በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ፌዴራል ህጎች ተፈፃሚነት መከታተያ ዳይሬክቶሬት የህንፃ አዋጅ ቁጥር 624/2001 ምክረ-ሀሳቦች አተገባበር ላይ ዳግም ክትትል ሪፖርት አስመልክቶ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ አባላት፣ ከከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለሥልጣንና ሌሎች ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ሰኔ 18 ቀን 2017 ዓ.ም ውይይት ተካሂዷል፡፡
በፍትሕ ሚኒስቴር የፌዴራል ህጎች ተፈፃሚነት መከታተያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሪት ሀወኒ ታደሰ የፍትሕ ሚኒስቴር የፌዴራል ህጎች ወጥ በሆነ መልኩ መፈፀማቸውን፣ ህጎች ለወጣላቸው ዓላማ ተግባራዊ መሆናቸውን ማረጋገጥ በአዋጅ ቁጥር 943/2008 አንቀጽ 6(6)መሠረት የተሰጠው ኃላፊነት መሆኑን ጠቅሰው በ2013 ዓ.ም በአዋጁ አፈፃፀም የክትትል ግኝቶች ዙሪያ ከየተቋማቱ ተገቢውን መረጃ ሊሰጥ ከሚችል የበላይ ኃላፊ ጋር በእያንዳንዱ ምክረ ሀሳብ ላይ ውይይት መደረጉን እና ኃላፊነት የተወሰደበት ጉዳይ መሆኑን አውስተዋል፡፡
ክትትሉ ከተደረገ ወዲህ በተሰጠው ምክረ-ሀሳብ መሠረት የተከናወኑ የሕግ እና የአሠራር ማሻሻያ ስራዎችን የሚያሳዩ የሰነድ ማስረጃዎችን፣ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ሕዝብ ተወካይች ምክር ቤት ሪፖርቶች፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በአዲስ አበባ የሚገኙ ሕንጻዎች ለአካል ጉዳተኞች ባላቸው ተደራሽነት ሁኔታ የተዘጋጀ ግልጽ አቤቱታ መቀበያ መድረክ እና የሚዲያ ዳሰሳ በማድረግ ሪፖርቱ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡
የመድረኩ ዓላማ በቀድሞ ክትትል ላይ የተሰጡ ምክረ-ሀሳቦች ተግባራዊ ስለመደረጋቸው ወይም አለመደረጋቸው መለየት፣ የአተገባበር ሁኔታቸው ያለበትን ደረጃ መለየት እና ተግባራዊ ያልተደረጉ ምክረ-ሀሳቦች ካሉ ምክንያታቸውንና በዚህ ረገድ ተቋሙ የወሰደውን አቋም ወይም እርምጃ ማየት መሆኑ ተገልፁዋል፡፡
ቀድሞ በክትትል ግኝት የተመላከቱ ምክረ-ሀሳቦችን መፈፃቸውን ለማረጋገጥ የተሰራው የዳግም ክትትል ሪፖርት በዝርዝር የቀረበ ሲሆን፤ ሪፖርቱ የህንፃ አዋጅ በሕግ ቀድሞ የተሰጡ ምክረ ሀሳቦች የተሻሻሉትን እንዲሁም ሳይፈጸሙ የቀሩ የምክረ-ሀሳብና የሕግ ድንጋጌዎቹን በግልፅ አመላክቷል፡፡
ከነዚህም ውስጥ በአዋጁ የተቀመጡ ምክረ ሀሳቦችን በማካተት እንዲሻሻል በተመላከተው መሠረት ያለግንባታ ፍቃድ ግንባታ ማካሄድና ያለተቆጣጣሪ የግንባታ ስራ መጀመር ተጨማሪ ጥናት ተደርጎ በሕንጻ ባለቤቱ፤ በስራ ተቋራጩ፤ በአማካሪው ላይ የፍትሐብሄር እና አስተዳደራዊ ቅጣቶችን መጣል የሚያስችል ሆኖ እንዲካተት ፣በሕንጻ ግንባታ ወቅት ለሰራተኞች የሚሰሩ መወጣጫዎች እና መሰላሎችን የመሳሰሉት በእንጨት መሥራት ቀርቶ በአስገዳጅ ሁኔታ በብረት የሚሰራበት አሠራር እንዲዘረጋ መደረጉ እና ሌሎች መሰል ምክረ ሀሳቦችን ማካተት መቻሉ የተመላከተ ሲሆን፤ ከዚህ በተጨማሪ የአሠራር ማሻሻያዎችን በተመለከተ እየለማ ያለው Construction Safety Information Management System (CSIMS) ሶፍትዌር በቀድሞ ክትትል ላይ ከተሰጡት የአሠራር ማሻሻያዎች በግብአትነት ተወስዶ ተግባራዊ መደረጉ እንደጠንካራ ጎን የተወሰዱ ናቸው።
ከታዩት መሻሻያች በተቃራኒ ደግሞ በቂ ወይም ምንም አይነት ማሻሻያ ያልተደረገባቸው ሲኖሩ ለአብነትም ለአገልግሎት ብቁ ናቸው የሚባሉ ሕንጻዎች ላይ የክትትል ስራዎች እየተሰሩ ቢሆንም በተለይም ከአካል ጉዳተኞች ጋር ተያይዞ ያለዉ የተደራሽነት እና አካታችነት ችግሮች እንደቀጠሉ መሆኑ፣ አደጋዎች ሲደርሱ ለፖሊስ የማሳወቅ ስራዎች አለመሰራታቸው፣ ያልተቀረፉ መሆናቸው እንደ ድክመት የታዩ መሆናቸው በቀረበው ሰነድ ተመላክቷል፡፡
ከመድረኩ የተነሱትን ወሳኝ እና ጠቋሚ ግብአቶች በመውሰድ የዳግም ክትትሉ ሊያሻሽላቸው የሚገቡ ጉዳዮችን በመለየት በቀጣይ በመድረኩ የተገኙ ባለድርሻ አካላት ቅንጅት ፎረም መመስረት እንደሚገባቸውና ለምክረ-ሀሳቦቹ ማስተግበሪያ የጋራ ድርጊት መርሀ ግብር እና እቅድ የሚዘጋጅ መሆኑን ተመላክተዋል፡፡