የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር በሕክምና እና ተያያዥ የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን አስመልክቶ በተዘጋጀው የምርመራና የክስ ማንዋል ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡
በውይይት መድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት በተቋሙ የሕግ ጥናት ማርቀቅና ማጠቃለል ዳይሬክቶሬት ጀኔራል ምክትል ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ጉደታ ቀነአ እንደተናገሩት በህክምና አገልግሎት አሰጣጡ ላይ በስራ ሂደቶች ውስጥ የተለያዩ ችግሮች እየተፈጠሩና ወንጀሎች እየተፈጸሙ እንደሆነ አንስተው፤ ከዚህም ጋር በተያያዘ እንደ አንድ መፍትሔ ተጠያቂነትን ለማስፈን እና የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ለመቀነስ ሲባል የክስና የምርመራ ማንዋሉ ተዘጋጅቷል፡፡
በመድረኩ በቀዳሚነት በሀገራችን የጤና ህጉ እና የህክምና ስህተት ምን እንደሚመስል የሚያሳይ የዳሰሳ ጥናት ቀርቧል፡፡
የክስና የምርመራ ማንዋሉ ዓላማ በሕክምና ሙያ አገልግሎት የሚፈጸም ወንጀል ምርመራና ክስ የሚመራባቸውን መርሆዎች እና ዋና ዋና ሕግጋት ማስተዋወቅ፣ በአግባቡም እንዲተገበሩ ማገዝ፣ የምርመራና ክስ አመሰራረቱ የጤና ሙያን ልዩ ባህሪ ያገናዘበ እንዲሆን ማድረግ፣ የጤና፣ የአካል ደኅንነት እና ሌሎች የታካሚ ወይም የተጎጂ መብትና ጥቅም በማክበርና በማስከበር የጤና አገልግሎት ተጠቃሚውንና የሕብረተሰቡን ሰላምና ደኅንነት ማረጋገጥ መሆኑን በቀረበው ሰነድ ተመላክቷል፡፡
ከጤና ጋር በተያያዙ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ምርመራ ውጤታማ እንዲሆን ማስቻል እና የፖሊስ እና የዐ/ሕግ ተቋም የተቋቋሙበትን አይነተኛ ዓላማ ማሳካት የሰነዱ ተጨማሪ ዓላማ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን የአፍሪካ ሀገራት ማለትም የጋና፣የደቡብ አፍሪካ፣የኬንያና የናይጀሪያ ተሞክሮዎችም በሰነድ ዝግጅቱ ወቅት መወሰዳቸው ተገልጿል፡፡
ከክልልና ከፌዴራል የተውጣጡ በዘርፉ የተሰማሩ ባለድርሻ አካላት በመድረኩ ላይ የተሳተፉበት ሲሆን በቀረቡት ሰነዶች ላይም ሰፊ ውይይት ከተደረገ በኋላ ለግብዓትነት የተነሱ ሀሳቦች ተወስደው የዕለቱ መርኃ-ግብር ተጠናቋል፡፡