በዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ ላይ 1ኛ መርጌታ ምስጥሩ ይግዛው፣ 2ኛ ዘውዲቱ ገብሬ እና 3ኛ ብሩክ ቸኮል የተባሉት ተከሳሾች ጥቅምት 6 ቀን 2015 ዓ.ም ከቀኑ በግምት 10፡00 ሲሆን በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 አያት ጣዕመ ዳቦ ቤት አካባቢ 2ኛ ተከሳሽ በቤት ሠራተኛነት ተቀጥራ ስትሰራበት የነበረውን ቤት ለቃ ከሄደች በኋላ ህጻን ጠልፈው ብር ለመቀበል ከ1ኛ ተከሳሽ ጋር በመስማማት ተመልሳ ለቃ ወደሄደችው ቤት በመመለስና በቤት ሠራተኛነት ተቀጥራ ለመቀጠል በመስማማት ከምትሰራበት ቤት ዕድሜው 2 ዓመት ከ11 ወር የሆነውን ህጻን ሳሙኤል ዮሃንስን ማስቲካ ልግዛለት በማለት አታልላ ይዛው ከቤት ከወጣች በኋላ በአካባቢው ይጠብቋት ከነበሩ 1ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች ጋር በመገናኘት ህጻኑን ይዘው ወደ ኦሮሚያ ክልል ኢጅሬ ወረዳ አዲስ አለም ከተማ ጨረታ ሰፈር በሚገኘው 1ኛ ተከሳሽ አስቀድሞ በተከራየው ቤት ወስደው ይደብቁታል፡፡
1ኛ ተከሳሽም ለህፃኑ ወላጆች ስልክ በመደወል 10 ሚሊዮን ብር ክፈሉና ልጁን ውሰዱት አለበለዚያ እንሸጠዋለን፣ ኩላሊቱ ሱዳን ይፈለጋል፣ ጎንደር አዞዞ ተራራ ላይ ሄዳችሁ አስከሬኑን ውሰዱ በማለት፣ 2ኛ ተከሳሽም ቶሎ ብሩን ክፈሉ ልጁን መተማ ሊወስዱት ነው እኔንም እጄን ቆርጠውኛል በማለት፣ 3ኛ ተከሳሽም የግል ተበዳይ ወላጅ አባት ጋር ስልክ በመደወል አስፈራርቶ ገንዘቡን ለመቀበል እየተደራደሩ እያለ በመያዛቸው ምክንያት በፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ በሴቶችና ህጻናት ላይ ሚፈፀሙ ወንጀሎች ዐቃቤ ሕግ ዳይሬክቶሬት በወ/ሕ/አ 32/1/ሀ/፣ 590/1/ለ እና /2/ሠ መሠረት በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ልዩ ልዩ ወንጀል ችሎት ክስ አቅርቦባቸው ክርክር ሲደረግ ቆይቷል፡፡
በክርክሩ ሂደትም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃ ከተሰማ በኋላ ተከሳሾች እንዲከላከሉ ብይን ተሰጥቶ የመከላከያ ማስረጃቸውን አቅርበው ያሰሙ ቢሆንም የቀረበባቸውን ማስረጃ መከላከል ባለመቻላቸው ዐቃቤ ሕግ ባቀረበው ክስ መሠረት የጥፋተኛነት ፍርድ በመስጠት 1ኛ ተከሳሽ በ7 ዓመት ፅኑ እስራት፣ 2ኛ ተከሳሽ በ6 ዓመት ፅኑ እስራት እና እንዲሁም 3ኛ ተከሳሽ በ5 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ሲል ወስኖባቸዋል፡፡