አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አትሌቲክስ ፌደሬሽን በአስተዳደሩ ውስጥ በተለያዩ እርከኖች በሚገኙ የከተማ፤ የክፍለ ከተማ፣ የወረዳ፣ የድርጅትና የክለቦችን የአትሌቲክስን ስፖርት ለማስፋፋት፣ ለማደራጀትና ለማጠናከር በከተማ አስተዳደሩ ስፖርት ኮሚሽን እንዲሁም በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ህጋዊ ሥልጣን የተሰጠው አካል መሆኑ ይታወቃል፡፡
ሰለሆነም ፌዴሬሽኑ በአዲስ መልክ ሥራዎችን ለመሥራት ብሎም የከተማውን የአትሌቲክስ ስፖርት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስና በከተማችን፤ በሀገር፣ በአህጉር እና በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የውድድር መድረኮች በአትሌቲክሱ መስክ ያላንን ተወዳዳሪነት ለማሣደግ ተልዕኮ እና ራዕዩን ሊያሳኩ የሚችሉ ልዩ ልዩ መመሪያዎችና አሠራሮች አዘጋጅቷል፡፡
ፌዴሬሽኑ የከተማ አስተዳደሩን ስፖርት ምክር ቤት፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን፣ የአህጉርና የዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንን መመሪያዎች ባገናዘበና በማይጻረር መልኩ የአዲስ አበባን አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መተዳደሪ መመሪያ አሻሽሎ ማዘጋጀት አስፈላጊ ሆኖ በማግኘቱ ይህን መተዳደሪያ መመሪያ አውጥቷል፡፡
የስፖርቱ አመራር አካላት፣ አሰልጣኞች፣ ዳኞች፣ ሙያተኞች በየደረጃው የሚገኙ አባል ክለቦችና ክፍለ-ከተማዎች በስራቸው ታቅፈው የሚገኙ አትሌቶች በጠቅላላ ጉባኤው ጸድቆ የወጣውን መተዳደሪያ ደንብ የማክበርና ተግባራዊ የማድረግ ኃላፊነት ስለላባቸው ተፈጻሚ እንድታደርጉ እናሳዉቃለን፡፡
በመሆኑም ለዚህ የዓላማ ስኬት ያግዘው ዘንድ የክለቦች የፕሮጀክቶችና የልዩ ልዩ ቡድኖችን አደረጃጀት በመፈተሽ እንዲጠናከሩ፣ የውጤታማነትና የተፎካካሪነት ስሜታቸውን ከፍ በማድረግ የላቀ ብቃትና የጥራት ደረጃ ያላቸውን አትሌቶች ማፍራት እንዲችሉ ብሎም በሂደት ከድጐማ ወጥተው ራሳቸውን በፋይናንስ የሚችሉበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ደመወዝ፣ ትጥቅ፣ ምግብ፣ ሕክምና ወዘተ… የመሳሰሉ በርካታ ወጪዎችን አውጥተው በሚያበቋቸው አትሌቶች ቀጥተኛ ተጠቃሚነታቸው እንዲረጋገጥ በማሰብ በአትሌቲክሱ ስፖርት ላይ የሚሠሩ የስፖርት ማህበራትንና ተቋማትን ወደ አትራፊነት (ወደ ቢዝነስ አስተሳሰብ) ሥርዓት በመቀየር ተግባራዊ ይሆን ዘንድ ይህ የክለቦች፣ የፕሮጀክቶችና የልዩ ልዩ ቡድኖች ማቋቋሚያ መመሪያ ወጥቷል፡፡