ከሚኖሩበት አካባቢ አርሶ አደሮች እና ቤተሰቦቻቸው ያለ በቂ ካሳ ከይዞታቸው እንዲለቁ ሲደረግ የኢኮኖሚ ተጎጂ እንዲይሆኑ ማድረግ በማስፈለጉ፤
ለከተማ አስተዳደሩ ብሎም ለሃገሪቱ የልማት እንቅስቃሴ እድገት ሲባል በልማት ምክንያት ከይዞታቸዉ የተፈናቀሉ ተጎጂ አርሶ አደሮችን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ተጠቃሚነታቸውን ማሳደግ ተገቢ መሆኑ በመታመኑ፤
የከተማ አስተዳደሩ በልማት ምክንያት ከይዞታቸዉ የተፈናቀሉ ተጎጂ አርሶ አደሮች ይዞታቸውን በማጣታቸው የመኖሪያ ቤት ችግር ተጠቂዎች እንዳይሆኑ ተገቢው የመንግሥት ድጋፍ እንዲያገኙ ማድረግ ተገቢ በመሆኑ፤
በከተማ አስተዳደሩ አማካኝነት ለከተማዋ ልማት ሲባል የልማት መብታቸው ሳይጠበቅላቸው ከይዞታቸው ለተፈናቀሉ ተጎጂ አርሶ አደሮቹ እና ቤተሰቦቻቸዉ ከደረሰባቸው ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግር እንዲወጡ ለማስቻል እና ያለባቸውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፍታት በከተማ አስተዳደር የተፈቀደ 22,915 የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በፍትሃዊነት፣ በግልጽኝነት እና በትክክለኛ ህጋዊ አሠራርን እና የአርሶ አደሮችን ነባራዊ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ መስጠት በማስፈለጉ፤
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስፈጻሚ አካላትን እንደገና ለማቋቋም በወጣው አዋጅ ቁጠር 64/2011 አንቀጽ 15 (3) (ሠ) መሠረት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአርሶ አደር እና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን ይህንን መመሪያ አውጥቷል::