የሕዋስ፣ ሕብረ-ሕዋስ ወይም አካል ልገሳ እና ንቅለ ተከላ በኢትዮጵያ ሕግ

ማውጫ

Share this Article

መግቢያ

የሕዋስ፣ ህብረ-ህዋስ፣ የአካል ክፍል ወይም የአካል ልገሳ እና ንቅለ ተከላ አገልግሎቶች በዘመናዊ ሕክምና ውስጥ ሕይወት ለመታደግ እና የታካሚዎችን ጤና ለመጠበቅ ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ። ይሁን እንጂ እነዚህ አገልግሎቶች በሕግ እና የሥነ ምግባር መመሪያዎች መሠረት በጥንቃቄ ካልተተገበሩ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትሉ ይችላሉ፡፡ በመሆኑም በኢትዮጵያ የጤና አገልግሎት  አዋጅ ቁጥር 1362/2017 የዚህን አገልግሎት አሰጣጥ ሂደት፣ ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያያዥነት ያላቸው የተከለከሉ ድርጊቶች እና የሚያስከትሉትን የግ ተጠያቂነትን ደንግጓል። ይህ ጽሁፍ እነዚህን ጉዳዮች በአጭሩ ይዳስሳል።

የንቅለ-ተከላ ምንነት

በአዋጁ አንቀጽ 2(31) መሠረት ንቅለ ተከላ ማለት የተለገሰን ህዋስ፣ ህብረ ህዋስ፣ የአካል ክፍል ወይም አካል ለተቀባይ የሚሰጥበት የህክምና አገልግሎት ነው፡፡ በዚህ ትርጓሜ ውስጥ የተካተቱት ህዋስ፣ ህብረ ህዋስ፣ የአካል ክፍል ወይም አካል በአዋጁ ላይ የየራሳቸው ትርጓሜ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ይኸውም ህዋስ ማለት የሰው አካል የተገነባበት የተለየ እና የታወቀ ሥራ የሚሰራ ሕይወት ያለው የሰው አካል የመጨረሻው ቅንጣት ሲሆን ሕብረ-ህዋስ ከሰውነት አካል የሚወሰድ በቅርፅ፣ በይዘትና በተግባር ተመሳሳይ የሆነ የህዋስ ስብስብ ነው፡፡ በተጨማሪም አካል ከሕብረ ህዋስ ስብስብ የተገነባ እና የተለየ ተግባር የሚያከናውን የሰውነት ክፍል እንደሆነ እንዲሁም ሙሉ አካል በሕብረ-ህዋሳትና እና በአካላት ስብስብ የተዋቀረ የአንድ ሰው ሙሉ አካል እንደሆነ በአዋጁ አንቀጽ 2(25-28) ትርጓሜ ተሰጥቶታል፡፡

የንቅለተከላ ሕክምና አገልግሎት የሚከናወንበት ሁኔታ

የሕዋስ፣ የሕብረ ሕዋስ፣ የአካል ክፍል እና የአካል ንቅለ ተከላ ሕክምናን ማከናወን የሚቻለው የተቀባዩን ሕይወት ለማቆየት ወይም የሰውነት አቋሙን ለማስተካከል ሌላ የተሻለ አማራጭ መንገድ የማይገኝ መሆኑ በሕክምና ቦርድ ሲረጋገጥ ብቻ እንደሆነ በአዋጁ አንቀጽ 22 ላይ ተደንግጓል፡፡ የተሻለ አማራጭ አለመኖሩ እና ንቅለ ተከላ አስፈላጊ ሕክምና መሆኑ ከተረጋገጠ በኋላም በአዋጁ አንቀጽ 21 መሠረት ለጋሹ ለመለገስ ፈቃደኛ መሆኑን መግለፅ የሚጠበቅበት ሲሆን ይህን ፈቃዱንም ከንቅለ ተከላው በፊት በማንኛውም ጊዜ የመሻር መብቱ የተጠበቀ ነው፡፡

ከንቅለ ተከላ አገልግሎት ካር በተያያዘ የተከለከሉ ድርጊቶች እና የሚያስከትሉት የሕግ ተጠያቂነት

በኢትዮጵያ የጤና አገልግሎት አዋጅ ቁጥር 1362/2017 ከደም፣ ህዋስ፣ ሕብረ ሕዋስ፣ የአካል ክፍል ወይም የአካል ልገሳ እና ንቅለ ተከላ አገልግሎቶች ጋር ተያያዥነት ያላቸው የተከለከሉ ድርጊቶችን እና የሚያስከትሉትን የሕግ ተጠያቂነት ደንግጓል፡፡

ይኸውም

 ያለ ለጋሹ ፈቃድ የሰውነት አካልን ወይም የአካል ክፍልን መውሰድ የተከለከለ ስለመሆኑ

ያለ ለጋሹ ፍቃድ የሰውነት አካልን ወይም የአካል ክፍልን የወሰደ ሰው ከአምስት ዓመት በማያንስ እና ከአስራ አምስት ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት ሊቀጣ እንደሚችል በአዋጁ አንቀጽ 55(4እና5) ተደንግጓል፡፡

