በህንፃ አዋጅ አፈፃፀም ዙሪያ በተደረገ ጥናት ግኝት መሰረት በአብዛኛዉ የህግ እና የአሰራር ክፍተቶች እንዳለባቸዉ ተመላከተ

Study on Building Proclamation Implementation Reveals Significant Legal and Procedural Gaps

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር በፌዴራል የህንፃ አዋጅ ቁጥር 624/2001 ማስፈፀሚያ ሕግጋት አፈፃፀም በተሰራ የዳሰሳ ጥናት ዙሪያ የተቋማት ሚኒስቴር ዲኤታዎች፣ ዳይሬክተሮች፣ የማህበራት ተወካዮችና ባለሙያዎች በተገኙበት በዛሬዉ እለት በአዲስ አበባ ከተማ ዉይይት አካሂዷል፡፡

በዚህ ወቅት የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥና የዜጎችን መብት ለማስጠበቅ በመንግሥትና በግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ የሚሰሩ ስራዎችንና የሚሰጡ አገልግሎቶችን በሕግ አግባብ መምራትና የአሠራር ክፍተት ሲኖርም አስፈላጊዉን የእርምት ርምጃ እንዲወሰድ ማድረግ እንደሚገባ የገለፁትና ዉይይቱን በንግግር የከፈቱት በፍትሕ ሚኒስቴር የመንግሥት ሕግና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አለምአንተ አግደዉ ከዚህ አንፃር የግንባታ ክፍለ ኢኮኖሚዉ የሚመራበትና የሚተዳደርበት የሕግ ማዕቀፍ በአዋጅ ቁጥር 624/2001 ጸድቆ ወደ ስራ ከገባ ከአስር አመታት በላይ ማስቆጠሩን ገልፀዋል፡፡

የዚሁ አዋጅ መሠረታዊ ዓላማም ነዋሪዎች ጥራአቱና ንፅህናዉ በጠበቀ አቅርቦትና ተደራሽነትን ባማከለ መልኩ በተገነባ የመኖሪያ አካባቢና ህዝባዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት እንዲገለገሉና እንዲኖሩ ማስቻል መሆኑና ይህ ሊሆን የሚችለዉ ደግሞ ህንፃዎች አለምአቀፋዊና ሀገር አቀፍ የግንባታ መርሆዎችንና ሕግጋትን መሠረት አድርገዉ ከቅድመ ግንባታ ጀምሮ በሕግ መሠረት መሰራቱን ቁጥጥር ሲደረግበትና ሁሉንም ህብረተሰብ ባሳተፈና ተጠቃሚ ባደረገ መልኩ አገልግሎት ሲሰጥ መሆኑን በመግለፅ ጥናቱም የአዋጁን አፈፃፀም በመመርመር የጋራ ግንዛቤ በመያዝ ክፍተቶችን አርሞ ወደፊት የህጉን ተፈፃሚነት ማረጋገጥ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

የዳሰሳ ጥናቱን አስመልክቶ አጠቃላይ ማብራሪያ ያቀረቡት በፍትሕ ሚኒስቴር የፌዴራል ህጎች ተፈፃሚነት መከታተያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ትብለጥ ቡሽራ ተቋሙ በአዋጅ በተሰጠዉ ሥልጣን መሠረት የህጎችን ተፈፃሚነት መከታተል አንደኛዉ ተግባሩ መሆኑን በመጠቆም ከደኅንነትና ከተደራሽነት አንፃር ያለዉን የአሠራርና የሕግ ክፍተት መፈተሸ አስፈላጊ በመሆኑ የህንፃ አዋጅ ላይ ጥናት መደረጉን ገልፀዋል፡፡

የጥናቱ ዋና ዓላማም በዲዛይንና በግንባታ ወቅት እንዲሁም ግንባታቸዉ በከፊልና በሙሉ የተጠናቀቁ ህንፃዎች ከደኅንነትና ከተደራሽነት አንፃር ያሉበትን ቁመና መርምሮ ለባለድርሻ አካላት ማሳወቅና መፍትሄ ማስቀመጥ መሆኑን የገለፁት ዳይሬክተሯ ጥናቱም ወሰኑን አዲስ አበባ በሚገኙ ህንፃዎች ላይ ብቻ አድርጎ መካሄዱን ተናግረዋል፡፡

ቀጥሎም የአዋጁ አፈፃፀም፣ የህንፃ አዋጁን ለማስፈፀም ኃላፊነት የተጣለባቸዉ አስፈፃሚ አካላት ምንነትና አፈፃፀም ዳሰሳና የጥናቱ መደምደሚያና ምክረ ሀሳብ በጥናት ቡድኑ አባላት በኩል ቀርቦ ሰፋ ያለ የጥያቄና የዉይይት ተካሂዶበታል፡፡

በጥናቱ ግኝትም በአብዛኛዉ በዲዛይንና በግንባታ ደረጃ እንዲሁም ግንባታቸዉ በሙሉና በከፊል በተጠናቀቁ ህንፃዎች ላይ የአዋጁን አፈፃፀም አስመልክቶ አብዛኛዎቹ የህንፃ አዋጁን አስገዳጅ መስፈርቶች የማያሟሉና በሕግ፣ በአሠራርና በአደረጃጀት ሊደገፉ የሚገባቸዉ መሆኑ የተመላከተ ሲሆን ስለ ህንፃዎች ሕግጋትም ለባለድርሻ አካላት በቂ የሆነ ግንዛቤ ሊፈጠርለት እንደሚገባ በመፍትሄነት ተጠቁሟል፡፡

በመጨረሻም በጥናቱ ለተሳተፉ ባለ ድርሻ አካላት ማለትም ከፍትሕ ሚኒስቴር፣ ከአዲስ አበባ ግንባታና ቁጥጥር ባለሥልጣን፣ ከኢትዮጵያ ኮንስትራክሽንና ከኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽንን ወክለዉ በጥናቱ ለተሳተፉ ባለሙያዎች እዉቅና በመስጠትና በማመስገን ዉይይቱ ተጠናቋል፡፡

Tagged Under: Legal Gaps
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች

ተመሳሳይ ዜናዎች

No data was found