ለፉት ዓመታት በመንግሥት አስተባባሪነትና ድጋፍ በክልሎችና በአዲስ አበባ ከ200 ሺሀ በላይ መኖሪያ ቤቶች ተገንብተው ከ60 በመቶ በላይ ለተጠቃሚዎች ማስተላለፍ የተቻለ ቢሆንም ከችግሩ ስፋትና ውስብስብነት አንጻር በከተሞች የቤት እጥረትና ተያያዥ የሆኑ አገልግሎቶችን ችግር ምላሽ ለመስጠት መንግሥት ብቻውን የሚወጣው ባለመሆኑ የቁጠባ መኖሪያ ቤት ገንብቶ ለተጠቃሚዎች ለማስተላለፍ የተነደፈውን የቤት አቅርቦት አማራጭ ስትራቴጂ ማስፈጸም በማስፈለጉ፣
በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ እየተባባሰ የመጣውን የቤት እጥረት ችግር ለመፍታት ህብረተሰቡ ለቤት መስሪያ የሚሆን ገንዘብ የመቆጠብ ባህሉ አለመዳበርና በፋይናንስ ተቋማትም በኩል ለቤት መስሪያ ብድር የማቅረብ አቅምና ተደራሽነት ውስን በመሆኑ፣ ከህብረተሰቡ በሚገኝ ቁጠባና ተመጣጣኝ ብድር በማዘጋጀት የቤት ችግርን ለመፍታት የተቀረጸውን ፖሊሲ ተግባራዊ ለማድረግ የቁጠባና ብድር አሠራር ስርዓት መዘርጋት በማስፈለጉ፤
የ40/60 ቁጠባ ቤቶች ልማት ፕሮግራም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከተጀመሩ ሌሎች የ10/90፣ 20 SO እና የመኖሪያ ቤት ህብረት ስራ ማህበራት የቤት ልማት ፕሮግራሞች ተመዝጋቢ ቤት ፈላጊዎች ጋር መረጃው ተናባቢ እንዲሆን ለማድረግ የሚያስችል የምዝገባና መረጃ አደረጃጀት ስርዓት መፍጠር በማስፈለጉ፣
በመንግሥት አዲስ ከተቀረጹት የቤት ልማት ፕሮግራሞች ውስጥ አንዱ የ40/60 ቤቶች ልማት ፕሮግራም ሲሆን በፕሮግራሙ ተጠቃሚ የሚሆኑ ግለሰቦችን ለመለየትና ሊያሟሉት የሚገባቸውን ቅድመ ሁኔታ እንዲያውቁት በማድረግ ምዝገባው ግልጽና ፍትሃዊ እንዲሆን ማድረግና አስፈጻሚ፣ ፈጻሚና በምዝው አፈጻጸም የሚሳተፉ ባለድርሻ አካላትን ተግባርና ኃላፊነት እንዲሁም ተጠያቂነት መወሰን በማስፈለጉ፤
የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ፖሊሲና ህጎችን ለማመንጨትና በስራ ላይ መዋላቸውን ለማረጋገጥ እንዲሁም በጸደቀው የ40/60 ቁጠባ ቤቶች ልማት ስትራቴጂ መሠረት ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በመተባበር የከተማ ነዋሪው ሕዝብ ከአቅሙ ጋር የተመጣጠነ መኖሪያ ቤት እንዲሰራ አጠቃላይ አቅጣጫ ለመቀየስ እና የአቅም ግንባታ ድጋፍ ለመስት በአዋጅ ቁጥር 691/2003 አንቀጽ 10 ንዑስ አንቀጽ 1 (ሀ) እና (ለ) እንዲሁም አንቀጽ 25 ንዑስ አንቀጽ 1 (ሪ) በተሰጠው ኃላፊነት መሠረት ይህን መመሪያ አውጥቷል።