የሴቶች መብቶች

ማውጫ

Share this Article

መግቢያ

ጥቃት በዓለም ዓቀፍ ደረጃ በተለያዩ መልኩ የሚፈጸም እኩይ ተግባር ሆኖ በሰዎች አካል፣ ደኅንነት፣ ህይወት እና ንብረት ላይ ጉዳት የሚያደርስ ድርጊት ነው፡፡ ጥቃት የሌላዉን አካል ነፃ ፈቃድ በመጣስ ይፈፀማል፡፡ ኃይልን ወይም ሥልጣንን በመጠቀም ያለ ተጎጅዎች ነጻ ፈቃድ የሚፈጸም የመብት ጥሰት ነዉ፡፡ በመሆኑም ጥቃት ሰዎች ሰዉ በመሆናቸዉ ብቻ የተጎናጸፏቸዉን እና በተለያዩ ዓለም ዓቀፍ ሰነዶች እዉቅና የተሰጣቸዉን ሰብዓዊ መብቶች የሚጥስ ድርጊት ነዉ፡፡ በሴቶች ላይ ጥቃት ማለት አካላዊ ጥቃትን ብቻ አይደለም በጣም ሰፋ ያለ እና ወሲባዊ፣ ስሜታዊ፣ ስነልቦናዊ እና የኢኮኖሚ ጥቃትን ያጠቃልላል። በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃትን ለማስወገድ ያወጣው መግለጫ የሚከተለውን ፍቺ ይሰጣል”በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃት የሚለው ቃል ጾታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች በሴቶች ላይ አካላዊ፣ ጾታዊ ወይም ስነ ልቦናዊ ጉዳት ወይም ስቃይ የሚያስከትል ወይም ሊያስከትል የሚችል ማንኛውንም ድርጊት ማለት ሲሆን ይህም የእንደዚህ አይነት ድርጊቶች በሕዝብ ወይም በግል ሕይወት ውስጥ የሚከሰት ማስፈራራት፣ ማስገደድ ወይም የዘፈቀደ የነጻነት መንፈግ በምሳሌነት ሊነሳ ይችላል፡፡ በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃት በአጠቃላይ ጾታን መሠረት ያደረገ ሲሆን በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃት ተብሎ ይጠራል፡፡

የሴቶች መብት በዓለም ዓቀፍ ህጎች

በተባበሩት መንግስታት እና በአህጉራዊ የሰብዓዊ መብት ስርዓቶች ውስጥ ሴቶች በተለይ ለአደጋ ተጋላጭ ቡድን ውስጥ በመመደብ በልዩ ሁኔታ ጥበቃ ተሰጥቷቸው ይገኛል፡፡ ለሴቶች መብት እውቅና የሰጡ ስምምነቶችን በሁለት ከፍለን ማየት የምንችል ሲሆን እነሱም ጠቅላላ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶች እና በልዩ ሁኔታ በሴቶች ላይ የተደረጉ ስምምነቶች ናቸው፡፡ ከጠቅላላ ስምምነቶች እንደ አብነት ብንመለከት :-

ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች መግለጫ (UDHR,1948)

በሰብዓዊ መብት መግለጫው እንደተደነገገው ማንኛውም ሰው በዘር፣ በቀለም፣ በጾታ፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ ወይም በሌላ አመለካከት፣ በብሔር ወይም በማኅበራዊ አመጣጥ፣ በንብረት፣ በትውልድ ወይም በሌላ አቋም ልዩነት ሳይደረግ በአዋጁ ውስጥ የተገለጹትን ሁሉንም መብቶችና ነጻነቶች የማግኘት መብት እንዳለው ያስቀምጣል፡፡ በመሆኑም ሴቶች እንደማንኛውም ሰው ጾታን መሠረት ባደረገ መልኩ ልዩነት ሳይደረግባቸው የሰብዓዊ መብቶች ተጠቃሚ መሆን እንዳለባቸው መገንዘብ ይቻላል፡፡ በተመሳሳይ ዓለም ዓቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ስምምነት (ICCPR,1966) እና ዓለም ዓቀፍ የኢኮኖሚዊ፣ የማኅበራዊና ባህላዊ መብቶች ስምምነት (ICESCR,1966) የስምምነቶቹ አባል የሆኑ መንግስታት በስምምነቶቹ የተዘረዘሩትን ሁሉንም የሲቪል እና የፖለቲካ ፣ኢኮኖሚያዊ መብቶች ለማስከበር የወንዶች እና የሴቶችን እኩል መብት ለማረጋገጥ እንደሚሰሩ እና ተገቢ እርምጃዎችን (ህጋዊ፣ አስተዳደራዊ እና የፖሊሲ) እንዲወስዱ ያስገድዳል፡፡

በሴቶች ላይ የተደረጉ ልዩ ዓለም ዓቀፍ ስምምነቶች

በሴቶች ላይ የሚደረጉ ማናቸውም ዓይነት ልዩነት ወይም አድሎ ለማስወገድ የወጣ ስምምነት (The Convention on the Elimination of All Forms of Discrimination against Women (CEDAW) ,1979)

ኮንቬንሽኑ በሴቶች ላይ የሚደርሰውን መድልዎ ሲተረጉም “…በሴቶች ላይ የሚደረግ አድሏዊ ልዩነት ማለት ጾታን መሠረት በማድረግ ሴቶች አገቡም አላገቡ፤ ከወንዶች ጋር በእኩልነት በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊና ባህላዊ፤ በሲቪልና ሌሎች መስኮች የሰብኣዊ መብቶች እና ነጻነቶች ሙሉ ተጠቃሚ እንዳይሆኑ የሚያደርግ ማንኛውም ልዩነት፣ ማግለል ወይም ገደብ ማለት ነው” ፡፡ ኮንቬንሽኑ በሁሉም ዘርፍ በሴቶች እና ልጃገረዶች ላይ የሚደርሰውን መድሎ እንዲያስወግድ እና የሴቶች እና ልጃገረዶች እኩል መብቶችን የሚያበረታታ ዓለም ዓቀፍ የሕግ መሳሪያ ነው።የስምምነቱ መንፈስ በተባበሩት መንግስታት ግቦች ላይ የተመሰረተ ሆኖ በመሠረታዊ ሰብዓዊ መብቶች፣ በሰው ልጅ ክብር እና ዋጋ ላይ እምነትን በማረጋገጥ በወንዶች እና በሴቶች እኩል መብቶች ማምጣት ነው፡፡

በሴቶች ላይ የሚፈጸም ማንኛዉም አይነት የሃይል ተግባራትን ወይም ጥቃትን ለማስወገድ የወጣ መግለጫ (Declaration on the Elimination of Violence Against Women (DEVAW), 1993)

በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ሲገልፅ “በስራ ቦታ፣ በትምህርት ተቋማት ወይም በሌሎች ቦታዎች ወሲባዊ ትንኮሳ እና ማስፈራራትን ያጠቃልላል”በማለት ሀገራት ጾታዊ ትንኮሳና ሌሎች በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን እና መሰል ድርጊቶችን ለመከላከልና ለመመርመር ሊሰሩ እንደሚገባ እና በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከል ሁሉን አቀፍ የሕግ፣ፖለቲካዊ፣አስተዳደራዊ እና ባህላዊ ፕሮግራሞችን ማዘጋጀት እንዳለባቸው ያስቀምጣል፡፡

የአፍሪካ የሰብዓዊና የሕዝቦች መብት ቻርተር (ACHPR, 1981)

መንግሥታት በዓለም ዓቀፍ ስምምነቶች ላይ እንደተደነገገው በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ማንኛውንም አድልዎ እንዲወገድ በማድረግ ለሴቶች እና ሕፃናት መብቶች ጥበቃን ማረጋገጥ እንዳለባቸው ያስቀምጣል፡፡ እንዲሁም በአፍሪካ የሴቶች መብት ቻርተር ፕሮቶኮል (Protocol to the African Charter on the Rights of Women in Africa) ሴቶች የመከባበር መብት እንዳላቸው ፣ በጋብቻ ውስጥ የእኩልነት መብት እና ልጅ ለመውለድ የመወሰን መብት እንዳላቸው እና በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ችግርም በማካተት ለሴቶች መብት ጥበቃ ትኩረት ሰጥቶ ይገኛል፡፡

በሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃትን ለመከላከል፣ ለመቅጣት እና ለማጥፋት የወጣ የኢንተር አሜሪካን ኮንቬንሽን (Inter-American Convention on the Prevention, Punishment and Eradication of Violence Against Women)

በኮንቬክሽኑ እንደተደነገገው ጥቃት የአንዲትን ሴት “የሲቪል፣ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊ እና የባህል መብቶቿን በነጻ እና ሙሉ በሙሉ እንዳትጠቀም” እንደሚከለክላት በመገንዘብ በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከል፣ ለመቅጣት እና ለማጥፋት አወንታዊ እርምጃዎች እንዲወስዱ እና በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ወይም መድሎዎች የሚያስከትሉትን ማኅበራዊ እና ባህላዊ ጉዳዮችን ለመፍታት መንግስታት እርምጃዎችን በደረጃ እንዲወስዱ ግዴታ ይጥላል ።

በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን እና የቤት ውስጥ ጥቃቶችን ለመከላከል እና ለመዋጋት የወጣው የአውሮፓ ምክር ቤት ስምምነት (Council of Europe Convention on Preventing and Combating Violence against Women and Domestic Violence)

ስምምነቱ የጾታ ትንኮሳ፣ አስገድዶ መድፈር፣ የግዳጅ ጋብቻ፣ የክብር ወንጀሎች፣ የብልት ግርዛት እና ሌሎች የጥቃት ዓይነቶች ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንደሆኑ እና በሴቶች እና በወንዶች መካከል እኩልነት እንዳይኖር ትልቅ እንቅፋት እንደሆኑ በመግቢያው ላይ በማስቀመጥ ሴቶችን ከጥቃት በመከላከል የሴቶች መብት እንዲከበር በሀገራት ላይ ግዴታን ይጥላል፡፡

ሴቶች መብት በኢትዮጵያ የሕግ ስርዓት ያለው ስፍራ

ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ከማቋቋም ጀምሮ የዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት መግለጫ(UDHR) ላይ በቀዳሚነት ከተሳተፉና ከፈረሙ ሃገራት ውስጥ ትገኛለች፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የሲቪልና ፖለቲካ መብቶች ስምምነት፣ የኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊና ባህላዊ መብቶች ስምምነት፣ በሴቶች ላይ የሚደረግ ማንኛውንም አይነት ልዩነት ለማስወገድ የተደረገው ስምምነትን የፈረመች ሲሆን እ.ኤ.አ ሀምሌ 1980 ዓ.ም አለም አቀፉን በሴቶች ላይ የሚደረግ ማንኛውንም አድሏዊ ልዩነት ለማስወገድ የወጣውን ስምምነት በመፈረም የሴቶችን መብት የሚያስከብሩ የተለያዩ እርምጃዎችን ስትወስድ ቆይታለች፡፡ ከነዚህም ተግባራት የሴቶችን መብት በህገ መንግስቱና ሌሎች ዝርዝር ህጎች ውስጥ እንዲሁም በፖሊሲና ስትራቴጂ ሰነዶች ውስጥ እንዲካተቱ ማድረግ የሚገኝበት ሲሆን ከነዚህም የሕግና የፖሊሲ ማእቀፎች ውስጥ የሚከተሉት ዋንኞቹ ናቸው፡-

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ መንግሥት

በኢ.ፌ.ድ. ሪ ህገ መንግሥት ስለሴቶች መብት እውቅና እና ጥበቃ ያደረጉ ድንጋጌዎችን ስንመለከትበአንቀጽ 34 እና 35 ስር ወንዶች እና ሴቶች በጋብቻ አፈፃፀም፣በጋብቻ ዘመንና በፍቺ ጊዜ እኩል መብት እንዳላቸው ያስቀመጠ ሲሆንበፍቺ ጊዜም የልጆች መብትና ጥቅም እንዲከበር የሚያደርጉ ድንጋጌዎች እንደሚገነገጉ ያስቀምጣል፡፡

የተሻሻለው የፌደራል የቤተሰብ ሕግ አዋጅ 213/1992

በተሻሻለውን የፌደራል የቤተሰብ ሕግ አዋጅ ቁጥር 213/92 ለሴቶች መብት ጥበቃ ካደረጉ ድንጋጌዎች ስንመለከት በጋብቻ ወቅት ሁለቱም ተጋቢዎች ጋብቻን ለመመስረት ነፃ ፍቃዳቸውን መስጠት እንዳለባቸው ያስቀምጣል፡፡ በተጨማሪም የተጋቢዎች የጋብቻ እድሜ ለሁለቱም እኩል 18 ዓመት መሆኑ ተጋቢዎች የኑሮ ጫናን በእኩል ኃላፊነት እንዲጋሩ የሚያስችላቸው ነው፡፡ ሌላው በቤተሰብ ህጉ አንቀጽ 49/1 ስር እንደተደነገገው ባልና ሚስት እርስ በርሳቸው መከባበር፣ መተጋገዝ እና መደጋገፍ አለባቸው፡፡ ይህም ሴቶች ተገቢውን ክብር የማግኘት መብት እንዳላቸው አመላካች ነው፡፡

የመንግሥት ሰራተኞች አዋጅ ቁጥር 1064/2010፣

ሴቶች ከሚሰማሩባቸው የሥራ መስኮች መካከል በተለያዩ መንግሥት መስሪያ ቤቶች መቀጠር አንዱ ነው፡፡ በመሆኑም የፌደራል መንግሥት ሰራተኞች አዋጅ ቁጥር 1064/2010 ሴት የመንግሥት ሰራተኞች ሴቶችን የተመለከቱ ድንጋጌዎች አካቷል፡፡ ለምሳሌ ሴት ሰራተኞች በእርግዝናቸው ጊዜ የህክምና ምርመራ ለማድረግ እና ሕክምና ፈቃድ ሲያዝላቸው ደሞዝ የሚከፈልበት ፈቃድ የማግኘት መብት አላቸው::

የአሰሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1156/2011)

ሴቶች በመንግሥት መስሪያ ቤት ተቀጥረው ከመስራታቸው ውጪ በግል መስሪያ ቤት ውስጥ ተቀጥረው ሊሰሩ ይችላሉ፡፡ ስለሆነም በግል መስሪያ ቤት ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩ ሴቶችን መብት የሚያስጠብቁ ድንጋጌዎች በየአሰሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 ውስጥ ተካተው ይገኛሉ፡፡

የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ፖሊሲ

በ1986 ዓ.ም ብሔራዊ የሴቶች ጉዳይ ፖሊሲ የወጣ ሲሆን ፖሊሲው በሀገራችን በገጠርም ሆነ በከተማ ያሉ ሴቶች ከባህልና ልማድ እንዲሁም በሌሎች ተደራራቢ ምክንያቶች ያለባቸውን ጫና እውቅና በመስጠት በቀጣይ በፖለቲካ፣ በማኅበራዊ እና በኢኮኖሚ ዘርፎች እኩል ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሁኔታ መዘርጋት እንዳለበት መሠረት ጥሏል፡፡ ለሴቶች ጤና እና የአካል ደኅንነት አደጋ ሆነው እንደ ግርዛትና ያለእድሜ ጋብቻ የመሳሰሉ የቆዩት ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች መወገድ እንዳለባቸው በአፅኖት አስቀምጧል፡፡

በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃት ዓይነቶች

ከዚህ በታች የተዘተዘሩት የጥቃት አይነቶች በተናጠል ወይም በተደራራቢነት በሴቶች ላይ ሊፈፀሙ የሚችሉ ናቸዉ፡፡

  1. የቤት ውስጥ ጥቃት፡- በስፋት የሚታወቅ የጥቃት ዓይነት ሲሆን በቤት ውስጥ እና በቤት ውስጥ ጉዳይ ምክንያት የሚፈፀም ማንኛውም ጥቃት ማለትም በሃይል፣ በቃላት እና በምልክት፣ በአካል ላይ፣ በሞራል እና ስነ-ልቦና እንዲሁም በማንኛውም መንገድ ነጻነትን በሚጋፋ ሁኔታ የሚፈፀም ጥቃትን ያካትታል፡፡ ምሳሌ ፡- ቀላልና ከባድ አካል ጉዳት፣ ስድብ፣ ዛቻ….ወ.ዘ.ተ.
  2. ኢኮኖሚያዊ ጥቃት፡- በማንኛውም መንገድ የንብረት እና የኢኮኖሚ መብት መጋፋት ወይም መንፈግን የሚያካትት ሲሆን ብዙ ጊዜ ሴቶችና ሕፃናት ንብረት ወይም ሃብት እንዳያፈሩ እና በንብረታቸው እንዳያዙ ወይም እንዳይጠቀሙ በማድረግ የንብረት ባለቤትነት መብታቸውን በማሳጣት ለሰሩት ሥራ ተገቢውን ክፍያ ባለመስጠት በጥገኝነት እንዲኖሩ ማድረግ ይገለጻል፡፡ ምሳሌ፡- የጉልበት ብዝበዛ፣ የጋራ ንብረትን /ሀብት ተጠቃሚ አለመሆን/፣ ለሰሩት ስራ ተገቢውን ክፍያ ያለመክፈል ወ.ዘ.ተ.
  3. አካላዊ ጥቃት ፡- በማንኛውም መንገድ በአካል ላይ የሚፈፀም የሃይል ጥቃት ነው፡፡ ለምሳሌ፡- መምታት፣ መገፍተር፣ በአካል ወይም በህይወት ላይ ጉዳት ማድረስ እስከ ግድያ ያለውን ያጠቃልላል፡፡
  4. ወሲባዊ ጥቃት ፡- ሃይልን በመጠቀም በሌላ ሰው ላይ ያለፍላጓቷ የሚፈፀም ማንኛውም የወሲብ ድርጊትና የወሲብ ድርጊትን የመሰሉ ለመልካም ፀባይ ተቃራኒ የሆኑ ድርጊቶችና ትንኮሳዎችን ያጠቃልላል፡፡ ለምሳሌ ፡- አስገድዶ መድፈር፣ የወሲብ ንግድ፣ ጾታዊ ትንኮሳ፣ ግብረ-ሰዶምና የመሳሰሉት ናቸው፡፡
  5. ሥነ-ልቦናዊ ጥቃት፡- አስቦ የሌላውን ሰው በተለይ የሴቶችን ሞራልና ስሜታቸውን በሚጎዳ ሁኔታ በማዋረድና በማሸማቀቅ የሚፈፀም ጥቃት ነው፡፡ ለምሳሌ በሠው ፊትና በአደባባይ ሞራል የሚነኩ ቃላትን በመጠቀም መሳደብና የበታች እንደሆኑ መግለፅ ወ.ዘ.ተ.
  6. ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ጥቃት፡- በማህረሰቡ የተለያዩ የአመለካከትና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ምክንያት በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚፈፀሙ ማናቸውም የጤና፣ የስነ-ልቦና እና የኢኮኖሚያዊ መብታቸው ላይ ተፅኖና ጉዳት የሚደርሱ ጥቃቶች ናቸው፡፡

በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃት በማን እና የት ይፈጸማል?

ጥቃት በማንኛውንም ሰው፣ በማንኛውም ስፍራ በማንም ሰው ላይ ሊፈጸም ይችላል፡፡ ይህም ማለት በቤተሰብ፣ በቅርብ ዘመድ፣ በባል፣ በወንድም፣ ፣ በመምህራን፣ በህክምና ባለሞያዎች በቢሮ ሃላፊዎች፣ በመሪዎችና በባለስልጣናት፣ በሃይማኖት አባቶች እና በማንኛዉም የህብረተሰብ ክፍል በቤት፣ በትምህርት ቤት፣ በስራ ቦታ፣ በመንገድ እና በማንኛዉም ቦታ ሊፈጸም ይችላል፡፡ በተጨማሪም በተማረና ባልተማረ፣ በህብታም ሆነ በድሀ ግለሰብ በሁሉም አካባቢና የህብረተሰብ ክፍል ጥቃት ፈጻሚዎች ያሉ ሲሆን ጥቃት የሚፈጸምባቸዉም ሴቶች የተማሩ፣ ያልተማሩ፣ ህብታም ወይም ድሀ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ሕግ

በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ወንጀል አድርጎ ቅጣት በማስቀመጥ በ1996 ዓ.ም የወጣዉ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ሕግ እንዲወጣ ካስፈለገባቸዉ ዋና ዋና ምክንያቶች መካከል ኢትዮጵያ በተቀበለቻቸዉ ዓለም አቀፍ ስምነቶች እና በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ሕገ መንግሥት የሴቶችና ሕፃናት መብት እዉቅና ማግኘታቸዉና በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚፈፀሙ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ወንጀል ተብለዉ እንዲካተቱ ለማድረግ እንደሆነ በመግቢያዉ ላይ ተቀምጧል፡፡ ስለሆነም የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ሕግ በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን በተመለከተ በተለያዩ ክፍሎች ስር በተቀመጡ ድንጋጌዎቹ ላይ በወንጀልነት እና ቅጣታቸዉ ተቀምጧል፡፡ ለምሳሌነትም

  1. በጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች አማካይነት በእርጉዝ ሴቶች እና ሕፃናት ህይወት ላይ ጉዳት ማድረስ ፣በጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች አማካይነት በእርጉዝ ሴቶች እና ሕፃናት አካል ላይ ጉዳት ማድረስ ፣በትዳር ጓደኛ ወይም ከጋብቻ ውጪ በሆነ የግብረስጋ ግንኙነት በሚኖር ሰው ላይ ጥቃት ማድረስ ፣ሴትን መግረዝ፣የሴት ብልት መስፋት የመሳሰሉት ወንጀሎች እንደየሁኔታው እየታየ በመቀጮ ወይም እስከ 10 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ሊያስቀጣ ይችላል፡፡
  2. የሰዉን ሕይወት፣ አካል ወይም ጤንነት ለአደጋ በማጋለጥ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ውስጥ ሰውን መግደል፣ሰውን ለአደጋ ማጋለጥ ወይም መተው ፣በሰዉ የግል ነጻነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ፣ሴትን መጥለፍ፣የአዕምሮ ህመምተኛ ወይም የመከላከል አቅም የሌላትን ሴት መጥለፍ የመሳሰሉት በእስራት የሚያስቀጡ ሲሆን ከባድ ግድያ በሆነ ጊዜ እሰከ ሞት ሊያስቀጣ ይችላል፡፡
  3. የአስገድዶ መድፈር ፣ አንዲት ሴት ያለባትን ከፍ ያለ ችግር ወይም ጥገኝነትዋን ምክንያት በማድረግ የሚፈጸም ወሲባዊ ድርጊት፣ሴቶችን እና ለአካለ መጠን ያልደረሱ ልጆችን ለዝሙት አዳሪነት በማቃጠር መነገድ፣ ሴቶችን እና ለአካለ መጠን ያልደረሱ ልጆችን ለዝሙት ለማቅረብ የሚደረግ ዝግጅት እንደየ ሁኔታው በቀላል እስራት ወይም ከ 3 እስከ 20 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት የሚያስቀጡ ወንጀሎች ናቸው፡፡

ማጠቃለያ

በአጠቃላይ ሴቶች ሰዎች በመሆናቸዉ ብቻ የተጎናጸፏቸዉን እና በተለያዩ ዓለም ዓቀፍ ሰነዶች እዉቅና የተሰጣቸዉን ሰብዓዊ መብቶች ያሎቸው እንዲሁም ሴቶች ሴት በመሆናቸው እና ቀደሞ በነበሩ የሴቶች መብት ጥሰቶችን አስቀርቶ ከወንዶች እኩል መብታቸው እንዲከበር ለማድረግ በልዩ ሁኔታ የሚሰጣቸው መብቶች ጭምር መከበር አለባቸው፡፡ እነዚህን መብቶች ሁሉም ሰው ወንዱም ሴቱም ሊያከብራቸው የሚገቡ ናቸው፡፡ ይህ ሳይደረግ ቀርቶ መብቶችን የሚጥሱ ሰዎች ካሉ በሕግ የሚያስጠይቃቸው ተግባር ይሆናል፡፡

በንቃተ ሕግ፣ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