ድርጊቱን የፈጸመው የጤና ተቋም ከሆነ ከአንድ ሚሊዮን ብር ያላነሰ እና ከአምስት ሚሊዮን ብር ያልበለጠ መቀጮ ይቀጣል፡፡

በተመሳሳይ የገንዘብ ወይም ሌላ ማንኛውንም ዓይነት ጥቅም ማግኘትን መሠረት ያላደረገ የለጋሹ ፈቃድ ሳይገኝ ፡-

  • የሕዋስ ወይም የሕብረ ሕዋስ ንቅለ ተከላ የሕክምና አገልግሎት የሰጠ ባለሙያ ከሦስት ዓመት በማያንስ እና ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት፣
  • የአካል ወይም የአካል ክፍል ንቅለ ተከላ ሕክምና አገልግሎት የሰጠ ባለሙያ ከሰባት ዓመት በማያንስና ከአስራ አምስት ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እሥራት፣
  • የተገኘን ሕዋስ፣ ሕብረ ሕዋስ፣ የአካል ክፍል ወይም አካል በመጠቀም የንቅለ ተከላ ሕክምና አገልግሎት የሰጠ የጤና ተቋም ከብር አንድ ሚሊዮን በማያንስና ከብር ሶስት ሚሊዮን በማይበልጥ የገንዘብ መቀጮ እንደሚቀጣ በአዋጁ አንቀጽ 55(6) ላይ ደንግጓል፡፡

 የአካል ክፍል መግዛት ወይም መሸጥ የተከለከለ ስለመሆኑ

የሕዋስ፣ ሕብረ ሕዋስ፣ የአካል ክፍል ወይም አካልን በገንዘብ፣ በውለታ ወይም ሌላ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በመስጠት የተቀበለ ሰው ከአምስት ዓመት በማያንስ እና ከአስራ አምስት ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት ሊቀጣ እንደሚችል ሲሆን ሕዋስ፣ ሕብረ-ህዋስ፣ የአካል ክፍል ወይም አካልን በገንዘብ፣ በውለታ ወይም ሌላ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማግኘት የሰጠ ወይም እንዲሰጥ ትብብር ያደረገ ሰው ከሦስት ዓመት በማያንስ እና ከሰባት ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት እንደሚቀጣ በአዋጁ አንቀጽ 55(7) ተደንግጓል፡፡ ድርጊቱ የተፈጸመው በተቋም ከሆነ በአዋጁ አንቀጽ 55(8) መሠረት ከብር ሁለት ሚሊዮን በማያንስና ከአምስት ሚሊዮን በማይበልጥ የገንዘብ መቀጮ ሊቀጣ ይችላል፡፡

ግ ከተፈቀደው አግባብ ውጪ መያዝ ወይም ማጓጓዝ

በሕግ ከተፈቀደው አግባብ ውጪ ሕዋስ ወይም ሕብረ ሕዋስ መያዝ ወይም ማጓጓዝ የተከለከለ ተግባር ሲሆን ይህንን ድርጊት ሲፈፅም የተገኘ ማንኛውም ሰው ከሦስት ዓመት በማያንስና ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት ሊቀጣ ይቀጣል፡፡ አካል ወይም የአካል ክፍል ይዞ ወይም ሲያጓጉዝ የተገኘ ማንኛውም ሰው ደግሞ ከሰባት ዓመት በማያንስ እና ከአስራ አምስት ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እሥራት የሚቀጣ ሲሆን ድርጊቱ የተፈጸመው በግል ተቋም እንደሆነ እንደነገሩ ሁኔታ ከብር ሦስት መቶ ሺህ በማያንስና ከአምስት ሚሊዮን በማይበልጥ የገንዘብ መቀጮ ይቀጣል፡፡ ድርጊቱ በጤና ተቋም የተፈጸመ እንደሆነ ተቋሙ ከብር አንድ መቶ ሺ እስከ አምስት መቶ ሺ በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ሊቀጣ እንደሚችል በአዋጁ አንቀጽ 55(9እና10) ተደንግጓል፡፡

ማጠቃለያ

የደም፣ ሕዋስ፣ ሕብረ ሕዋስ፣ የአካል ክፍል ወይም የአካል ልገሳ እና ንቅለ ተከላ አገልግሎቶች በተገቢ ሕጋዊ እና ሥነ ምግባራዊ መመሪያዎች መሠረት መከናወን ያለበት እንደመሆኑ የኢትዮጵያ የጤና አገልግሎት አዋጅ ይህንን በዝርዝር ደንግጓል፡፡ ስለሆነም የጤና ባለሙያዎች እና ተቋማት ሕጉን በማክበር ለታካሚው ደህንነቱ የተጠበቀ እና ጥራት ያለው የሕክምና አገልግሎት መስጠት ይጠበቅባቸዋል።

በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ።