በተለያዩ ጊዜያት መንግሥት በልማት ሰበብ አርሶ አደሮችን ከማፈናቀል ባለፈ የግብርና አርሶ አደሩ የመኖሪያ ቤት እና የግብርና መጠቀሚያ ባለይዞታነት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት ያልተሰጠዉና በይዞታዎቹ ላይ እንዲያለማ አልተደረገም የሚል ጉዳይ ከወቀሳ አልፎ የማኅበራዊ፣ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ አጀንዳ ሆኖ ገፍቶ የመጣ በመሆኑ የከተማ አስተዳደሩ የአርሶ አደሩን የመኖሪያ ይዞታ ዋስትናና የልማት ተጠቃሚነት ይበልጥ በማረጋገጥ ለአርሶ አደሩ ኑሮና ገቢ መሻሻል በተግባር ማሳየት አለበት የሚል እምነት በመያዙ፡፡
በዚህም መሠረት በአርሶ አደር የተያዙ የመኖሪያ ወይም የእርሻ ይዞታዎች የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት መስጠትና በከተማዉ መዋቅራዊ ፕላን መሠረት የከተማ መሬት አጠቃቀም መሠረት አርሶ አደሩ ከከተማ ግብርና ባሻገር በፕላኑ መሠረት በይዞታዉ ላይ በግለ ወይም በሕግ አግባብ ከሌሎች አርሶ አደሮች ወይም ባለሀብቶች ጋር ተደራጅቶ የተለያዩ የኢንቨስትመንት ሥራዎች ቢያከናዉን የአኗኗር ዜይቤዉን ከመቀየር ባለፈ ለሥራ ዕድል ፈጠራና ለአካባቢዉ ገጽታ ግንባታ ከፍተኛ ኣስተዋጽኦ እንደሚኖረው በመታመኑ፤
እንዲሁም ሥራ ላይ ባሉ አግባብ ባላቸው መመሪያዎች አርሶ አደሩ ለመኖሪያ ይዞታዉ እስከ 500 ካሬ ሜትር ብቻ እንደሚሰጠዉ የተገለጸ በመሆኑ ቀሪዉን ቦታ ባልተመጣጠነ የካሳ ክፍያ ይወሰድብኛል በማለት በህገ-ወጥ የመሬት ሽያጭ ዉስጥ በመግባት ለህገ-ወጥ ግንባታ ሰፊ በር የከፈተና ተመልሶም የመልካም አስተዳደር ችግር እየሆነ የመጣ በመሆኑ የከተማ አስተዳደሩ እነዚህን ችግሮች ሥርዓት ማስያዝ እንደለበት በማመኑ፤
ከዚህም በመነሳት አርሶ አደሩ የከተማዉ ፕላን በሚፈቅደዉ አግባብ በራሱ ይዞታ ላይ እንዲያለማ፣ ፍትሃዊነት እንዲሰፍን እና ህገ-ወጥ የመሬት ወረራን መከላከል እንዲቻል በቅድሚያ አርሶ አደሩ ለመኖሪያና ለከተማ ግብርና መጠቀሚያ የይዞታ ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት እንዲሰጠዉ ማድረግ እና የልማት ተጠቃሚነቱን ማረጋገጥ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤
የአዲስ አበባ ከተማ ካቢኔ የከተማ ቦታን በሊዝ ስለመያዝ በወጣው አዋጅ ቁጥር 721/2004 አንቀጽ 33 ንዑስ አንቀጽ (2) መሠረት ይህን መመሪያ አውጥቷል።